Saturday, November 28, 2015

መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሠራቂ ሌባ የማያገኘው መዝገባችን ክፍል አምስት


Image result for The rich young manImage result for the widow's offeringImage result for the widow's offeringመዝገብነ ዘኢይረክቦ ሠራቂ


ሌባ የማያገኘው መዝገባችን




ክፍል አምስት




መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ

ትርጉም ሌባ የማያገኘው ብል  ነቀዝ የማያበላሸው መዝገባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው


( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት )

መዝገብን ስናስብ መዝገብ መላ ሕይወትንና ማንነትን ሳይቀር መስጠት ይጠይቃል ይህንን ለማድረግ ግን የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ እንደነገረን በመጀመርያ ሌባ ያልሰረቀውን ብል ነቀዝ ያላበላሸውን እውነተኛውን መዝገባችን ኢየሱስን ለቤዛችን ለምሕረታችን እና ለደህንነታችን ማግኘት  

ዋናውና ተቀዳሚው ነገራችን ሊሆን ይገባል  ያለ እርሱ መዳን የለምና የሐዋርያት ሥራ 4 12 እንደገናም ያልዳነ ሰው መላ ሕይወቱንና ማንነቱን መስጠት አይችልም ይህንን ለማድረግ በመጀመርያ ለዛ ሰው መዳን የግድ ነው ለመዳን የፈለገ ሰውም ቢሆን እንኳን መዳን ከፈለገ በመጀመርያ ሕይወቱን ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ አሳልፎ መስጠት አለበት የቀራጮች አለቃ የነበረው ሀብታሙ ዘኬዎስ ሕይወቱን ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሲሰጥ ያደረገው ነገር ነበር በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 19 7 _ 10 እንደምንመለከተው ሁሉም አይተው፦ ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን፦ ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው ቀጣዩን ቃል በግዕዙ እናገረዋለሁ ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ ዮምሰ ሕይወት ኮነ ለሰብአ ዝንቱ ቤት እስመ አንተሂ ወልደ አብርሃም አንተ እስመ መጽአ ወልደ እጓለ እመሕያው ይኅሥሥ ወያድኅን ዘተሐጒለ ወደ አማርኛው ስተረጉመው ኢየሱስም፦ እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው በማለት የሚናገር ነው ሌሎችም እንደ ዘኬዎስ ለመዳን ሲሉ ሕይወታቸውን ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጡትን ሰዎች በብዙ ልናይ እንችላለን ለጊዜው ግን አሁን ዘኬዎስን እንደ አስረጂ ካቀረብን በቂ ነው የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ እንዳለው ብል ነቀዝ ያላበላሸውን ሌባም ያልሰረቀውን እውነተኛው መዝገባችን ኢየሱስን ማግኘት ለማንኛውም ሰው እጅግ በጣም አስፈላጊና ዋናም ነገር ነው መጽሐፍም ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ ስለዚህ ግን፥ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ፥ ምህረትን አገኘሁ ይለናል 1 ጢሞቴዎስ 1 15 እና 16 መዝገባችን ኢየሱስ ውስጥ ማንም ሊሰጠን የማይችለው ዘላለማዊ ምሕረት የመዳን ጸጋ የኃጢአት ሥርየትና ይቅርታ መታጠብ ከኃጢአትም መንጻት መቀደስ እና የመሣሠሉት ሁሉ አሉ ኢየሱስን ያላገኘ እና ኢየሱስም የሌለው ሰው እነዚህን ለደህንነታችን ሲባል በነጻ የተሰጡንን ነገሮች ማግኘት አይችልም እነዚህን ነገሮች ለማግኘት የግድ ሕይወቱን ለጌታችን ለኢየሱስ እንደነ ዘኬዎስና እንደሌሎችም መስጠት አለበት ቀጣዩ ነገር ያለው ግን ሕይወትን ለጌታ ለኢየሱስ ከሰጡ በኋላ ነው መላ ሕይወቱንና ማንነቱን ለአዳኙ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠ ሰው ገንዘቡን ጊዜውን እውቀቱን ልምዱን ያለውን ችሎታና ጌታ የሚጠብቅበትን ማንኛውንም ነገር ሁሉ ለዚህ ጌታ መልሶ መስጠት አያቅተውም መጽሐፍ ሲናገር አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል ? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው ? ይለናል 1 ቆሮንቶስ 4 7 ስለዚህ ከእኛነታችን ጀምሮ ያለውን ማንኛውንም ነገራችንን የተቀበልነው ከጌታ ነው የእኛ የምንለው እና ከእኛም የሆነ የምንመካበት አንድም ነገር የለም ሁሉ የጌታ እንደሆነ ካመንን ደግሞ ሁሉንም መልሰን ለዚሁ  ለጌታ ለመስጠት አንቸገርም ለዚህም ነው ንጉሥ ዳዊት በ1ኛ ዜና 29 12 _ 15 ላይ ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው አሁንም እንግዲህ፥ አምላካችን ሆይ፥ እንገዛልሃለን፥ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን  ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፥ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ ? ሕዝቤስ ማን ነው ? አባቶቻችንም ሁሉ እንደነበሩ እኛ በፊትህ ስደተኞችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ናት፥ አትጸናም በማለት የተናገረው ንጉሥ ዳዊት እንግዲህ በአጠቃላይ ሁሉ ያንተ ነው እያለን ነው አያይዞም ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ ? ሕዝቤስ ማን ነው ? በማለት ለአምላኩ ያቀረባቸው ስጦታዎች ሁሉ ከእጁ የተቀበላቸው እንጂ ከእርሱ አለመሆናቸውን በግልጽ አሳወቀን ስለዚህ ማንኛውንም ነገራችንን ሰጠን ብንል እንኳን ሁሉ የእርሱ በመሆኑ ሰጠን ብለን የምናወራው አንድም ነገር እንደሌለን ቃሉ ያስተምረናል ያቺ በማርቆስ ወንጌል የተጻፈላት መበለት ሁሉ ከትርፋቸው ሲጥሉ እርስዋ ግን ከጒድለቷ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ የጣለችው የኔ የሆነ አንዳች ነገር የለም ሁሉ የአንተ ነው ከማለት የተነሳ ነው ይህቺ መበለት በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ደሃ መበለት መሆንዋን መጽሐፉ ይነግረናል የማርቆስ ወንጌል 12   43 እና 44 ትዳርን መጣል ማለት ደግሞ መላ ሕይወትንና ማንነትን ሳይቀር መስጠት ነው ታድያ ይህቺ መበለት ከጒድለትዋ የነበራትን ሁሉ በመስጠት ትዳርዋን ሳይቀር የጣለችው ማንነትዋንና ሕይወትዋን ለጌታ በቅድሚያ ስለሰጠች ነው ነገር ግን በአንጻሩ ሕይወቱን ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያልሰጠ  የዘላለም ሕይወት ጥያቄ የነበረው አንድ ሰው  የዘላለም ሕይወት እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ ሲል ላነሳው ጥያቄ ኢየሱስ ተገቢውን መልስ ከሰጠው በኋላ ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና፦ አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው  ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ ይለናል  የማርቆስ ወንጌል 10 17 _ 22 ይህ ሰው ፊቱ ጠቊሮ እያዘነ የሄደበት ምክንያት ከጌታ ከኢየሱስ የሚያሳዝን ነገር ሰምቶ ሳይሆን ጌታ ካቀረበለት ጥያቄ ይልቅ የሰበሰበው ገንዘብ ስለበለጠበት ነው ሕይወቱን ለጌታ የሰጠ ግን ገንዘቡን ትዳሩንም ሳይቀር አምጥቶ በጌታ ፊት ይጥላል ጌታ ይህን ሰው ያለህን ሁሉ ሽጠህ ተከተለኝ ሲል ሕይወትህን ስጠኝ ማለቱ ነው ለዚህ ሰው ግን ሕይወቱ ያከማቸው ሀብትና ገንዘቡ ስለነበረ ይህ የጌታ ጥያቄ ገንዘቤንም ሆነ ንብረቴን የሚያሳጣኝ ጥያቄ ነው ከሚል አንጻር የገንዘብና የንብረት ጉዳይ አሳስቶት ፊቱን እያጠቆረና እያዘነ ሄደ ወገኖቼ ምስጢሩ ይሄ ነው የብዙ ሰዎች ሕይወት ዛሬም ጌታ ሳይሆን ገንዘብ ስለሆነ ሕይወትን ለጌታ የመስጠት ነገር በተነሳ ቊጥር ገንዘቤንና ንብረቴን የሚያሳጣኝ ጉዳይ ነው በሚል ሰበብ የፊት መጥቆር መክሰልና የማዘን ነገር ይታይባቸዋል ገንዘባቸው ለእነርሱ ገዢና አምላክ የሆነ ጌታ ነውና ይህ የጌታ ጥያቄ አይመቻቸውም ጌታ ያለህን ሽጠህ ተከተለኝ ሲል ገንዘብም ሆነ ንብረት አይኑርህ ሙልጭ ያልክም ደሃ ሆነህ ተከተለኝ ማለቱ አይደለም ከገንዘብህም ሆነ ከንብረትህ ይልቅ እኔ ስለምበልጥብህ መላውን ሕይወትህን ለእኔ ስጠኝ ማለቱ ነው ሕይወታችንን ለጌታ ለኢየሱስ ካለመስጠታችን የተነሳ ከጌታ ዘንድ ለቀረበልንና ለሚቀርብልን ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያቅተንና  ብዙ ነገሮች ፊታችንን ያጠቁሩታል ልባችንንም ያሳዝኑታል ከዚህ የተነሳ የጌታን ጥያቄ ወደኋላ ገሸሽ በማድረግ ፊታችንን ከጌታ እንድናዞር እንሆናለን ወደ ፊት በመሄድ ፈንታም ወደ ኋላ እናፈገፍጋለን ወገኖቼ ከማንምና ከምንም ይልቅ በቅድሚያ ጌታን እንድናስቀድም የሕይወታችንም ጌታ እንድናደርገው ጌታ ይርዳን ከዚያ በኋላ ከጌታ የተጠየቅነውንና ጌታም የሚጠብቅብንን ለማድረግ አንቸገርም የሰማነውንና የምናነበውንም ቃል እንድናስተውለው እግዚአብሔር ይርዳን



ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

የ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry

አገልጋይና ባለራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ





No comments:

Post a Comment