Sunday, February 7, 2016

የትምህርት ርዕስ ፦ የምንሳለመውም ሆነ የምናሳልመው መስቀል ለእኛ የለንም ( ምንጭ ትምህርተ ኅቡአት ) ክፍ...የትምህርት ርዕስ ፦ የምንሳለመውም ሆነ የምናሳልመው መስቀል ለእኛ የለንም ( ምንጭ ትምህርተ ኅቡአት ) ክፍል አራት የተወደዳችሁ ወገኖች የመጨረሻውንና የማጠቃለያውን የክፍል አራት ትምህርታችንን እንቀጥላለን መስቀልን በተመለከተ መልክ ስላላየን የተቀረጸውንም ምስል ሆነ ማናቸውንም ምሳሌ እንዳናደርግ ተጠንቀቁ የተባልን ስለሆነ በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ በሚገባ ገልጬዋለሁና ያንን ትምህርት መመልከት ነው ስለዚህ መስቀል የተቀረጸ ምስል ስለሆነ እንኩዋን ከፈጣሪ ጋር ከምንም ጋር ልናመሳስለው ስግደትም ልንሰጠው የተገባን አይደለንም መስቀሉ ግኡዝ የሆነ የሰው እጅ ሥራ ነውና ስግደትም ሆነ መመለክ ይገባኛል አላለንም ሊለንም አይችልም ዘዳግም 4 ፥ 15 _ 24 ፤ ዘጸአት 20 ፥ 4 _ 6 ፤ የዮሐንስ ወንጌል 4 ፥ 23 እና 24 ከዚህም ሌላ እነዚህ ሁለቱ ፍጡራን የተባሉት ፈጣሪ ሆነው የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል የሚል የተጻፈም ሆነ የተሰማ ታሪክ የለም ምናልባትም የመናፍስት ኃይላት ከሲኦል ሆነው ያስተጋቡት ድምጽ ነው ብዬ እገምታለሁ እነዚህ መናፍስት ምናልባት በደካማ ሰዎች በኩል ጮኸው ለማርያምና ለመስቀል የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል ብለው ተናግረው ከሆነ እነርሱን ገስጸን ወደ መጡበት ወደዚያው ወደሲኦላቸው ስንልክ መናፍስቱ የተጠቀሙባቸውን ሰዎች ግን ለክርስቶስ እንማርካቸዋለን ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ አሁንም ጥናት ስናደርግ ከታሪክም እንደተረዳነው ለማርያምና ለመስቀል የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ አዘዙ የተባሉ ቅዱስ የወንጌል መምሕራን የደብረብርሃን ንጉሥ የነበረው ዘርዓ ያዕቆብና በእርሱ ዘመን የነበሩ መምህራን ናቸው ታሪኩ እንደሚገልጽልን በዚያን ጊዜ የኢየሱስን ብቸኛ አዳኝነት ከእግዚአብሔር ቃል በመረዳት አባ እስጢፋኖስ የሚባል በ14ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የተነሳ ይህ ሰው ብዙ ተከታዮች የነበሩት ከመሆኑ የተነሳም ለማርያምና ለመስቀል ለንጉሥም ጭምር አንሰግድም የሚል አቋም ነበራቸውና ይህን አቋማቸውን ለማስለወጥ የተጻፈ የጸሎት ድርሰት በመሆኑ እነዚህ መምህራን የተናገሩትና ያዘዙት እንደሆነ ይነገራል እነ አባ እስጢፋኖስም በዚህ አቋማቸው ስለገፉበት ንጉሥ ዘርአ ያዕቆብ አፍንጫቸውን አስፎንኖ ምላሳቸውን አስቆርጦ እንደገደላቸው በታሪክ ይነገራል በነዚህም ቅዱሳን ሞት ምክንያት በከተማው ላይ ብርሃን የወረደ መሆኑንም የታሪክ እውነታዎች ይመሠክራሉ ለዚህም ነው እንደ ቃሉ ያልሆነና የተሳሳተ ይህንን የጸሎት ድርሰት ያገኘነው ከላይ እንደገለጽኩት ማርያም ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ተብላ ከሴቶች ተለይታ የተመረጠች ብትሆንም የተመረጠችው የፈጣሪን ምስጋና ልትወስድ የተገባት ሆና የተመረጠች ሳትሆን ኢየሱስን ልትወልድ የተመረጠች ስለሆነ ነው በትንቢተ ኢሳይያስ 48 ፥ 3 ላይ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም ብሏል በመሆኑም ጌታ እግዚአብሔር ክብሩንም ሆነ ምስጋናውን ለማንም የሚሰጥ አይደለምና በዚህ ተረት መሰል ልብ ወለድ ቃል የሚሞኝልን ከዚህ በኋላ አናገኝም ይልቁንም ለራሳችን ተሞኝተን ጉድ እንዳንሆን ራሳችን ለራሳችን እንጠንቀቅ ከዚህ ይልቅ ለእኛ የሚበጀን ነቅተን በእውነት ቃል ተዋጅቶ መኖሩ ብልህነት ነውና ለቃሉ ልባችንን እንስጥ መስቀልን በተመለከተ አሁንም የኦርቶዶክስ የመስተብቊዕ መጽሐፍ ማለትም የምልጃው መጽሐፍ እንዳለው ለክብር የተመረጠ ሳይሆን መስቀል በዚያን በክርስቶስ ዘመን ወንጀለኛና ኃጢአተኛ የተባለ ሰው የሚቀጣበት መሳርያ ነው ለዚህም ነው ኢየሱስ በዚያ መስቀል ላይ መርገም ሆኖ የተቀጣልን ከሕግም እርግማን የዋጀን ገላትያ 3 ፥ 13 እና 14 መስቀሉ ትምክህት የሆነን ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ነው ኃጢአት ፣ ዓለም ፣ ሰይጣን ሥጋ የተሸነፉበት መሣርያ ሆኖአልና ገላትያ 6 ፥ 11 _ 16 ታድያ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ተሸነፉ ስንል ከኢየሱስ ትንሣኤ የተነሳ መሆኑን በማመን ነው እንጂ የማሸነፊያ አርማችን ነው ስንል ከአንጥረኛ ቤት ባመጣነው መስቀል ውስጥ ማሸነፍም ሆነ መሸነፍ የለም ያ ገዝተን ከየገበያው ያመጣነውና ወደፊትም እናመጣዋለን የምንለው መስቀል ኢየሱስ የተሰቀለበት ስንል በሲንቦልነት ከምንጠቀምበት ውጪ ሌላ የተለየ ትርጉም አንሰጠውም የኛ መስቀል የትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍ እንደነገረን የሚታሰብ እንጂ የሚታይ ስላልሆነ የሚታይ መስቀል ለእኛ የለንም ኃጢአት ዓለም ሥጋ ሰይጣን የተሸነፈበትና ዛሬም የሚሸነፍበት አርማችን ያልነው ያን የማይታየውንና እኛም በመንፈሳችን የምናስበውን መስቀል ነው በዚያ መስቀል ላይ የኢየሱስ ስለሆንን ሥጋን ከክፉ መሻቱና ምኞቱ ጋር ከዚህ በፊት ሰቅለናል አሁንም ሆነ ወደፊትም እንሰቅላለን ገላትያ 5 ፥ 24 በዚሁ መስቀል ላይ አሁንም የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው እናስወግድበታለን ኤፌሶን 4 ፥ 22 _ 24 ፤ ቆላስያስ 3 ፥ 5 _ 14 ታድያ ይህንን የምናደርገው ከአንጥረኛ ቤት ወይንም ከመርካቶ ወይንም ከሌላም ከሌላም ቦታ በሉት ገዝተን ባመጣነው ግዙፍና ቅርጽ ያለው መስቀል አይደለም ይህንን የምናደርገው በመንፈስ በምናስበውና በማይታየው መስቀል ነው ለእኛ የሚታሰብ እንጂ የሚታይ መስቀል የለንምና የተወደዳችሁ ቅዱሳን ሌላው ስለመስቀል መናገር የምፈልገው የትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍ እንደነገረን የሚታሰብ እንጂ የሚታይ መስቀል የሌለው የሚታየውንና ግዙፉን የተቀረጸውንም መስቀል ፍለጋ ንግሥት ዕሌኒ ለኮሰች እንደተባለ ዓይነት ደመራ ዓመት እየጠበቀ የሚለኩስ አይደለም መስቀሉንም በዓይነሕሊናው ወይም በመንፈሱ በኩል ተስሎ የሚያየው ስለሆነ አሁንም መስቀሉን ፍለጋ ተራራና ቋጥኝ አይቧጥጥም እንደ ንግሥት ዕሌኒም የሚያስቆፍረውም ሆነ የሚቆፍረው ጉድጓድ የለውም እኛ ክርስቲያኖች በመንፈሳችን የምንመለከተው በአጠቃላይ የሚታይን ሳይሆን የሚታሰብን መስቀል ነውና የጠፋብን ደመራ ለኩሰን እና አስለኩሰን በዓልም አድርገን እንደገናም ቁፋሮ ቆፍረንና አስቆፍረን የምንፈልገው ተፈልጎም ተገኘ የምንለው እና ያገኘነው መስቀል ለእኛ የለንም ስለዚህ እኛ ክርስቲያኖች ማለትም ዳግም ከእግዚአብሔር የተወለድን አማኞች ንግሥት ዕሌኒ ካደረገችው ደመራና መስቀሉን የማግኘት ቁፋሮ ዛሬም ድረስ ፍለጋዋን ተከትለው ከሚደምሩ ችቦም ከሚለኩሱ ሰዎች በብዙ የተለየን ነጻም የወጣን ሕዝቦች ነን ስለዚህ የመስቀል ደመራው አልተለኮሰም ብለን ቅር አንሰኝም ተለኮሰም ብለን አንቦርቅም ለእኛ አንድ ጊዜ ስለኃጢአታችን ሞቶ የተቀበረና ችቦ ለኩሳችሁ ዓመት በመጣም ቊጥር ጠብቃችሁና ደመራም ደምራችሁ ፈልጉኝ ያላለ መፈለግና ቁፋሮም ሳያስፈልገው በሦስተኛው ቀን መቃብር ፈንቅሎ የተነሣው ኢየሱስ እኛን ስለማጽደቅ የተነሣ ስለሆነ አንዴ ለሰው ልጆች የሆነ የደህንነትና የዕረፍት ችቦ በኢየሱስ በኩል ተለኩሶልና ይህን ያደረገልን ጌታ ሁሉ በሁሉ የሆነልን ጌታ ነውና የምስጋናውንም ሆነ የስግደቱን ችቦ የምንለኩሰው ለእርሱ ብቻ ነው ታድያ ወገኖቼ አሁንም የትምህርተ ኅቡአት የጸሎት መጽሐፍ እንዳለው የማይታይ እና የሚታሰብ መስቀል ያለው ሰው እንዴት እንደገና ወደኋላ ተመልሶ የሚታይ ቅርጽም ያለው ግዙፍ መስቀል ፍለጋ በየዓመቱ ችቦ ይለኩሳል ወገኖቼ እኔ እንኩዋን የሚታይ መስቀል ፍለጋ በየዓመቱ ችቦ መለኮስ ይቅርና ንግሥት ዕሌኒ ይህንኑ ግዙፉን መስቀል ለመፈለግ ችቦ ለኮሰች የተባለውን እንደ ትምህርተ ኅቡአቱ ሃሳብ እንደመጽሐፍቅዱሳችን ቃልም ሳየው ምንም የታየኝም ሆነ የሚታየኝ ነገር የለም ለምን ስንል ያለንና ሊኖረንም የሚገባ መስቀል የሚታሰብ እንጂ የሚታይ አይደለምና ነው በግዕዙ ቃልም ለዚህ ነው አኮ ከመ ይትረአይ አላ ከመ ይሐለይ ውእቱ ዝንቱ መስቀል ሲል የትምህርተ ኅቡአት የጸሎት መጽሐፍ የነገረን ይህ መስቀል የሚታሰብ እንጂ የሚታይ አይደለም እያለን ነው ሌላው በቀላሉ ወደመጽሐፍቅዱሱ ሳንገባ በራሱ በኦርቶዶክሱ መጽሐፍ ዙርያ እንኳ ብንመለከት በትምህርተ ኅቡአቱ መጽሐፍ የተጠቀሰውን ይህ መስቀል