የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ወይም የገና መልዕክት
ወይቤሎሙ መልአክ
ኢትፍርሁ እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዐቢየ ዜና ፍሥሐ
ዘይከውን ለክሙ ወለኲሉ ዓለም እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ
ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት
ወንጌል ዘሉቃስ ምዕራፍ ፪ ቊጥር ፲
ትርጉም ፦ መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና
የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ቊጥር 10
ይህ በ Joshua Breakthrough Renewal
Teaching and Preaching Ministry ሥር ተዘጋጅቶ የቀረበላችሁ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት መልዕክት ነው
የተወደዳችሁ ብፁአን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ፣ አበው ሊቃውንት መምሕራን ፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም አዕይንተ እግዚአብሔር ካህናት እና ዲያቆናት የሰንበት ትምህርት መምርያ ሃላፊዎች እና የሰንበት ተማሪዎች ፣ አስተማሪዎች ሕዝበ እግዚአብሔር ምዕመናን በሙሉ በቅድሚያ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ የከበረና ልባዊ ሰላምታዬን ሳቀርብ ይህ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ለሁላችንም የጤና ፣ የበረከት ፣ የደስታና የሰላም በዓል በያለንበት እንዲሆንልን እመኛለሁ በመቀጠልም ይህንን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት አስመልክቶ የተዘጋጀ ስብከተ ወንጌል ስላለኝ እርሱን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ ከላይ በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት መላኩም ይህንን የምሥራች መንጋቸውን በሌሊት በሜዳ ሲጠብቁ ላደሩ እረኞች ሲያበስራቸው ኢትፍርሁ እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዐቢየ ዜና ፍሥሐ ዘይከውን ለክሙ ወለኲሉ ዓለም እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት ወደ አማርኛው ስተረጉመው እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና አላቸው ወገኖቼ የሚፈሩ ሰዎች በሰዎች ሳይሆን ከሰማይ በመጡ የመላዕክቱ አንደበት አትፍሩ ሲባሉ በእርግጥም ይህ ታላቅ ደስታና የምሥራች ነው ታድያ ይህ ፍርሃት በእረኞች ዙርያ የታየና እየታየም ያለ ፍርሃት ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ሁሉ ፍርሃት ነው ይህ ፍርሃት ደግሞ የተፈጥሮ ፍርሃት ወይንም በተፈጥሮ የመጣ ማንኛውም ዓይነት ፍርሀት ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ እስኪወለድ ፣ ተወልዶም ለሰው ልጆች ኃጢአት እስኪሞትና የሰው ልጆችንም ስለማጽደቅ ከሞት እስኪነሳ ድረስ ያለ የባርነትና የሞት ፍርሃት ነው መጽሐፍቅዱስ ሲናገር በመጀመርያ በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል ወካዕበ ይቤ አንሰ
እትዌከል ቦቱ እስመ ደቂቅ ተሳተፉ በሥጋ ወደም ውእቱኒ ተሳተፈ በዝንቱ ወከመ ቢጾሙ ኮነ ሎሙ ከመ በሞቱ ይስዐሮ ለመልአከ ሞት ዘውእቱ ሰይጣን ወያዕርፎሙ ለኲሎሙ እለ በፍርሀተ ሞት ተኰነኑ በኲሉ መዋዕለ ሕይወቶሙ ወተቀ ንዩ ለግብርናት ወደ አማርኛው ስተረጉመው እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ በማለት ይናገራል ዕብራውያን 2 ፥ 14 እና 15 ታድያ ይህ የሞት ፍርሃት በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የተወገደው ነው ይህ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሊሞት ፣ ሰዎችንም ስለማጽደቅ ከሞት ሊነሣ ፣ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ዲያብሎስንም በሞት እንዲሽር ስለሞት ፍርሃትም በባርነት የታሰርነውን እኛን ነጻ ሊያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ የተካፈለ ነው እንግዲህ በሥጋና በደም የመካፈሉ አንደኛውና ዋነኛው ጉዳይ በበረት መወለዱ ፣ በመጠቅለያም መጠቅለሉና በግርግም ተኝቶ መገኘቱ ነው መጽሐፉም ሲነግረን ወወለደት ወልደ ዘበኲራ ወአሰረቶ መንኮብያቲሁ ወአስከበቶ ውስተ ጎል ወጠብለለቶ በአፅርቅት እስመ አልቦሙ መካን ውስተ ማኅደሮሙ ወደ አማርኛው ስተረጉመው የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው ማለትን የሚያመለክት ነው የሉቃስ ወንጌል 2 ፥ 7 ለዚህም ነው ካህናቱ በቅኔ ማህሌታቸው የሰንበት ተማሪዎችና መዘምራኑም በአውደ ምሕረታቸው በጐል ሰከበ በአፅርቅት ተጠብለለ ቤዛ ኲሉ ዓለም ዮም ተወልደ እያሉ በያሬዳዊ ጣዕመ ዜማ ማቀንቀናቸው ትርጉሙም በበረት ተኛ በጨርቅም ተጠቀለለ የዓለም መድኃኒት ዛሬ ተወለደ የሚለውን ትርጉም የሚሰጠን ነው ኢየሱስ በእንግዶች ማደርያ ሥፍራ አጥቶ በግርግም የተወለደውና በመጠቅለያም የተጠቀለለው በእርግጥም ሥፍራ አጥቶ አይደለም እርሱ ጌታና መድኃኒት ሆኖ
በሥጋ ከማርያም የተወለደ ቢሆንም ከአብ ጋር በቅድምና የነበረ ፣ ሰማይ ዙፋኑ ምድር የእግሩ መረገጫ የሆነ ፣ በኪሩቤል ሠረገላ ላይ የተቀመጠ ፣ ዓለማትን የአብ ባሕርያዊ ቃል ሆኖ የፈጠረ፣ የክብሩም መንጸባረቅና የባሕርዩም ምሣሌ ሆኖ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል የደገፈ ፣ ኃጢአታችንንም በራሱ ያነጻና የሚያነጻም ነው ዕብራውያን 1 ፥ 1 _ 3 መጻሕፍት የሚመሰክሩለት ይህንን እውነት ነው የእንግዶች ማደርያ አጥቶ በግርግም መጠቅለሉ ግን እኛ ከእግዚአብሔር ጋር በኃጢአት ምክንያት በመጣብን የልዩነት ዕዳ ማደርያ አጥተን ፣ ተጥለን የነበርነውን ከወደቅንበት ለማንሳትና ወደቀደመ ቦታችንም ለመመለስ ኢየሱስ ለእንግዶች የሚሆን ማደርያ አጥቶ በግርግም ተኛ ወገኖቼ ምሥጢሩ እንግዲህ ይህ ነው ኢየሱስ መጥቶ እስኪወለድልን ድረስ በሞት ፍርሀት ውስጥ በባርነት ተይዘንና ማደርያ አጥተን በእንዲህ ሁኔታ በዚሁ የሞት ፍርሃት ታስረን የተጣልን ነበርን ተወልዶ ያልቀረው ኢየሱስ ግን ጊዜው ደርሶ ስለእኛ ኃጢአት በመሞት በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ዲያብሎስንም በሞት በመሻር በሞት ፍርሃት የታሠርነውን እኛን ነጻ አወጣን ስለዚህ ዛሬ ትንሣኤና ሕይወት የሆነው ኢየሱስ በእኛ ውስጥ ስላለ በሞት ላይ ሥልጣን የነበረው ዲያብሎስ ሥልጣኑን አጥቶአል እንግዲህ ምስጢሩ ምንድነው ወገኖቼ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ዲያብሎስን