Friday, April 15, 2016

ሐዋርያት በሰበሰቡዋት በአንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን


ይህን የሚመስል አቋዋም ይዘው ለተነሱ ሰዎች የሚሆን  መጽሐፍቅዱሳዊና መንፈሳዊ ምላሽ



ቤተክርስቲያን ዛሬ ላይ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ እንደ ቃሉ የሆነ ተሃድሶ ያስፈልጋታል

image




ቤተክርስቲያን ዛሬ ላይ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ እንደ ቃሉ የሆነ ተሃድሶ ያስፈልጋታል


ሐዋርያት በሰበሰቡዋት በአንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን

ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት

ምንጭ ጸሎተ ሃይማኖት

የትምህርት ርዕስ

ስለ ቤተክርስቲያን አመሠራረት የጥንትዋ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ያላት መጽሐፍቅዱሳዊ ትምህርትና የእምነት አቁዋም

የጥንትዋ ኦርቶዶክሳዊትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን የቤተክርስቲያንን አመሠራረት አስመልክቶ ያላት የእምነት አቁዋም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ የተመሠረተ ነው ለምን ስንል ሐዋርያት የሰበሰቡዋት ቤተክርስቲያን የተገኘችው በርደተ መንፈስቅዱስ ማለትም በመንፈስቅዱስ መውረድ ጊዜ  ጴጥሮስ በመንፈስቅዱስ ተሞልቶ እንግዲህ ይህ እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ ብሎ ሲናገር ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት ምንተ ንግበር አኃዊነ አሉዋቸው ይለናል ወደ አማርኛው ስተረጉመው ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ ? አሉዋቸው ማለትን የሚያመለክት ነው ወይቤሎሙ ጴጥሮስ ነስሑ ወተጠመቁ ኩልክሙ በስሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ወይትኀደግ ለክሙ ኃጢአትክሙ ወትነሥኡ ጸጋሁ ለመንፈስቅዱስ ይህንንም ቃል ወደ አማርኛ ስተረጉመው ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ አላቸው አያይዞም የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና፦ ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር ይለናል የሐዋርያት ሥራ 2 38 _ 42  ይመልከቱ ከዚህ እውነት የተነሳ ነው እንግዲህ ጥንታዊት ኦርቶዶክሳዊትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት  ስትል የተናገረችው ወደ አማርኛው ስተረጉመው በሁሉም ዘንድ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቡዋት በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን ማለትን የሚያመለክት  ነው ስለዚህ በዚያን ጊዜ ሐዋርያት የሰበሰቡዋት ቤተክርስቲያን ቃሉን የተቀበሉ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው የዳኑ የተጠመቁና ወደ ጌታ የተጨመሩ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ የነበሩትን ነው ታድያ እነዚህ ሐዋርያት ብዙዎች እንደሚያስቡት ጣራና ግድግዳው ያማረ ሆኖ በተሸለመ ሁኔታ የተሠራ ፤ ጉልላቱ ያጌጠ ትልቅ ካቴድራልን ቤተክርስቲያን ማለት ይህ ነው ሲሉ የሰበሰቡ አይደሉም ቤተክርስቲያን ማለት አምነው የዳኑ የቅዱሳን ስብስብ ወይንም ማኅበረ ምዕመናን ማለት እንጂ ጣርያና ግድግዳው ያማረ የተሸለመው ቤት ሕንጻው ወይንም ካቴድራሉ አይደለም ክርስቶስ ኢየሱስም የሞተው በልዩ ልዩ ዓይነት ሞዴል ተሠርቶ እና ተሸልሞ ጉልላት ገብቶለት ላሸበረቀው ቤት አይደለም እርሱ የሞተው የኃጢአት እስረኛ ሆኖ በዲያብሎስ ግዛት ሥር ለወደቀው ለሰው ልጅ ነው  ከዚህም ባሻገር ይህቺው ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሐዋርያት በሰበሰቡዋት አንዲት ቤተክርስቲያን ለማመንዋ ብጹእ አቡነ ጎርጎርዮስ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ የተናገሩትን በዋቢነት መጥቀስ እችላለሁ እርሱም ምንድነው ስንል ሐዋርያት መንፈስቅዱስን በተቀበሉ ጊዜ

1ኛ) ከብልየት (ከእርጅ) መታደሳቸው በአዕምሮ መጎልመሳቸው

2ኛ) ፍሩሐን የነበሩ ጥቡአን ሆነው ፈርተው የከዱትንና እየተንቀጠቀጡ ጥለውት የሸሹትን ክርስቶስን ለመስበክና መስቀሉንም ለመሸከም የማያወላውሉ ሆነው መገኘታቸው

3ኛ) ትንሣኤውንም ለመመስከር በየአደባባዩ መርዋራጣቸው እና ይህንኑ ጌታ መስበካቸው

4ኛ ) በዚሁም ምክንያት እነ ዮሐንስ አፈወርቅ ሐዋርያት መንፈስቅዱስን የተቀበሉበትን ዕለት የቤተክርስቲያን የልደት ቀን ብለዋታል ሲሉ ጽፈዋል

ብጹእነታቸው አሁንም  በዚህ ሳያበቁ አያይዘውም ቤተክርስቲያን  በክርስቶስ ደም የተመሠረተች ነች ብለዋል ታድያ መጽሐፍቅዱሳችን ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር

1ኛ) ቤተክርስቲያን በሐዋርያትና በነቢያት  መሠረት ላይ የታነጸች ሆና የማዕዘኑ ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ቢሆንም የቤተክርስቲያን መሥራች ግን ጌታችን ኢየሱስ ነው ኤፌሶን 2 ፥ 20 _ 22 ፤ የማቴዎስ ወንጌል 16 ፥ 13 _ 20

2ኛ) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም ያለው በመሆኑ ጌታችን ኢየሱስ አሁኑም በቤተክርስቲያን ጉዳይ የባለቤትነት መብት ይዞ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ ያለ  ነውና  ቤተክርስቲያን የማንም ልትሆን ስለማትችል የገሃነም ደጆች የማይችሉአት ሆና በምድር ላይ ያለች የክርስቶስና የክርስቶስ ብቻ ናት የማቴዎስ ወንጌል 16 ፥ 18


3ኛ) ከዚህም ሌላ በሐዋርያት ሥራ 20 ፥ 28 ላይ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ  ሲል በመንፈስቅዱስ የተሾሙ ጳጳሳት ሊጠብቁት የሚገባው በደሙ የተዋጀች ቤተክርስቲያን የተባለችው ጣራና ጉልላትዋ ያማረውን ሕንጻ ቤተክርስቲያንን አይደለም እነዚህ ጳጳሳት እንዲጠብቁ የታዘዙት መንጋውን ነው ሕንጻ ቤተክርስቲያንንማ የሚጠብቁ የተቀጠሩ ዘበኞች አሉ ከሌሉ ደግሞ ኖረው ወይም ተገኝተው እንዲጠብቁ  አቅም በፈቀደ መጠን ለመቅጠር መሞከር መልካም ነው  በደሙ የዋጃት ቤተክርስቲያን የተባለው ግን መንጋው ነው ለዚህም ነው ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ የተባሉት ስለዚህ ቤተክርስቲያን ማለት ጣራውና ግድግዳው ወይንም የመሰብሰብያ አዳራሹ ሳይሆን ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተዋጁ የቅዱሳን ስብስብ ፣ ማኅበረ ምዕመናን ወይንም መንጋው ማለት ነው ታድያ ክርስቶስ የሞተው ለሕንጻና ለግድግዳ ወይንም ለጉልላቱ ሳይሆን   የእግዚአብሔር መንጋ  ተብሎ ለተጠራው ፣ ወደፊትም የራሱ መንጋ ሊያደርገው ለወደደው ለሕዝቡ ነው   ከዚህም ሌላ ራሱን ያልጠበቀ ጳጳስ ሌሎችን መጠበቅ አይችልምና መንጋውን የሚጠብቅ ጳጳስ ወይንም አገልጋይ ደግሞ መንጋውን ሲጠብቅ ራሱን ከመጠበቅ መጀመር እንዳለበት የክፍሉ ሃሳብ ያመለክተናል እንደገናም ክርስትና ሌሎችን ሳይሆን በቅድሚያ ራስን ከማዳን የሚጀምር ስለሆነ ለራሳችሁና ለመንጋው ተጠንቀቁ   የሚል ቃል ተጻፈልን



4ኛ) የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መሠረታዊ ዓላማ የዘለዓለም መንግሥቱን ለሕዝቡ መስጠት ነው ስለዚህም በሉቃስ ወንጌል 12 ፥ 32 ላይ አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ አለን  ስለዚህም ነው እንግዲህ  በሐዋርያት ሥራ 20 ፥ 28 ላይ  በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ  ሲል የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ የዘገበልን ሰው ይህንን እውነታ የነገረን መንግሥት የተሰጠውና ሊሰጠውም የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ የሆነለት ይህ ታናሽ መንጋ ደግሞ በተሰጠው እንደገናም በሚሰጠው መንግሥት ውስጥ ጸንቶ እስከመጨረሻው በመኖር የዚሁ መንግሥት ወራሽ ሆኖ ታሪኩ እንዲያበቃ ልንጠነቀቅለት ፣ ሊጠበቅ ይገባዋል




5ኛ) ቤተክርስቲያንን መሳለም በተመለከተ አሁንም በዘመናችን ሰዎች የተሳሳተ መረዳት ይዘው በሐዋርያት ሥራ 18 ፥ 22   የተጠቀሰውን ቃል መሠረት በማድረግ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቂሣርያ በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ ይለናልና በዓይናችን ለምንመለከተው ፣ ቅዱስ ብለንም ለምንጠራው ሕንጻ ቤተክርስቲያን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ሰላም ለኪ ቤተክርስቲያን ስንል ቤተክርስቲያንን መሳለም ወይንም ስግደት ለቤተክርስቲያን መስጠት አለብን ይላሉ ይህንን ሁኔታ በተመለከተ  ጳውሎስ ወደ ቂሣርያ በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ መስጠቱ የጉልላት መስቀል በአናቱ ላይ ሰቅሎ ላማረውና ላሸበረቀው ሕንጻ ቤተክርስቲያን በሃይማኖታዊ ባሕልና ሥርዓት ተይዞ  አንገቱን ደፋ ቀና በማድረግ ለካቴድራሉ ሰላምታ የሰጠ አይደለም ጳውሎስ  ሰላምታ የሰጠው ቤተክርስቲያን ተብለው ለተጠሩና በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው ለዳኑ ቅዱሳን  ማኅበረ ምዕመናን ነው ቤተክርስቲያን እነርሱ ናቸውና ይህንን በተመለከተ ሃሳቡን  ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እና ለማብራራት  ከሌሎች የመጽሐፍቅዱስ  ማስረጃዎች  ጋራ ተያይዘው የቀረቡ ልዩ ልዩ የመጽሐፍቅዱስ ክፍሎች ስላሉ በቪዲዮ የተለቀቀውን ትምህርት በመስማት እነዚህኑ ሃሳቦች እንድትመለከቱዋቸው ለማሳሰብ እወዳለሁ

እንደገናም እኚሁ አባት  አቡነ ጎርጎርዮስ አሁንም ቤተክርስቲያን በጰራቅሊጦስ ወይም በመንፈስቅዱስ መወለድ ሳታበቃ ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን የጀመረችው መንፈስቅዱስ ለሐዋርያት ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ነው ብለዋል

ምንጭ የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ( ብጹእ አቡነ ጎርጎርዮስ ) 1978 ዓመተ ምሕረት አዲስ አበባ

በመሆኑም ከእነዚህ እውነቶች የተነሳ ይህቺ ጥንታዊትና ኦርቶዶክሳዊት ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያንም ሐዋርያት በሰበሰቡዋት በአንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን የሚል የእምነት መግለጫ ያላት በመሆንዋ በመንፈስቅዱስ የሆነ ሐዋርያዊ ተልእኮ ያላት ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ናት ታድያ አሁን ላይ ባለ ዘመናችንም ቤተክርስቲያን የምንለው በመንፈስቅዱስ አማካኝነት በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው የዳኑትን ማኅበረ ምዕመናንን ወይንም የቅዱሳን ኅብረትን እንጂ አሁንም ጉልላት ተሠርቶላቸው የኦርቶዶክስ ፣ የካቶሊክም ሆነ የፕሮቴስታንት ፣ የግሪክ ፣ የአርመን ፣ የሶርያ የግብጽንም ሆነ የመሣሠሉትን ልትሉት ትችላላችሁ እንደነዚህ ዓይነት አብያተ ክርስቲያናት ናቸው ተብለው  የተሰየሙትን ፣ የተሸለሙና ያማሩ በዘመናዊ መልክ የተሠሩ ቤቶችንና የካቴድራል ሕንጻዎችን አይደለም እነዚህ ሕንጻዎችና ካቴድራሎች ምንም እንኩዋ ቤተክርስቲያን የሚል ስያሜ ያገኙና ሰዎችም የሚሉዋቸው ቢሆኑም ትክክለኛ ትርጉማቸውን ስናይ ግን የመሰብሰብያ አዳራሾችና የማምለክያ ጣብያዎች ናቸው ከዚህ የተነሳ እኛም ለነዚህ ካቴድራሎች የመሰብሰብያ ጣብያዎችና አዳራሾች  ከዚህ በሁዋላ ቅዱሳን ቦታዎችና  ጫማ ዎች ተወልቀው ስግደት የሚቀርብላቸው  የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያኖች ናቸው ስንል ወደ ሕንጻዎቹ ውስጥ ልንገባ ጫማችንን አውልቀን እንደገናም ወደ ሕንጻው ውስጥ መግባት ባልቻልንበት ጊዜና ባልተመቸን ሰዓት ደግሞ እንሳለም ስንል በአጠገቡ ባለፍንና ባገደምን ቁጥር አንገታችንን ወደላይ ወደታች እየወዘወዝን  የምንሰጠው ስግደት፣ መሳለምም ሆነ አምልኮ የሚባል ነገር የለም ዮሐንስ ወንጌል 4 19 _ 24

የትምህርቱ ሃሳብ እንግዲህ በአጭሩ ይህን የመስላል ጌታ እግዚአብሔር በዚህ ትምህርት ሁላችንንም ይባርከን አሜን

Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ





No comments:

Post a Comment