የሚታሰብ እንጂ የሚታይ አይደለም የተባለውን ንግሥት ዕሌኒ በደመራዋ አማካኝነት ፍለጋ አድርጌ አገኘሁት ስትል በዓልን ከአደረገችለት መስቀል ጋር እንዴት ነው ልናስማማው የምንችለው ? ሁለቱም ሃሳቦች በኦርቶዶክስ መጽሐፍ ውስጥ ነው ያሉት ንግሥት ዕሌኒ በደመራው ጠቋሚነት ፈልጌ አገኘሁት ያለችው ግዙፉንና የሚታየውን ሰዎችም ቀርጸው ያበጃጁትን መስቀል ነው የትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍ ደግሞ አኮ ከመ ይትረአይ አላ ከመ ይትሐለይ ውእቱ ዝንቱ መስቀል ወደ አማርኛው ስተረጉመው ይህ መስቀል የሚታሰብ እንጂ የሚታይ አይደለም እያለን ነው ታድያ አሁንም የትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍ ለእኛ እንዳለን የሚታሰብ እንጂ የሚታይ መስቀል ለእኛ ከሌለን የሚታየውንና ግዙፉን ቅርጽ ያለውን የሰው እጅ የሰራውንና ያበጃጀውን የሚዳሰሰውንም መስቀል 1ኛ) ንግሥት ዕሌኒ ያን ያህል ድካም ደክማ ደመራ ለኩሳና አስለኩሳ ብዙ ዕጣን አጪሳ ከዚያም መልስ ለወራት ያክል ቁፋሮ ቆፍራና አስቆፍራ መፈለጓ ለምን ይሆን ? 2ኛ) ሌላው እሺ ፈለገች እና አገኘች እንበል የትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍ ግን የነገረን ለእኛ የሚታሰብ እንጂ የሚታይ መስቀል የለንም ነውና ንግሥት ዕሌኒ ፈልጋና አስፈልጋ አገኘሁት ያለችው መስቀል ጥቅሙ ምን ይሆን ? 3ኛ) የሚታሰብ እንጂ የሚታይ መስቀል ለእኛ እንደሌለን የትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍ እየነገረን ፣ የንግሥት ዕሌኒ ፍለጋና አገኘሁት የሚለውም ነገር ሳያንስ እስካሁን ሕዝባችን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ታሪክን እየደገመ ደመራ ደምሮ መስቀል መፈለጉ በበኩሌ ትክክል መስሎ አይታየኝም ትክክል ነው ብዬም አላምንም የትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍም ሆነ መጽሐፍቅዱሳችን እንደነገሩን ትክክል አይደለም ስለዚህ ልብ ያለው ያስተውል ነውና እነዚህን በጥያቄ መልክ የቀረቡትን ሁለቱን ሃሳቦች በተብራራው ሃሳብ መሠረት አስተያይተን በመጽሐፍቅዱሳችን መመዘኛም መሠረት ወደ ትክክለኛው ሃሳብ ልንመጣና እውነተኛውን ትክክለኛውንም ሃሳብ ልንይዝ ይገባል ጌታ እግዚአብሔር የምናነበውንም ቃል ይባርክልን ከክፍል አንድ እስከ ክፍል አራት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ትምህርት ጨርሰናል አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው አሜን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን የJoshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment