Tuesday, February 2, 2016
የትምህርት ርዕስ ፦ የምንሳለመውም ሆነ የምናሳልመው መስቀል ለእኛ የለንም ( ምንጭ ትምህርተ ኅቡአት የትምህርት ርዕስ ፦ የምንሳለመውም ሆነ የምናሳልመው መስቀል ለእኛ የለንም ( ምንጭ ትምህርተ ኅቡአት ) አኮ ከመ ይትረአይ አላ ከመ ይትሐለይ ውእቱ ዝንቱ መስቀል ይህ መስቀል የሚታሰብ እንጂ የሚታይ አይደለም ( ምንጭ ትምህርተ ኅቡአት ) የተወደዳችሁ ሕዝበ እግዚአብሔር ምዕመናን አዕይንተ እግዚአብሔር ካህናትና ዲያቆናት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዲሁም አረጋውያን አባቶች እና እናቶች በሙሉ አምላካችን እግዚአብሔር ፈቅዶ ለዚህ ቀንና ሰዓት ስላደረሰን ለእርሱ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው አሜን ከዚህ በመቀጠል ከላይ በትምህርት አርዕስቴ ላይ እንደገለጽኩት ለእኛ የምንሳለመውም ሆነ የምናሳልመው መስቀል የለንም የሚል ሃሳብ ሰጥቼዋለሁና ለምን ይህንን አልክ ? ብትሉኝ ክቡር መስቀሉን የሚሳለሙትንም ሆነ የሚያሳልሙትን ወገኖች ለመቃወም ብዬ ሳይሆን ትምህርተ ኅቡአት የተሰኘው መጽሐፍ ላይ አኮ ከመ ይትረአይ አላ ከመ ይትሐለይ ውእቱ ዝንቱ መስቀል ወደ አማርኛው ስተረጉመው ይህ መስቀል የሚታሰብ እንጂ የሚታይ አይደለም የሚል ትርጉም የሚሰጠን ነውና በትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍ አነጋገር መሠረት የሚታሰብ እንጂ የሚታይ መስቀል ከሌለን የምንሳለመውም ሆነ የምናሳልመው መስቀል ለእኛ አይኖረንም እያልን በመሆናችን ዛሬ ላይ ተነስተን ይህንኑ የትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍን በመሻር የሚታሰብ እንጂ የሚታይ መስቀል ለእኛ የለንም እያለን ከየትኛው ጓሮአችን ቀጥፈንና ቆርጠን ነው መስቀል ስንል አበጅተን ወይም ቀርጸን ሰው ማሳለማችን ? እንደገናስ ከየትኛው አንጥረኛ ቤት ገዝተን ይሆን የብር የወርቅና የናስ መስቀል ነው ስንል ይህ የክርስቶስ መስቀል ምሳሌ ነው በማለት ማሳለማችን ? እኛስ ተሳላሚዎች ከየትኛው መጽሐፍ ማስረጃ አግኝተን ነው ቀን ከሌሊት ሳንል ይህንኑ መስቀል መሳማችን ፣ መሳለማችን ? በብዙዎች ሳይሆን በአንዳንድ ሰነፎችና ለጥቅም ያደሩ ካህናት እንዲሁም የከተሜ ባሕታውያን ሕይወት ዙርያም ስንመለከት እንደሰማነውና እንዳየነውም ከወርቅ ወይም ከብር ያሰሩትን መስቀል ነው ሲሉ ሽቶ ቀባብተው ባማሩ እና ነጫጭ በሆኑ ጨርቆችም ሸፍነው በተለየ ኪስ ውስጥ በማስቀመጥ ትንሽ ዳጎስ ላለ ገንዘብ ለሚሰጡ ባለጸጋና ኃብታም ሰዎች ሊቸሩም ለሚችሉ ሁሉ ይህንኑ በሽቶ ያወደ የወርቅ ወይም የብር መስቀል በማውጣት የሚያሳልሙ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር እየሆነ መጥቶአል ምንም ለሌለው ለደሃው ደግሞ በምንም ዓይነት ቅርጽና መልክ ትሰራ ብቻ ያቺኑ የእንጨት መስቀል እንደልማዳቸው ከተለመደው ኪሳቸው አውጥተው ያሳልማሉ ታድያ በዚህ ጉዳይ ላይ የዘመኗ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንም ይህንኑ አሳሳቢ ጉዳይ ተከታትላ የወሰደችው አንዳችም እርምጃ የለም ስለዚህም ጉዳይ እኛም ቤታችን ነውና እየሆነ ባለው አሳፋሪ ነገር ሁሉ ልባችን እጅግ አዝኗል ይሁን እንጂ እንጨትም ይሁን ብረት ናስ ብር ወይም የወርቅ መስቀል ማሳለም እንደገናም መሳለም እንደማይገባ የትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍ እየነገረንና ወገኖቻችንም ይህንን እያወቁ ይባስ ብለው በዚሁ በመስቀላቸው የብር የወርቅና የእንጨት መስቀል ሲሉ ሊያሳልሙ ሰው መለያየታቸው ምን ያህል አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን ልባቸው ሳያውቀው ቀርቶ ይሆንን ? እንደዚህ ዓይነቱን አስነዋሪ ድርጊት የምንፈጽም ካህናት እግዚአብሔር ያስበን ዓይኖቻችንንም በመጽሐፍቅዱስ የቃሉ እውነት ይክፈትልን ወደ መጽሐፍቅዱሱ ቃልም ሆነ ወደ ትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍ ስንመለስ በእርግጥም ለእኛ የሚታሰብ እንጂ የሚታይ መስቀል የለንም ስለዚህ የሌለንንና መጽሐፉም አዘጋጁ ያላለንን መስቀል የእንጨት የብረት የወርቅም በሉት የብር ወይም የናስ በእግዚአብሔር ቃልም ሆነ በአምላካችን በእግዚአብሔርና በዙፋኑ ፊት ስንመዝነው ተራ የሆነ የአንጥረኞች የእጅ ሞያተኞችም የሥራ ውጤት ስለሆነ የተሰራበትን የገንዘብ ፍጆታና የሥራ ውጤት ቅርጹን ውበቱን ጌጡን ብናደንቅም ይዛችሁ አሳልሙትም ሆነ ተሳለሙት የሚል የመጽሐፍ ቃል ስለሌለ ማሳለምም ሆነ መሳለም እንደ ትምህርተ ኅቡአት የመጽሐፍ ሐሳብ እና እንደ መጽሐፍቅዱሳችንም ቃል ፍጹም ስህተት ነውና ይህንን የማሳለሙንም ሆነ የመሳለሙን ተግባር ፈጥነን እንድንተወው እንድናቆመውም ለማሳሰብ እወዳለሁ በእርግጥም ከዚህ ነገር በቀላሉ ለመውጣትና ለመተውም በብዙ ሊከብደን ይችል ይሆናል ይሁን እንጂ ቢከብደንም መጽሐፉ ያልፈቀደልንን የምናደርግ በመሆናችን መተዉ አማራጭ የሌለው ነገር ነውና አሁኑኑ ዛሬ ነገ ሳንል መተው ይገባናል በዚሁም መስቀል በማሳለምና በመሳለም ጉዳይ ሰዎችንም መለያየት የለብንም ሰዎች ተሳለሙም አልተሳለሙ ሰዎች ናቸው እግዚአብሔር የሰውን ፍጥረት የሚያየው በአንድ ዓይን ነው እኛ ግን ለራሳችን ጥቅም ስንል ባመቻቸነው ነገር ሰዎችን መለያየት ራሱን የቻለ ትልቅ በደል ነው መጽሐፍቅዱሳችን በያዕቆብ መልዕክት 2 ፥ 1 _ 7 ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን ? ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን ? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን ? እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን ? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን ? የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን ? ነገር ግን መጽሐፍ፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል ይለናል ስለዚህ ልናሳልመውም ሆነ ልንሳለመው በማይገባ መጽሐፉም እንድንሳለምም ሆነ እንድናሳልም ባልፈቀደልን መስቀል ይባስ ብለን ሰዎችን በመለያየት የብር የወርቅ መስቀል በሽቶ የተርከፈከፈ ከሽቶ ነጻ የሆነ ስንል ለማሳለም መሞከራችን ራሱን የቻለ ሌላውና ትልቁ አስከፊውም በደላችን ስለሆነ ከዚህ ክፉ ጥፋት ፈጥነን መመለስ ይሁንልን እንደገናም ከትምህርተ ኅቡአት የኦርቶዶክስ መጽሐፍ ባሻገር መጽሐፍቅዱሳችን መስቀል በማሳለምም ሆነ በመሳለም ዙርያ የሚለን ነገር አለ የትምህርተ ኅቡአት መጽሐፍ የሚታይ መስቀል ለእኛ የለንም የሚታሰብ እንጂ ሲለን መጽሐፍቅዱሳችን ደግሞ በዘጸአት 20 ፥ 4 _ 6 ላይ በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና ይለናል እንደገናም በዘዳግም 4 ፥ 15 ላይ በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል ወዕቀቡ ጥቀ ነፍሰክሙ እስመ ኢርኢክሙ ርእየቶ በይእቲ ዕለት እንተ ባቲ ተናገረክሙ እግዚአብሔር በኮሬብ ላዕለ ደብር እማእከለ እሳት ከመ ኢትጌግዩ ወደ አማርኛው ስተረጉመው እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ ይለናል ስለዚህ የተቀረጸ ምስልን የማናቸውንም ምሳሌ ለእኛ አናደርግም መልክ ስላላየን እንዲህ ነውና ይህንን ይመስላል ስንል የምንስለውም ሆነ የምንቀርጸው ምስልም ሆነ መስቀል የለንም ይህንን እውነታ በሐዲስ ኪዳን መጽሐፍም ሄደን ስንመለከተው አሁንም በግዕዙ ቃል ወባሕቱ ትመጽእ ሰዓት ወይእዜ ይእቲ አመ እለ በርቱዕ በአማን ሰጋድያን ይሰግዱ ለአብ በመንፈስ ወበጽድቅ እስመ አብኒ ዘከመዝ የኀሥሥ እለ ይሰግዱ ሎቱ እስመ እግዚአብሔር መንፈስ ውእቱ ወእለሂ ይሰግዱ ሎቱ በመንፈስ ወበጽድቅ ሀለዎሙ ይስግዱ ሎቱ ወደ አማርኛው ስተረጉመው ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል ይለናል የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 4 ፥ 23 እና 24 ወገኖቼ ከመጽሐፉ ቃል እንደምንመለከተው ከእግዚአብሔር ውጪ የምንሰግድለትም ሆነ የምናመልከው ምንም ነገር የለም ለዚሁ ለእግዚአብሔር የምንሰግደውም በእውነትና በመንፈስ ነው ስለዚህ ቅርጽና ምስል ስዕልም ጭምር በአምልኮአችን ውስጥ ቦታ የላቸውም በዘዳግም 4 ፥ 15 መሠረትም መልክ ከቶ አላየንምና ለምንሰጠው አምልኮም ሆነ ለምናደርገው ነገር እጅግ ልንጠነቀቅ ይገባል ይሁን እንጂ እነዚህ ምስሎችም ሆነ ቅርጾች ምናልባትም በማስተማርያነት ይጠቅሙናል ካልን ደግሞ ያንንም በጥንቃቄና በማስተዋል ማድረግ ይኖርብናል ከዛ ውጪ ግን ቀርጸንና ስለን የምናመልከው እግዚአብሔርም ሆነ የምንሳለመውና የምናሳልመውም መስቀል ለእኛ የለንም ጌታ እግዚአብሔር በዚህ እውነት ይገናኘን የክፍል ሁለት ትምህርት ይቀጥላል ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን የJoshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ)
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment