Tuesday, November 3, 2015

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የመልዕክት ርዕስ ብቸኛ የመዳኛ መንገድ የሆነውን የኢየሱስን መንገድ እንምረጥ






በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
                     
የመልዕክት ርዕስ

ብቸኛ የመዳኛ መንገድ የሆነውን የኢየሱስን መንገድ እንምረጥ


  የተወደዳችሁ አበው መምሕራን የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ሊቃውንተ እግዚአብሔር ካህናት ዲያቆናት የሰንበት ተማሪዎችና አስተማሪዎች እንዲሁም ሕዝበ እግዚአብሔር ምዕመናን በሙሉ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቸርነቱና ምሕረቱ በዝቶልን እዚህ ላደረሰን ለእርሱ ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምሥጋና ይግባው አሜን
የዛሬው ትምህርታችን በመጽሐፈ ሰዓታት ላይ የተዘገበ ቃል ሲሆን ቃሉንም እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ ፍኖት ለኀበ አቡሁ አንቀጽ ዘመንገለ ወላዲሁ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚል ነው ወደ አማርኛው ስንተረጉመው ወደ አባቱ የሚያደርስ መንገድ ወደ ወላጅ አባቱም የሚያስገባ በር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ይለናል ( መጽሐፈ ሰዓታት ገጽ 122 )
ይህ የመጽሐፈ ሰዓታት መጽሐፍ ሁላችንም እንደምናውቀው የቤተክርስቲያኒቱ ካህናት መምሕራንና ሊቃውንት በቤተክርስቲያኒቱ በሚታወቁት የአጽዋማት ጊዜያቶች ሌሊት እየተነሱ የሚጸልዩበት የሚያዜሙትና ምሥጋናም የሚያቀርቡበት የጸሎት መጽሐፍ ነው ይህንንም የሚያደርሱት አጽዋማቱን ተከትለው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በአብዝሆተ ፍቅር በንቅሐ ልቡና ስለሆነ ጸሎቱ ብቻ ሳይሆን ጣዕመ ዜማው ሳይቀር ልብን የሚመስጥ እጅግ አስደሳችና ማራኪም ነው ነገር ግን የዚህን የመጽሐፈ ሰዓታት የውስጥ ሃሳብ በማስተዋል ሆነን ስንመለከተው ከቅዱስ መጽሐፋችን መጽሐፍቅዱስ ጋር ሊጋጩ የማይችሉ ሃሳቦችን አግኝተንበታል
አንደኛው ሃሳብ እንግዲህ በመግቢያ ትምህርታችን ላይ የጠቀስነው ዛሬ የምንመለከተው ሃሳብ ነው እርሱም እንዲህ የሚል ነው ፍኖት ለኀበ አቡሁ አንቀጽ ዘመንገለ ወላዲሁ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አማርኛው ስንተረጉመው ወደ አባቱ የሚያደርስ መንገድ ወደ ወላጅ አባቱም የሚያስገባ በር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚል ትርጉም ይዟል
የእናት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አንጋፋ መጽሐፍ ነው ተብሎ በሚታመነውና በሚጠራው የሃይማኖተ አበው መጽሐፍም ላይ ከመጽሐፈ ሰዓታት ጋር በተዛማጅነት የሚሄድ ተመሣሣይ ቃል እናገኛለን ቃሉም እንዲህ የሚል ነው
ጥንተ አንቀጽ መካነ ሕይወት ፈውስነ ሲሳይነ ስቴነ መኮንንነ ይላል ወደ አማርኛው ስንተረጉመው
በር አማጋ መሠማርያ የሕይወት መገኛ የሚያድን ምግባችን የሚፈርድልን መጠጣችን የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል ( ሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ምዕራፍ 3 ይመልከቱ )
እነዚህን ሃሳቦች እንግዲህ እንደ ቃሉ ስንመለከታቸው ብዙ ሃሳቦች ያሉባቸው ቢሆኑም ለዛሬ ግን መጽሐፈ ሰዓታት የነገረንን ወደ አባቱ የሚያደርስ መንገድ ወደ ወላጅ አባቱም የሚያስገባ በር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚለውንና በሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ምዕራፍ 3 ላይ የተጠቀሰውን በር አማጋ መሠማርያ የሚሉትን ሃሳቦች ከመጽሐፍቅዱስ ጋር በማገናኘት ትክክለኛውን እውነት ለማወቅና ለመያዝ በዚያም ላይ ለመሄድ እንዲያስችለን እንመለከታቸዋለን
መጽሐፍቅዱሳችንን አውጥተን ስናይ ደግሞ ከጠቀስናቸው የመጽሐፈ ሰዓታትና የሃይማኖተ አበው ቃሎች ጋር አንድ ዓይነት ሃሳቦች ይዘውና ተጽፈውልን ያሉ ቃሎች እናገኛለን
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ቊጥር 6 ላይ በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ወአልቦ ዘይመጽእ ኀበ አብ ዘእንበለ እንተ ኀቤየ
