Wednesday, July 1, 2015

የጌታ እራት ክፍል ሦስት

የጌታ እራት


ክፍል ሦስት


በዚህ ክፍለ ትምህርት የጌታን እራት የምንጠቀመው በ1ኛ ቆሮንቶስ 11 20 በተጻፈው ቃል መሠረት ሲሆን የጌታን እራት በምንካፈልበት ጊዜ ዓላማው ከጌታ ኃይልንና ጥንካሬን መቀበላችንን እንድናውቅ የሚያስችለን ነው  እንደገናም ራሳችን ለጌታ የተሰጠን እንድንሆን ለማድረግ ነው ይህንን የጌታን እራት ስንወስድ ቅዱስ ቁርባን ወይንም በእንግሊዘኛው Holy Communion (ሆሊኮሚኑየን )መሆኑን እንረዳለን ከዚህም ሌላ መጽሐፍቅዱሳችን እንደሚያስተምረን ከግሪኩ ቃል የተነሳ ምስጋናም የምንሰጥበት ነው በሉቃስ ወንጌል 22 17 _ 19 ላይ ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት እላችኋለሁና፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም አለ እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ ይለናል እንደገናም በ1ኛ ቆሮንቶስ 11 24 _ 25 ላይ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ ይለናል ስለዚህ ቅዱሳን ወገኖች ሳይመሰገን የተሰጠን የጌታ እራት የለምና  እኛም አጉረምርመን ፣ አምተን ፣ ተጋጭተንና ሌላም ሌላም ነገር ሆነን ሳይሆን  አመስግነን ሊሆን ይገባል የጌታን እራት መውሰድ ያለብን ጌታ እግዚአብሔር በምስጋና መንፈስ ይሙላን ወገኖቼ የኅብስቱ ወይንም የእንጀራው መቆረስ አገላለጽና ሁኔታ አደራረግም አለው  በሐዋርያት ሥራ 2 42 46 ላይ የተጻፈውን ስንመለከት በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር ይለናል እንደገናም በሐዋርያት ሥራ 20 7 11 ላይ ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፥ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ በማለት ይነግረናል ከእነዚህ የመጽሐፍቅዱስ ክፍሎች እንደምንረዳው እንግዲህ በዚያን ዘመን በጌታ ያመኑ ቅዱሳን እንጀራውን ወደ መቊረስ ሕይወት የመጡት እንዲሁ ዝም ብለውና መጥተው ተንደርድረው አይደለም እነዚህ ቅዱሳን በመጀመርያ ቃሉን የተቀበሉና የተጠመቁ ወደ ጌታም የተጨመሩ ናቸው የሐዋርያት ሥራ 2 41 ይህም ሆኖ እንኳን አሁንም ወደ ጌታ እራት በመምጣት በቀጥታ የጌታን እራት የተካፈሉ አይደሉም ወደ ጌታ እራት ሊመጡ የሐዋርያት ትምህርት አስፈልጓቸዋል ይህ የጌታ እራት ደግሞ ወደ ኅብረት መምጣትና በኅብረት ውስጥ መሆንን  የሚጠይቅ ነው  ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ ወደ እንጀራ መቁረስና በየጸሎቱም ወደሚተጉበት ሕይወት የመጡት ዛሬ ግን በዘመናችን የት እንዳሉና ምን እያደረጉ እንዳሉ የማናውቃቸው ሰዎች ዛሬ እና ድንገተኛ  በሆነ  ወደ ጌታ ቤት የመምጣት ማንነታቸው በኮንፍረንስ በሠርግና በመሣሠሉት በዓላት ምክንያትም ሊሆን ይችላል ወይንም በጓደኛ ምክንያት ተጋብዘው መጥተው እንደሆነ አላውቅም በጌታ ቤት ውስጥ የጌታ እራት ስለተሰጠ ብቻ ያለ ምንም ፍርሃትና ይሉኝታ ፣ ጥንቃቄም ሳይታከልበት ፣ ከልካይና ሃይ የሚላቸውም ሳይኖር እንዲያው በደፈናው ብድግ ብለው የጌታን እራት ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ጊዜ  በተደጋጋሚ ሲወስዱ አይቻለሁ  ታድያ ይህ የእነዚህ የጌታን እራት የወሰዱ ሰዎች ሁኔታ የእኔ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ከቀረ ሰንበትበት ብሎአል  በዚህ ጉዳይ ላይ እንግዲህ  ይህንን የጌታን እራት በድንገትና በዛሬ ማንነታቸው መጥተው የወሰዱትን ሰዎች በዚህ በአሁኑ ሰዓት ምንም ነገር ልላቸው ባልፈልግም በቤተክርስቲያን  በኃላፊነት የተቀመጡ ሰዎች ግን ይሄ ሁሉ ዓይነት የዕቃ ዕቃ ጫወታ ሲካሄድ ዓይናቸው እያየ ዝም ማለታቸው እጅግ በጣም አስደንቆኛል  አሳዝኖኛል ደግሞም ጥያቄም ሆኖብኛል የቤተክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች  ሃላፊነት መባ ለመሰብሰብና ማን መጣ ? ማን ቀረ ? ማን አስራቱን ሰጠ ? ማን አልሰጠም ? ለማለት ብቻ ከሆነ ምን ዋጋ አለው ከዚህ ሁሉ ኃላፊነቱን  ብናወርደውና ቢቀርብን አይሻልምን ? አለበለዚያም እኛ ካልቻልን ለሚችሉና ለሚሰሩ ሰዎች ቃሉንም ለሚያስጠብቁ ስፍራውን መስጠቱ መልካም ነው የጌታን እራት ድንገት በመጣ ማንነታቸው ሊወስዱ የተነሱ ሰዎች ሲገኙ ቃሉ የገባቸውና ቃሉን ማስጠበቅ የሚፈልጉ ሰዎች የቤተክርስቲያንም መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ በምንግዴለሽነት ወይንም በይሉኝታ ዝም አይሏቸውም ጌታን የት እንደተቀበሉ ? የት እንደተጠመቁ ?ኅብረታቸው ከነማን ጋር እና የት እንደሆነ ? አሁን ሊቀበሉት ስላለው የጌታ እራት ያላቸው መረዳት ምን እንደሆነ ? ጊዜ ሰጥተው ቀስ ብለው ይጠይቋቸዋል ይህን ሳያጣሩ እነዚህን ድንገተኛ የጌታ እራት ተመጋቢ ክርስቲያኖችን ወደ ጌታ እራት አያቀርቧቸውም ይህን እንደሚገባ አጣርተው እንደ እግዚአብሔር ቃል መመለስ እስኪችሉ ድረስ ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ የቀረውን ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነጝጋለሁ ይለናልና ቃሉ 1 ቆሮንቶስ 11 34  ይህንኑ እራት በቤታቸው እንዲበሉ ያደርጓቸዋል ይህ ዓይነት እርምጃ ደግሞ በቤቱ  በአግባቡ እየኖረ ላለ ክርስቲያኑም ሆነ ለድንገተኞቹ የሕይወት መትረፍና ጥንቃቄ ሲባል የሚወሰድ እርምጃ እንጂ ሰዎችን ከቤቱ ለማሸሽ የሚደረግ አጉለኛ ሰዋዊ ሥርዓት አይደለም ሰዎች የጌታን እራት ጥቅምም ሆነ ጉዳት የሚያውቁበት መንገዱ ክርስቲያኖች ስለሆኑ ብቻ በድንገት መጥተው አትለፈኝ ስልህ ዓይነት የጌታን እራት መውሰዳቸው አይደለም እንደገናም አምነው መጠመቃቸውና ወደ ጌታ ኅብረት መጨመራቸውም አይደለም በሐዋርያት ትምህርትና በሕብረት ውስጥ መሆናቸው ነው ይሔ የሐዋርያት ትምህርት የቃሉን እውቀት የሚሰጥ የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ስለሆነ ኅብረት የሚለው ነገር ምን እንደሆነ እና ኅብረት ደግሞ ከምንና ከማን ጋር እንደሆነ በግልጽ የሚያሳውቀን ነው ከዚህም ሌላ ከዚህ ከተማርነውና ከተረዳነው የቃሉ እውነት ተነስተን የኅብረቱ የአካሉ ብልት እንሆናለን ክርስቶስንም ራስ እናደርጋለን ቤተሰብነት ይሰማናል የምንቆርሰውም እንጀራ ይታወቀናል ዓይናችንም ይከፈታል የኤማሁስ መንገደኞች የሆነላቸው እንዲህ ነበር እንጀራውን አንስቶ ባርኮ ቆርሶ በሰጣቸው ጊዜ ዓይናቸው ተከፈተ አወቁትም እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ እርስ በርሳቸውም በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን ? ተባባሉ በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል እያሉ በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው እነርሱም በመንገድ የሆነውን እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንደ ታወቀላቸው ተረኩላቸው ይለናል የሉቃስ ወንጌል 24 13 _ 35 የእነዚህን የኤማሁስ መንገደኞችን ዓይን የከፈተውን እንጀራ የቆረሱት እራሳቸው የኤማሁስ መንገደኞች ብቻ አይደሉም ጌታም ነበር የቆረሰላቸው ታድያ ይህንን እንጀራ ጌታም አብሮአቸው ሆኖ ወደቤታቸውም ገብቶ ቆርሶ የሰጣቸው  በመሆኑ ዓይናቸው ተከፈተ የጌታንም እራት በተመለከተ እንግዲህ  እኛ የእርሱ አካል የሆንን ቅዱሳን የምንቆርሰው ብቻ ሳይሆን ጌታም የሚቆርስልን በመሆኑ የእነዚህ የኤማሁስ መንገደኞች ዓይን እንደተከፈተና ጌታም እንደታወቀላቸው ለእኛም እንዲሁ ይሆናል ነገር ግን ከዚህ ይልቅ ብዙ ጊዜ እንጀራውን የምንቆርሰው እኛው ለእኛ ለብቻችን በመሆኑ የሚከፈት ዓይንም ሆነ  የተከፈተ ዓይን የለንም ጌታም አይታወቅልንም  ሁሉም ነገር እንዳለ እንዲሁ ነው ያለው ይህ ማለት እንጀራ ከመቁረስ በፊት ባለው በኤማሁስ መንገደኞች ላይ ይታይ የነበረው ዓይነት የሕይወት ማሽቆልቆል  በእኛም ላይ ይታያል ማለቴ ነው እንጀራውንም ብንቆርሰው ጌታ የቆረሰልን ስለማይመስለን እንደገናም ቆረሰልን ብለን ብናስብ እንኳ የምናስብበት መንገዱ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል እንደሚገባ ያልተማርንና በትክክልም ያላወቅን በመሆኑ የቆረስነው እንጀራ ለእኛ ያው የለመድነው   የቤታችን እንጀራ ነው ለዚህም ነው የኤማሁስ መንገደኞች እንጀራውን ቆርሶ ሰጥቷቸው ይህንን እንጀራ በመብላት ዓይናቸው ተከፍቶ ጌታ ከታወቀላቸው በኋላ በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን ? የተባባሉት  በዚያው ቅጽበትም ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ለነዚህ ለኤማሁስ መንገደኞች የዓይን መከፈት አስተዋጽኦ ያደረገው ከጌታ ጋር በቤታቸው የቆረሱት እንጀራ ብቻ ሳይሆን በመንገዳቸው ላይ መሃል ገብቶ ጌታ የከፈተላቸው መጻሕፍትና በዚህ በተከፈተላቸው መጽሐፍ ምክንያትም የተቃጠለው  ልባቸውም ጭምር ነው ታድያ እነዚህን ሰዎች ጌታ በመንገዳቸውና በደከመው ጭውውታቸው መሃል ገብቶ መጻሕፍትን እየገለጠ ሳያውቁት እነርሱ በማዕዳችን ተቀመጥ ወዳሉት ነገር ግን ዓይናቸው ወደሚከፈትበት   ጌታም ወደሚታወቅላቸው ወደዚህ ወደ ክቡር እራት አድርሶአቸው ነበር ጌታም ይህንን ካደረገ እና እዚህ ደረጃ ላይ ካደረሳቸው በኋላ ነው ከእነርሱ የተሰወረው ከዚህ የቃሉ እውነታ እንደምንረዳው ዛሬም ወደዚህ ወደ ተባረከው እና ቅዱስ ወደሆነው ወደ ጌታ እራት ለመምጣትና እንጀራውንም ለመቁረስ ይህ ብቻ አይደለም የኤማሁስ መንገደኞች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል እያሉ በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው ይለናልና የግልን   የብቸኝነትን እና የተስፋ መቁረጥን ጉዞ ወደ ኋላ አስጥሎ ጌታ ወደሚፈልገው ኅብረት ለማምጣትና እና ለመቀላቀል  ከኅብረቱም ጋር በየጸሎቱ እየተጉ እንዲኖሩ ለማድረግ  በጌታና በሐዋርያት ትምህርት ብቻ ያልቀረ እስከ ክርስቶስ ምጽአት ድረስ እየተከፈተና እየተገለጠ የእኛንም ልብ እያቃጠለ ዓይናችን ወደሚከፈትበት ወደዚህ ወደ ጌታ እራት እና የጌታን እራት ሊወስዱም ወደ ተገባቸው ትክክለኛ የቅዱሳን ኅብረትና አገልግሎት የሚያመጣ ይህ የመጽሐፉ ቃል መከፈትና የእውቀቱ ቃል  ነው እንግዲህ ወደ ኅብረት መጥተን እንጀራውን ማለትም የጌታን እራት ከመውሰዳችን በፊት የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት የሚያስፈልገን ለዚህ ነው ላልተማረና የእግዚአብሔርን ቃል ላላጠና ሰው ኅብረትም ሆነ በኅብረት የሚቆረሰው የጌታ እራት  ምኑም አይደለም እንዲያው በዘልማድ ተንደርድሮ ከሚቀበለውም ውጪ ለሕይወቱ ትርጉም አይሰጠውም  ከዚህም ሌላ ሳያውቅና ሳይገባው ነውና ይህንን የጌታ እራት የወሰደው ለፍርድ ይበላል በማለት የእግዚአብሔር ቃል ያስጠነቅቀናል 1 ቆርንቶስ 11 26 _ 34 እግዚአብሔር ከዚህ ይጠብቀን ወገኖቼ በዚያን ዘመን የነበሩትን ቅዱሳንና የቃሉ አማኞችን በሐዋርያት ትምህርት በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየጸሎቱም እንዲተጉ ያደረጋቸው ይህ ሕይወት በየቀኑ በአንድ ልብ  በየቤታቸው ሳይቀር እንጀራቸውን ሲቆርሱና ሲመገቡ በደስታና በጥሩ ልብ እንዲመገቡ ያስቻላቸው ነበር  በዚህም ምክንያት ነው እንግዲህ ቃሉ እንደሚነግረን እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር የሚለን የሐዋርያት ሥራ 2 46 የመጽሐፉ መገለጥና የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ሲኖር እኛን አማኞችን በቤተክርስቲያን ውስጥ ባለ የጌታ ኅብረትና የጌታን እራት መውሰድ አያስቀረንም ይህ ዓይነቱ የተባረከ የአንድነት ሕይወትና የጌታን እንጀራ መቁረስ ቤታችን ድረስ ሄዶ ጓዳችን ድረስ በመግባት በየቀኑ በአንድ ልብ በጥሩ ልብና በደስታ የየግል እንጀራዎቻችንን ሳይቀር እንድንቆርስና እንድንመገብ የሚያስችለንና መረዳቱንም የሚሰጠን ይሆናል  ዛሬ ግን ይህን የመሰለ የእግዚአብሔር ቃል መረዳትና የዓይንም መከፈት ስለሌለ ከጓዳ ጀምሮ እስከ ቤተክርስቲያን ያለው ገበታችን የተነቀፈ ነው ግብዣውና መጠራራቱ አለ ብለን ብናስብ እንኳ ለይስሙላ ለታይታና እኔስ ለምን ይቅርብኝ ? ሲባል የሚደረግ  ስለሆነ አንድ ልብና ጥሩ ልብ የለበትም አይታይበትምም በዚያን ዘመን የነበሩ አማኞች አንድ ልብ ግን በየቀኑ የሆነ አንድ ልብ ስለሆነ ከእኛ የተለዩ ናቸው እንጀራቸውንም ሲቆርሱ በደስታና በጥሩ ልብ ነው   ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር የልብ ደስታና አንድነት ከሌለበት የእርስ በእርስ እና  የይስሙላ ግብዣዎቻችን በፊት ወደዚህ እውነት እና የመረዳት ልክ ይውሰደን ያሳድገን እላለሁኝ ጌታኢየሱስ ስምዖን ፈሪሳዊውን አንተ ውኃ እንኳ ለእግሬ አላቀረብክልኝም አልሳምከኝም ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም ያለው ምሳውንም ሆነ ከምሳ መልስ ያለውን ተገቢ መስተንግዶ  ፈልጎ ሳይሆን የስምዖንን ልብ  ፈልጎ ነው ስምኦን ፈሪሳዊው ኢየሱስን ምሳ ይጋብዘው እንጂ ከኢየሱስ ጋር በጥሩ ልብ አልነበረም የተወደዳችሁ ወገኖች ዛሬም በእኛ ዘመን ይህን ስናስበው ያለንበት ሁኔታና እያደረግነው ያለ ነገር በብዙ ከዚህ የራቀ አይደለም ጌታ እግዚአብሔር አስተሳሰባችንንና ድርጊቶቻችንን ይፈውስ ስለ ኅብረትና አንድነት ስናስብ  አንድነቱም ሆነ ኅብረቱ ያለው የምናቀርበው ምሳ ላይ ሳይሆን ልባችን ላይ መሆኑን በብዙ ልንረዳ ይገባል   ኅብረት ማለት ከቤተክርስቲያን  አምልኮ መልስ ስብና ቅልጥም የበዛበት ፣ ክትፎና ጥሬ ሥጋም የማይጠፋበት ጥሩ የሆነን ምሳ መገባበዝ ሳይሆን አቅም በረዳ መጠን በጥሩ ልብ የሆነን ቤት ያፈራውን ምሳ መገባበዝ ነው ጌታም ከእኛ የሚጠብቀው ጥሩ የሆነ የምሳ መገባበዛችንን ሳይሆን በጥሩ ልብ መገናኘታችንንና ኅብረት ማድረጋችንን ነው ጥሩ ልብ የምሳ መገባበዝን ብቻ ሳይሆን  የሕይወት ግንኙነትና አንድነትን መተሳሰብንም ጭምር የሚፈጥር ነው የምሳ ግብዣዎቻችን ግን በየቤታችንም ቢሆን እንደ አቅማችን ስላሉ እነዚህን ቁልፍ ነገሮች አያስገኙልንም ትምህርቴን ስጠቀልለው በየቤታችን ያለ በልብ አንድነት የሆነው ግብዣችን ያማረ የሚሆነው በቤተክርስቲያን ያለ ኅብረታችንና እንጀራውን መቁረሳችን ማለትም የጌታን እራት መካፈላችን በመጽሐፉ ቃል እውቀት የቀና ፣ የተስተካከለና የሰመረ ሲሆን ነውና ጌታ እግዚአብሔር ሕይወታችንን በዚሁ በቃሉ ያሳምረው በሚቀጥለው የክፍል አራት


ትምህርታችን እስከምንገናኝ ተባረከልኝ በማለት የምሰናበታችሁ

Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry

አገልጋይና ባለ ራዕይ      


ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ




No comments:

Post a Comment