Saturday, February 6, 2016

የትምህርት ርዕስ ፦ የምንሳለመውም ሆነ የምናሳልመው መስቀል ለእኛ የለንም ( ምንጭ ትምህርተ ኅቡአት ) ክፍል ሦስት


መስቀልን ስለ መሳለምም ሆነ ስለ ማሳለም  የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍቅዱስ ምን ይላል?  ይህንን ጠይቀው ያውቃሉ ?

Image result for kissing the cross from pristes ethiopian orthodox





የትምህርት ርዕስ   የምንሳለመውም ሆነ የምናሳልመው መስቀል ለእኛ የለንም ( ምንጭ ትምህርተ ኅቡአት )

ክፍል ሦስት



በዚህ የክፍል ሦስት ትምህርት የምንመለከተው መስቀልን ፍለጋ ንግሥት ዕሌኒ ደመራ የለኮሰችበትንና ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ መስከረም 16 በዋዜማው ወደ ማምሻሻው ላይ በሀገራችን በመላው ኢትዮጵያ ደመራ ይለኮሳል መስከረም 17 ቀን ደግሞ የመስቀል በዓል ይከበራል ይህ  እንግዲህ በሀገራችን የታወቀና ብሄራዊ የሆነ በዓል ነው ታሪኩን የሚናገሩ ሰዎችም እንደሚሉት በአጭሩ ንግሥት ዕሌኒ የተቀበረውን መስቀል ለማግኘት መስከረም 16 ቀን ደመራ አስደምራ መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ ያስጀመረችበት ቀን ሲሆን መስቀሉን ግን ያገኘችው መጋቢት 10 ቀን ነው ሲሉ መጋቢት 10 ንም መስቀሉ የተገኘበት ቀን ነው ብለው በታላቅ ድምቀት ያከብሩታል ታድያ በዚህን ዕለት የኦርቶዶክስ ካህናት እዚያው በደመራው የጸሎት ጊዜ የሚያዜሙት የጸሎት መዝሙር አለ እርሱም መስተብቊዕ ዘመስቀል ይባላል በግዕዙ የግሥ እርባታ ወይም አረባብ አስተብቊዐ አማለደ ማለት ሲሆን መስተብቊዕ ማለት ደግሞ ምልጃ ማለትን የሚያመለክት ነው በመሆኑም መስተብቊዕ ዘመስቀል ማለት የመስቀል ምልጃ ማለት ነው እንግዲህ በዚህ መስተብቊዕ ዘመስቀል ማለትም የመስቀል የምልጃ ጸሎት ላይ እንኳን አይደለም አምኖ ለመጸለይ በጆሮ ሰምቶ የሰሙትን እንኳ ለማመን እስኪያስቸግር ድረስ ይህ የሰማሁት በእርግጥም እንደዚህ ነውን ? ወይስ በእኔነቴ የሰማሁት አይደለም ? ብለን እራሳችንን ለራሳችን እስክንጠራጠር የሚያደርስ የጸሎት ቃል ከዚህ  የመስቀል የምልጃ ጸሎት (መስተብቊዕ ዘመስቀል ) እንሰማለን  ሃሳቡም እንዲህ የሚል ነው በመጀመርያ በግዕዙ ቃል አስቀምጥዋለሁ በእንተ ዝንቱ አዘዙ መምህራነ ቅዱስ ወንጌል አምሳለ ፈጣሪ ልዑል ንስግድ ለመስቀል ወለማርያም ድንግል ……………..ለእሉ ፪ቱ ፍጡራን ስብሐተ  ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን ይለናል ወደ አማርኛው ስተረጉመው የልዑል ፈጣሪ ምሳሌ ለሆኑት ለመስቀልና ለማርያም ቅዱስ የወንጌል መምህራን አዘዋልና እንስገድ የሚል ሲሆን ሁለተኛው ሃሳብ ደግሞ ለእነዚህ ለሁለቱ ፍጡራን ማለትም ለመስቀልና ለማርያም የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል ከዘላለም እስከዘላለም በክብራቸው ተመርጠዋልና የሚል ቃል ነው ይህንን ነው እንግዲህ በጽሁፌ ላይ ከላይ እንደገለጽኩላችሁ ይህን ጸሎት ከሚጸልዩት ጋር ተባብሮ በመጸለይ  ወይንም አሜንታን በመግለጽ መስማማታችንን የምናሳይበት ጉዳይ ሳይሆን ሰምቶ የሰሙትን እንኳን በእርግጠኝነት ሰምቼዋለሁ ? ብሎ ለማመን ሳይቀር  የሚያጠራር እንደሆነ የገለጽኩላችሁ ይህን ያልኩበት ምክንያት የጸሎት መጽሐፉ ካሰፈረው ሃሳብ ተነስቼ ነው እስቲ አስቡት ለመሆኑ የትኞቹ የቅዱሱ ወንጌል መምህራን ይሆኑ ? የልዑል ፈጣሪ ምሳሌ ለሆኑት ለመስቀልና ለማርያም ስገዱ ያሉን ? በእውነቱ እነዚህ መምህራን ይህንን ተናግረው ከሆነ እነዚህ የቅዱሱ ወንጌል መምህራን ሳይሆኑ ዘንዶውና እባቡ ጊንጡም የላካቸው የሐሰት መምሕራን ናቸው ለምን ? ስንል ለማርያምና ለመስቀል  እንስገድላቸው የሚል መጽሐፍቅዱሳችን ላይ የተጻፈ ነገር የለም እንደገናም የልዑል ፈጣሪ ምሳሌዎች ሊሆኑም በፍጹም አይችሉም እርሱ እግዚአብሔር ሰማይ ዙፋኑ ምድር የእግሩ መረገጫ ስለሆነ ምሳሌ የለውም የሐዋርያት ሥራ 7 47 _ 50 ኢሳይያስ 66 1 እና 2 1 ነገሥት 8 27 እንደገናም በዚሁ በትንቢተ ኢሳይያስ 46 5 ላይ  በማን ትመስሉኛላችሁ ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ ? ይለናል ሌላም ብዙ ጥቅሶችን መጥቀስ እንችላለን ይሁን እንጂ እነዚህ ጥቅሶች እራሳቸውን የቻሉ በቂና ብርቱ መረጃዎች ናቸው ስለዚህ ፈጣሪያችንን በምንምና በማንም እንዲሁም ከምንምና ከማንም ጋር አናስተካክለውም አናስተያየውም እንዲሁም አናመሳስለውም እርሱን የሚመስለውም ሆነ የሚስተካከለው ማንም የለም ቅድስት ማርያም የኢየሱስ እናትም እኔ እመስለዋለሁ እስተካከለዋለሁ አላለችንም እርስዋ ያላለችንን ማለት ደግሞ ማርያምንም ሐሰተኛ እንዳደረግናት ያስቆጥርብናልና ይህ ታድያ በእግዚአብሔር ዘንድ ትልቅ ነውረኝነትና  ኃጢአትም ነው ይልቁንም እርስዋ ያለችው አይደለም እግዚአብሔርን ወደ እርስዋ የተላከውን መልአክ እንኳን በግዕዙ ቃል እንደሚናገረው ወትቤሎ ማርያም ለመልአክ ነየ አመተ እግዚአብሔር ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ አለች ወደ አማርኛው ስተረጉመው  እነሆኝ የጌታ ባርያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ነው ያለችው የሉቃስ ወንጌል 1 38 እንደገና አሁንም በግዕዙ ቃል  ወትቤ ማርያም ተዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር ወትትኃሠይ መንፈስየ በአምላኪየ ወመድኃኒየ እስመ ርእየ ሕማማ ለአመቱ ወደ አማርኛው ስተረጉመው ማርያምም እንዲህ አለች ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና አለች የሉቃስ ወንጌል 1 47 እና 48 ስለዚህ የኢየሱስ እናት ማርያም ከልዑል ፈጣሪ ጋር ምሳሌ ልት የተዘጋጀች ራስዋንም ያዘጋጀች ሳት የጌታ ባርያ እነሆኝ ስትል   ጌታዋን ለማገልገል በትሕትና ራስዋን የሰጠች የጌታ ባርያ ነች ከአፍዋም የወጣው ቃል የወይን ጠጅ ላለቀባቸው አገልጋዮች የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ የሚል ነው የዮሐንስ ወንጌል 2 5 እርሱ የሚላቸውን ማድረግ የተሳናቸው ሰዎች ግን የሌለ ታሪክ ይዘው ማርያምን ከፈጣሪ ጋር ማርያምን ከልጇ ጋር ሊያጣሉ የፈጣሪ ምሳሌ ናትና እንስገድላት ይላሉ እርስዋ እኮ በዚህ ነገር ውስጥ የለችበትም ያለችውም ነገር የለም ደግሞም የባርያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና አለች እንጂ የፈጣሪ ምሳሌ ነኝና ስግደት ስጡኝ አላለችም ታድያ የቅዱስ ወንጌል መምህራን የተባሉ  ከየትኛው የመጽሐፍ ቃል አውጥተው  ነው ይህንን ትዕዛዝ ያዘዙት  ? ከኪሳቸው  ? ወይስ ከመጽሐፉ ቃል ? ከመጽሐፉ ቃል ቢሆን እስካሁን በቂ ማስረጃዎች ይቀርቡ ነበር ነገር ግን ከመጽሐፉ ቃል ያልሆነ ጉንጭ አልፋና እንዲሁ በይሆናል ከኪስ የተመዘዘ እውቀት አልባ ትእዛዝ ስለሆነ እኛም በመጣበት መንገድ አኳን ውድቅ አድርገነዋል  የዚህ ትምህርት ማጠቃለያ የክፍል አራት ትምህርት ይቀጥላል እስከዚያው ተባረኩ ሰላም ሁኑ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን


Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ

ቀሲስ አባ  ዮናስ ጌታነህ




No comments:

Post a Comment