ወደ አማርኛው ስንተረጉመው ኢየሱስም እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ማለቱ ነው
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ቊጥር 1 ላይ ደግሞ አሁንም በግዕዙ ቃል አማን አማን እብለክሙ ዘኢቦአ እንተ አንቀጽ ውስተ ዐፀደ አባግዕ ወአርገ እንተ ካልእ ገጽ ሰራቂ ወጒሕልያ ውእቱ ይለናል ወደ አማርኛው ስንተረጉመው እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደ በሮች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው የሚል ትርጉም ይሰጠናል
በሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ምዕራፍ 3 ላይ ጥንተ አንቀጽ መካነ ሕይወት በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በር አማጋ መሠማርያ እንደሆነ ጠቅሶልናል ይህንንም በመጽሐፍቅዱሳችን የቃሉ መስታወት ስንመለከተው በግዕዙ ቃል እንዲህ ሲል ተጽፎ እናገኘዋለን
አነ ውእቱ አንቀጸ አባግዕ ዘበአማን ዘቦአ ብዕሲ እንተ ኀቤየ ይድኅን ወይበውእ ወይወጽእ ወይረክብ ምርዓየ ትርጉም እውነተኛ የበጎች በር እኔ ነኝ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል ይገባልም ይወጣልም መሠማርያም ያገኛል የሚል ነው የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ቊጥር 9
እንግዲህ የመጽሐፈ ሰዓታት መጽሐፍም ሆነ የሃይማኖተ አበው ዘእልመስጦአግያ ምዕራፍ 3 ክፍል እንደገናም በመጽሐፍቅዱሳችን በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ቊጥር 6 እና አሁንም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ቊጥር 1 ቊጥር 9 ላይ በተጻፉት ሃሳቦች መሠረት ኢየሱስ ወደ አባቱ የሚያደርስ መንገድ ወደ ወላጅ አባቱም የሚያስገባ በር ሆኖ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ካለ ከዚህም ሌላ እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው ካለን እንደገናም ኢየሱስ ወደ አባቱ የሚወስድ መንገድ እውነተኛ የበጎች በርና መግቢያ መውጫ መዳኛ መሠማርያ ከሆነ ስለምን ሌሎች መግቢያዎች ሌሎች መዳኛዎችና የመዳኛ መንገዶች እንዲሁም መሠማርያዎች አስፈለጉን ? ዛሬ ሕዝባችንን መውጫ መግቢያ መዳኛና የመዳኛ መንገድ ይህ ነው ስንል ያሠማራንበት ብዙ የሆኑ ወደ አብ መንግሥት ያስገቡሃል ስንል የከፈትንለት መንገዶች አሉ ኢየሱስ ግን አሁንም እኔ መንገድ እኔ እውነት እኔ ሕይወት እኔ የበጎች በር እኔ መውጫ እኔ መግቢያ እኔ መዳኛ እኔ መሠማርያ ያለ ብቻ ሳይሆን በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ብሎናል የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ቁጥር 6 ስለዚህ ወደ አብ መንግሥት ለመምጣትና የመንግሥቱም ባለቤት ለመሆን በኢየሱስ በኩል መምጣት ሁላችንንም ግድ ይላል አለበለዚያ አብ አያውቀንም የመንግሥቱም ባለቤት ሊያደርገን አይችልም ኢየሱስም በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ያለ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል ተብሎም የተነገረለት ጌታ በመሆኑ በእርሱ በኩል ካልመጣን አያውቀንም(ወደ ዕብራውያን የተጻፈ መልዕክት ምዕራፍ 7 ቊጥር 25 )
እንግዲህ ይህንን መልዕክትና ትምህርት የሰማን ያነበብንም የእግዚአብሔር ሕዝቦች አረጋውያን አባቶች እና እናቶች እህቶችና ወንድሞች ወጣቶች አዕይንተ እግዚአብሔር ካህናት ዲያቆናት መዘምራን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በሙሉ ብዙ ብዙ ደክመን በፍጻሜው ዘመናችን እንዳናዝን ዛሬውኑ ወደ አብ መንግሥት ወስዶ የሚያድነንን የሚያገባንን የሚያወጣንን መሠማርያም የሚሰጠንን ብቸኛ መዳኛና የመዳኛም መንገድ የሆነውን የኢየሱስን መንገድ እንምረጥ ኢየሱስ መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ብሎናል 
የሰማነውን በልቡናችን ያሳድርልን አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው አሜን
Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment