Thursday, February 5, 2015

ሳሙኤልን ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር

ለቅዱስን የታዘዘ ወቅታዊ መልዕክት


ክፍል ሁለት


ሳሙኤልን ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር


ሳሙኤልም ሳኦልን አላበጀህም አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን
ትዕዛዝ አልጠበክም ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥጥን በእስራኤል
ላይ ለዘላለም አጽንቶልህ ነበር አሁንም መንግሥጥ አይጸናም
እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል እግዚአብሔርም
ያዘዘህን አልጠበክምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን
ዘንድ አዝዞታል አለው

     1  ሳሙኤል 13 13 እና 14

በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ ሳኦልን ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር የአክብረኝ ነገር በመሆኑ እርሱም፦ በድያለሁ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት፥ እባክህ፥ አክብረኝ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው ሳሙኤልም ከሳኦል በኋላ ተመለሰ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ የሚለውን ሃሳብ አንስተን ሳኦል ከማንምና ከምንም ይልቅ ክብሩን ያስቀደመ ሰው በመሆኑ ሳሙኤል ሳኦልን በመተባበር ትክክልም እንደሆነ በመግለጽ ከእርሱ ጋር ተመልሶ በሕዝቡ ሽማግሌዎችና በእስራኤል ፊት ሳኦል መንግሥቱ የጸና እና ለሌላም የማይሰጥ እውነተኛ ንጉሥ ነው በማለት በእግዚአብሔር ፊት ሳይቀር ከእርሱ ጋር በመስገድና በማምለክ እንዲያከብረው ተምኔቱንም እንዲፈጽምለት ያደረገውን ሙከራና የሳሙኤልንም ከአንተ ጋር አልመለስም ሲል የወሰደውን እርምጃ እንዲሁም አለመስማማት በሰፊው ተመልክተናል አያይዘንም በዚህ በክፍል ሁለት መልዕክት ታድያ የምናየው የዚሁ የሳሙኤልን ያሳሰበውንና ግድ ያለውን ነገር ከሳኦል ጋር በማነጻጸር ይሆናል ሳሙኤልን ያሳሰበውንና ግድ ያለውን ነገር  ሳኦል ካሳሰበውና ግድ ካለው ነገር በብዙ ይለያል ሳኦል ከምንም በላይ ቅድሚያ በመስጠት ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር በእስራኤልና በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት የነበረው ክብሩ ማንነቱ መንግሥቱ ሲሆን ሳሙኤል ደግሞ ያሳሰበው ነገር ሳኦል ከምንም ይልቅ እንዲጠብቀው ታዞ ያልጠበቀውና ያቃለለውም የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነው በመሆኑም እነዚህን ሁለቱን የሳኦልና የሳሙኤልን ግድ የተሰኙበትን ሃሳቦች በንጽጽር ተመልክተን እኛም የየራሳችንን አቋም  ወይም መንገድ እንይዛለን ማለት ነው ነገር ግን  እኛንስ የትኛው ነገር ግድ ሊለን ይገባል ? ንጉሥ ሳኦልን ግድ ያለው ነገር ? ወይስ ሳሙኤል ? መልሱን ለእናንተ ለአንባቢዎች እየተውኩ በመቀጠልም እግዚአብሔር የሚያስተምረንን እውነቶች እንደሚከተለው እንመለከታለን ሳሙኤል ሳኦል ካሳሰበውና ግድም ካለው ነገር ይልቅ ሳኦል እንዲያደርግ ታዞ ያልፈጸመው የእግዚአብሔር ሃሳብ አሳስቦት ግድም ብሎት  ሳኦልን አላበጀህም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቅህም ያለ ቢሆንም ጉዳዩ ግን በዚሁ ሳሙኤል ምስጢር ሆኖ የቀረ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ደርሶ ከመለኮታዊው አምላክ ከእግዚአብሔር ለዚሁ ለንጉሥ ሳኦል የተላለፈ  እና የማይለወጥ ውሳኔም  የመጣ በመሆኑ ሳሙኤል   በመልዕክቱ እርግጠኛ ነበርና እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው  ወገኖቼ ለሁለ ነገራችን የኔ ለምንለው ክብራችንና ማንነታችን ሥልጣናችን ሊሆን ይችላል ዘውዳችን ንግሥናችን ዙፋናችን አገልግሎታችን የአገልግሎት ስማችን መሪነታችን አስተዳዳሪነታችን ወዘተርፈ ለዚህ ነገሮቻችን መጠብቅ ምክንያቱ ግን እነዚህ ነገሮች ሳይሆኑ ምክንያቱ ወይም መሠረቱ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ መጠበቃችን ነው በነዚህ ነገሮቻችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመሪነትና በቀዳሚነት ካልጠበቅን እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከእኛ ጋር አይሆኑም ዛሬ ላይ ባይሆንም ለእኛም ባይመስለንም ቀስ በቀስ ግን ከእኛ እየተንሸራተቱ እየከዱንና እየጣሉን መሄዳቸው አይቀሬ ነው ንጉሥ ሳኦልን ንግሥናው ቅባቱ ዘውዱ ዙፋኑና ክብሩ እየከዳው የሄደው ቀስ እያለ ነው ሳኦል ንጉሥ ነኝ ብሎና ዘውድ ጭኖ ቤተመንግሥት ዙፋን ላይ ቢቀመጥም ንጉሥ እንዳይሆን አቅም ያሳጡት ብዙ ነገሮች ነበሩ በዚህም ምክንያት ክፉ መንፈስ ይጫወትበት እንደነበር ከመጽሐፉ እናስተውላለን ዛሬም ቢሆን ያለው ሁኔታ ይሄ ነው ዛሬም  አገልጋዮቻችን አንዳንዶች መሪዎች ናቸው የምንላቸው ሳይቀሩ ምንም እንኳ እንዲህና እንዲያ እያደረግን ነው አለን በቦታው ብለው ቢናገሩም መንፈሳዊ አቅም ያጡበት ጉዳይ እንዳለ  ግን ከነገሮቻቸውና ከሁኔታዎቻቸው ማስተዋል ችለናል ለዚህ መፍትሔው ምንም ሳይሉ ምክንያት ሳያበዙና  ልብንም ሳያደነድኑ እንደሎዶቅያ ቤተክርስቲያንም እኔ ሙሉ ነኝ አንዳች አያስፈልገኝም ሳይሉ በጊዜ ወደ እግዚአብሔር በንስሐ መመለስ የተዉትንና ቸልም ያሉትን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ መፈጸም የናቁትን ሊሰሙትም ያልፈለጉትን የእግዚአብሔር ቃል ዳግመኛ ሊያከብሩት መመለስ አማራጭ የሌለው ነገር ነው ይህ ካልሆነ ግን ፍጻሜው መልካም አይሆንም ንጉሥ ሳኦል የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜያለሁ እያለ ከላይ ታች ቢልም እንደገናም የፍጻሜ ገመዱን ለማርዘም ፈልጎ ትግል ውስጥ ቢገባና የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግም ውጤቱ ግን አሳዛኝና እጅግም የከፋ ነበር እግዚአብሔር ከንግሥናችን ከዘውዳችንና ከስማችን ጋር ሳይሆን ሁልጊዜም ከትዕዛዛቱ ጋር ነው ያለው ለዚህም ነው ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ ያለን ሕዝቅኤል 36 25 _ 27 ከርኩሰታችን ነጽተንና የድንጋዩ ልብ ወጥቶልን የሥጋ ልብ ሲሰጠን እግዚአብሔር መንፈሱን በውስጣችን ሊያኖርና በትዕዛዙ ሊያስኬደን አይቸገርም ነገር ግን ከዚህ ይልቅ ጌታ እግዚአብሔር የተቸገረው በደንዳናውና በድንጋዩ ልብ ነው ይህንን ሁኔታ በሐዲስ ኪዳኑም ስንመለከተው ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም አለ ዮሐንስ ወንጌል 14 21 24 ስንወደው ለዝና ለክብር ለዘውድና ለንግሥና  ስንል በትዕዛዙ ላይ አናምጽም የእግዚአብሔርንም ቃል አናቃልልም የእግዚአብሔር ትዕዛዛት ደግሞ እንድንፈጽመው የተጻፉልን የፍቅር ትእዛዞች ስለሆኑ ከባባዶች አይደሉም ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም ይለናል 1 ዮሐንስ መልዕክት 5 3 የምናነበውን አስተውለን እንድንጠቀምበት ጌታ ይርዳን


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment