Saturday, November 7, 2015

የትምህርት ርዕስ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ክፍል አንድ

የትምህርት ርዕስ

ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ


                                                                 
ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን


ክፍል አንድ

 Stilling the Storm










በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን



የተወደዳችሁና የተከበራችሁ ብፁአን አባቶች አበው መምህራን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሕዝበ እግዚአብሔር ምዕመናን በሙሉ በቅድሚያ በፍቅሩና በርህራሄው የተቤዠን ለዘለዓለምም የወደደን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ ይክበር ይመስገን ከዚህ በመቀጠል ለዛሬ ወደ እናንተ ወደ ብፁአን አባቶች ወደ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና ወደ ቅዱሳን ምዕመናን የምትደርስ አጭር ትምህርት አዘል መልዕክት ትኖረኛለች እርስዋን በማስተዋል ሆናችሁ እንድትከታተሉኝ በፍጹም ትሕትና እና በተዋረደ ልብ ከታላቅ አክብሮት ጋር እጠይቃለሁ

ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ



ትርጉም ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ሌባ የማያገኘው ብል  ነቀዝ የማያበላሸው ሳጥናችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው



               ( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት )


የተወደዳችሁ አባቶቼና ወንድሞቼ ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወገኖቼ በሙሉ ትምህርቴ የሚያጠነጥነው በዚህ ሃሳብ ዙርያ ነው ባለፈው ትምህርታችንም ከዚሁ ከመጽሐፈ ሰዓታት በመጥቀስ ፍኖት ለኀበ አቡሁ አንቀጽ ዘመንገለ ወላዲሁ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ይለናልና ወደ አማርኛው ስተረጉመው ወደ አባቱ የሚያደርስ መንገድ ወደ ወላጅ አባቱም የሚያስገባ በር ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ከመጽሐፍቅዱሳችን ሃሳብ ጋር በተለይም ከዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 6 ጋር በማገናኘት ዘርዘር አድርገን በሰፊው ተማምረናል የጥንቷ ኦርቶዶክሳዊትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ትክክለኛ ወንጌል የሰበከች መሆኑን የምናውቅበት መንገዱ ይህ ነው ብዙ ከእግዚአብሔር ቃል ሃሳብ ጋር የማይጋጩ ከመጽሐፈ ሰዓታት ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክስ ካሳተመቻቸው ከተለያዩ የጸሎትና የምሥጋና መጻሕፍቶችዋ ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት መንገድና እውነት ሕይወት መሆኑን እንደገናም የሕይወት በር መውጫና መግቢያ መሠማርያ በደሙ ኃጢአታችንን ያጠበልን  የኃጢአትንም ሥርየት የሰጠን ሊቀ ካህናችን መሆኑንና የመሣሠሉትን ሁሉ የሚገልጹ ቃሎች ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በፍጹም ሊጋጩ የማይችሉ ሃሳቦችን አግኝተናል ታድያ መጽሐፍቅዱሳችን በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈልን ብቸኛ መጽሐፋችን ነውና እነዚህን ሃሳቦች ስላገኘን እነዚህን መጻሕፍት በእግዚአብሔር መንፈስ ከተጻፈው ከመጽሐፍቅዱሳችን ጋር በእኩል ዓይን አስተያይተን የመጽሐፍቅዱስ ቃል ነው ብለን ባንወስደውም ወይም ስድሳ ሰባተኛ የመጽሐፍቅዱስ እትም ነው ባንለውም  ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይቃረን ቃል በውስጡ የተጻፈ ሃሳብ እስካገኘን ድረስ እውነቶችን ፈልቅቆ በማውጣትና ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በማገናኘት አሁን ላይ ላለው ትውልዳችን የቃሉን እውነት በብዙ እንዲረዳ ቤተክርስቲያኒቱንም ወደ ጥንተ መሠረቷ ወደ እግዚአብሔር ቃል እውነት እንዲመልስ እና   የራዕዩም ባለቤት ሆኖ በራዕይና በዓላማ ጭምር እንዲያገለግል ያላሰለሰ ትግል በማድረግ ብርቱ የሆነ ጥረት እያሳየን በጸሎትም ጭምር እየተጋን  ከማስተማር ከመስበክ ከመቀስቀስና ከማነቃቃት ወደኋላ አንልም ማለትም በመጽሐፎቹ ውስጥ ያሉትን የእግዚአብሔርም ቃል የደገፋቸውን እውነታዎች ከቃሉ ጋር እያገናኘን  የቃሉን እውነት እናስተምረዋለን ከተጻፈለት የመጽሐፉ ቃል ጋራም በብዙ እናስተዋውቀዋለን መልዕክተኛም ለላከው ነውና እንደሚል ቃሉ የተልዕኮም ሰው እናደርገዋለን ቤተክርስቲያኒቱ በወንጌል መሠረት ላይ በቆመችባቸው ዘመናት ሁሉ ከተረትና ልብ ወለድ ድርሰቶች ይልቅ የእግዚአብሔርን ቃል ያመነች እና  አምናም ቃሉን ብቻ ያስተማረች የምሥራቹን ቃልም በትክክል የሰበከች መሆኑን እንደሚገባ እናውጅለታለን  እንደገናም  ብዙዎች ይህን እውነት ካለማወቃቸው የተነሣ ቤተክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊት አይበሏት ወይንም ሊሏት አይውደዱ እንጂ እኛ ግን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይጋጩ እውነቶች በውስጧ ያገኘን በመሆኑ ይህቺ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ለመሆንዋ በጽኑ እንመሠክራለን ፣ እንናገራለን ወደ ሃሳባችን ስንመለስ ከላይ በመግቢያ ጥቅሳችን ላይ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሠራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን ሃሳብ አንስተን ነበር ትርጉሙም እንዲህ የሚል ነው ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ሌባ የማያገኘው ብል ነቀዝ የማያበላሸው ሳጥናችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚል ሃሳብ ይዟል

      ዛሬ እንግዲህ ትኩረት አድርገን የምንመለከተው የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ እንደጠቆመን በግዕዙ ቃል ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ይላልና ሞገድ የማይቀርበው መርከባችን የሚል ትርጉም ስላለው ይህንን ