Saturday, January 17, 2015

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ምዕራፍ ሁለት እረኞች ሰንፈዋል

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ


ምዕራፍ ሁለት



ክፍል አስር



እረኞች ሰንፈዋል


በክፍል አስር የምንመለከተው ሌላው የእረኞች ስንፍና ያለማየት ስንፍና ነው የመንጋው እረኞች ስንሆን የምናይ ልንሆን ይገባል ምክንያቱም መንፈሳዊ ሥራ እይታን የሚጠይቅ ሥራ ነው በጉልበት የምንሠራውና በድምጽ ብልጫ የምናካሂደው አይደለም እግዚአብሔር ሙሴን ለእስራኤል ሕዝብ መሪ ሲያደርገው ዓይኑን ጭምር ነው የከፈተለት በመዝሙር 77 20 ላይ በሙሴና በአሮን እጅ ሕዝብህን እንደ በጎች መራሃቸው ይለናል በሙሴና በአሮን የዓይን መከፈት ባይኖር እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ በጎች በእነርሱ እጅ አይመራም እጅ የሃይል የሥልጣን የአደራረግና የአካሄድ ምልክት ነውና እግዚአብሔርም ሕዝቡን ለሙሴና ለአሮን ለእጃቸውም ፈቃድ  አሳልፎ አይሰጥም ነበር ስለዚህ ሙሴና አሮን በዘመናቸው ከእግዚአብሔር የሆኑ ትክክለኛ የእስራኤል መሪዎችና መጋቢዎቻቸውም ነበሩ ማለት እንችላለን በተለይ ወደ ሙሴ ሕይወት ስንመጣ ሙሴ የዮቶርን የአማቱን የሚድያምን ካህን በጎች ሲጠብቅ ሳለ እስራኤልን ነጻ የማውጣት የመጠበቅና የመምራት ጥሪ ሲደርሰው በመጀመርያ ያለው ነገር የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነዽ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ ይለናል ታድያ ይህ ሙሴ በማየት ብቻ በዚያው ምድረበዳ ከበጎቹ ጋር አልቀረም በሕይወቱም ጭምር ውሳኔ በማድረግ ሙሴም፦ ልሂድና ቍጥቋጦው ስለ ምን አልተቃጠለም ? ይህን ታላቅ ራእይ ልይ አለ ይለናል በመሆኑም በዚህ የሙሴ ቁርጥ የማየት ውሳኔና መሻት ተመስርቶ ጌታ እግዚአብሔር ይህንን ነጻ የማውጣት እና የመሪነት ጥሪ ሰጠው ዘጸአት ምዕራፍ በሙሉ እንመልከት ታድያ ሙሴ ሲያይ አገልግሎቱን ነጻ ማውጣቱንና መሪነቱን ብቻ አይደለም ያየው ራሱን የግል ሕይወቱንና ማንነቱንም ጭምር ነበር የተመለከተው ጌታ እግዚአብሔርም ከብዙ ምልልስ በኋላ በብቃት ወደ ወደ ግብጽ ከግዞት ቤት ሕዝቡን እንዲያወጣ ላከው ስለሆነም እንግዲህ ይህ የሙሴ አይቶ አለመቅረት ልይ ማለትና ማየት የእስራኤልን ሕዝብ ብቻ አይደለም የጠቀመው ራሱን ሙሴን ጭምር በብዙ ጠቅሞታል ማየታችን ለሌሎች ጥቅም ብቻ ሳይሆን በመጀመርያ ለራሳችን ነው እኛ ያላየነውንና ያላጣጣምነውን ውሳኔም ያልሰጠንበትን ነገር ሌሎች እንዲያዩትና እንዲያጣጥሙት  ውሳኔም እንዲሰጡበት ማድረግ አንችልም ሙሴ ባየው ነገር ውስጥ ነው ብድራቱን ትኩር ብሎ የተመለከተው፣ የፈርኦን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ ያለው ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ መነቀፍን ከእግዚአብሔር ሕዝብም ጋር መከራ መቀበልን የመረጠው ባያይ ኖሮ እነዚህን ምርጫዎች ሁሉ የመቀበልና የማስተናገድ እድሉም ሆነ አቅሙም አይኖረውም ነበር ዕብራውያን 11 23 _ 31 ይህንን ሃሳብ ዛሬ ላይ ወዳለነው ወደ አገልጋዮች ወደ መጋቢዎችና ወደ መሪዎች ስናመጣ በሕይወታችን የማየት ዕድል ገጥሞንና ተጠግተን ያየናቸው ጥቂት የእግዚአብሔር ነገሮች በመሆናቸው ጥቂት ምዕራፎች ከተጓዝን በኋላ ብዙም ሳንቆይ ከሌሎች ጋራ ልንደራደር የመብት ጥያቄዎች እናነሳለን በጉዞ ላይ ሳሉ የዘብዴዎስ ልጆች ያደረጉት ይህንን ነበር  የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን አሉት እርሱም፦ በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን አሉት ኢየሱስ ግን፦ የምትለምኑትን አታውቁም እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ እኔ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን  አላቸው እርሱም፦ እንችላለን አሉት ኢየሱስም፦ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፥ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም አላቸው አሥሩም ሰምተው በያዕቆብና በዮሐንስ ይቈጡ ጀመር ኢየሱስም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የአሕዛብ አለቆች ተብሎ የምታስቡት እንዲገዙአቸው ታላላቆቻቸውም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም ሲላቸው እንመለከታለን የማርቆስ ወንጌል 10 35 _ 45 እግዚአብሔር ለአገልግሎቱ የጠራን ከሌሎች ይልቅ ለየት ብለንና መብት ኖሮን ወንበር እንድናገኝ ባገኘነውም ወንበር ሌሎችን እንድንገዛ በሌሎች ላይ እንድንፈርድ እንድንሰለጥንባቸውም ሳይሆን ታላቅ ልንሆን ስንወድ የሁሉ አገልጋይ ፊተኛ ልንሆን ስንወደ የሁሉ ባርያ ልንሆን ነው ለዚህ ነው ኢየሱስ የራሱን የመጨረሻ ዓላማ ግልጽ አድርጎ በመናገር የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም ሲል የተናገረው የእኛም የአገልግሎት መጠንና የመጨረሻ ደረጃ እንዲህ ሊሆን ይገባል የእስራኤል መሪ ሙሴ ምንም እንኳ በብሉይ ኪዳን የተጠራ ቢሆንም ያደረገው ነገር እንደዚህ ነው ነጻ አውጣ ለተባለው ለእስራኤል ሕዝብ  ራሱን ሰጠ ይህ ሕዝብ ከሚጠፋ እኔን ከጻፍከው መጽሐፍ ደምስሰኝ አለ አንድም ቀን ሕዝቡ በጉዞ ላይ ሳሉ የራስ የሆነ የመብት ጥያቄ ሲያነሳ በዚህም ምክንያት ሕዝብን ሲያከፋፍልና ሲከፋፍል አላገኘነውም ዓይናችን ሲከፈት ሕዝብን ወዴት መምራት እንዳለብን እናውቃለን ዓይናችን ካልተከፈተ ግን የዘብዴዎስ ዓይነት ልጆችና ሌላም ሌላም የመብት ጥያቄዎችን የምናነሳ ለምቾቶቻችንና ለወንበሮቻችን የምንታገል የምንሞትም እንሆናለን ለዚህ ነው  በሉቃስ ወንጌል 6 39 ላይ  ምሳሌም አላቸው ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን፧ ሁለቱ በጕድጓድ አይወድቁምን፧ በማለት የተናገረው ከዚህም የተነሳ መሐል ላይ የምናነሳቸው አንዳንድ ጥያቄዎቻችንም ይሁኑ መብት አለን ብለን በወንበሮቻችንም ተኩራርተን የምናካሂዳቸው ክፉ ተግባሮች ዛሬም  ላይ ቢሆን እውር የእውር መሪ አስብሎናል ከዚህ ይልቅ በኢሳይያስ 42 6 ላይ እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፥ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅሕማለሁ፥ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ ይላልና እንደገናም በዘካርያስ 11 15 _ 17 ላይ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ ዳግመኛም የሰነፍን እረኛ ዕቃ ውሰድ እነሆ፥ በአገሩ ውስጥ እረኛ አስነሣለሁ እርሱም የጠፋውን አያስብም፥ የባዘነውን አይፈልግም፥ የተሰበረውን አይጠግንም የዳነውንም አይቀልብም፥ ነገር ግን የሰባውን ሥጋ ይበላል፥ ሰኰናውንም ይቀለጣጥማል መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት፦ ሰይፍ በክንዱና በቀኝ ዓይኑ ላይ ይሆናል ክንዱም አጥብቃ ትደርቃለች፥ ቀኝ ዓይኑም ፈጽሞ ትጨልማለች ስለሚል ተግባራችን ከግዞት ቤት ከጨለማ ሥራ ማውጣት ዓይንን መክፈት የጠፋውን ማሰብ የባዘነውን መፈለግ የተሰበረውን መጠገን የዳነውን መቀለብ ቢሆን የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን አክሊል ይሸልመናል እግዚአብሔር የዚህ ሰው ይበለን


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ











No comments:

Post a Comment