ሥልጣኑን ሲሽረው ለእኔና ለእናንተ ትንሣኤና ሕይወት ሆኖን ነው በመሆኑም ይህን ትንሣኤና ሕይወት የሆነውን ጌታ በእርግጠኝነት በሕይወተ ሥጋ ሳለን አሁኑኑ ወደ ውስጣችን ፈቅደን እንዲህ ስንል ማስገባት አለብን ጌታዬ ሆይ አንተ ለእኔ ትንሣኤዬና ሕይወቴ ነህ ብሞት እንኳ አንተን በማመኔ ምክንያት ሕያው እንደምሆን አምናለሁና አንተን አዳኜን ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ ወደ ውስጠኛው ክፍል አስገባሃለሁ አንተኑ የሕይወቴ ጌታም አድርጌ እቀበልሃለሁ ብለን ፈቅደን ስንወስንና ኢየሱስን ወደ ውስጣችን ስናስገባ ኢየሱስ ለእኛ ትንሣኤና ሕይወት ይሆንልናል በዚያው ቅጽበትም የሞት ፍርሃት እስራት ከእኛ ይበጠሳል ሥልጣኑ የተሻረው ዲያብሎስም ከእግራችን ሥር ይወድቃል ይህ ይሆን ዘንድ ግን አሁኑኑ እያንዳንዳችን ለራሳችን ወስነን ይህንን ልናደርግ ይገባል ወገኖቼ ኢየሱስን ያመነ ሰው ዛሬ የማደርያም ሆነ የመኖርያ ሥፍራ የሚያጣ አይሆንም በግርግምም አይጣልም የኢየሱስ የሆነ ሰውና ኢየሱስንም የሕይወቱ ጌታና ንጉሥ ያደረገ ሰው ሁሉ ሀገሩ በሰማይ ነው የሚጠብቀውም ከላይ የሚመጣውን መድኃኒት ነው ፊልጵስዩስ 3 ፥ 20 እና 21 ይመልከቱ ለዚህ ነው እንግዲህ የእኛ ጌታ የናዝሬቱ ኢየሱስ ከተጣልንበት ከታችኛው ሥፍራ አንስቶ ሀገራችንን በሰማይ ያደረገው የእግዚአብሔር ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ ሲል የተናገረንና ይህንን አስደናቂ የሆነን የተስፋም ቃል የሰጠን ዮሐንስ ወንጌል 14 ፥ 3 መላዕክቱ መንጐቻቸውን ሲጠብቁ በሜዳ ላደሩ እረኞች እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ሲሉ የማብሠራቸው ሌላው ምስጢሩ ደግሞ መደኃኒት ሊሆን የተወለደው ኢየሱስ ብቸኛ የኃጢአት መድኃኒት ስለሆነ ነው ሞትንም ስናስብ ለሞትም እንዲሁ ብቸኛ የሞት መድኃኒት እርሱ ኢየሱስ ብቻ ነው ከእርሱ ውጪ ከኃጢአትም ሆነ ከሞት የሚያድን ሌላ መድኃኒት የለም ለዚህም ነው በዚያን ዘመን ሊወለድ ላለው ኢየሱስ ወትወልድ ወልደ ወትሰምዮ ስሞ ኢየሱስሃ እስመ ውእቱ ያድኅኖሙ ለሕዝቡ እምኃጢአቶሙ የተባለለት ወደ አማርኛው ስተረጉመው ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ ማለትን የሚያመለክት ነው የማቴዎስ ወንጌል 1 ፥ 21 ሞትንም በተመለከተ ብቸኛ የሞት መድኃኒት መሆኑን የምናይበት እውነት በግዕዙ ቃል አነ ውእቱ ትንሣኤ ወሕይወት ዘየአምን ብየ እመኒ ሞተ የሐዩ ወኲሉ ዘሕያው ወየአምን ብየ ኢይመውት ለዓለም ተአምኑኒ ዘንተ ወደ አማርኛው ስተረጉመው ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል
ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን ? የሚል ቃል የተጻፈልን በመሆኑ ነው ዮሐንስ ወንጌል 11 ፥
25 _ 27 ስለዚህ ኢየሱስ ብቸኛው የሞት መድኃኒት ስለሆነ በእርሱ ሕያዋን ሊሆኑ ለሚያምኑበት ሁሉ ብቸኛው ትንሣኤና ሕይወት እርሱ ነው የተወደዳችሁ ወገኖች የሰማነውን ይህንኑ ቃል ፣ ልናነብ የተዘጋጀነውንም ሁሉ ጌታ እግዚአብሔር በቃሉ ልባችንን ይጎብኘው ፣ ይለውጠው አባቶቼና ወንድሞቼ ወገኖቼ ምዕመናን በሙሉ አሁንም ይህ የልደት በዓል ለሁላችንም የበረከት ፣ የጤናና የሰላም ፣ የደስታ በዓል ይሁንልን በማለት የምሰናበታችሁ
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
No comments:
Post a Comment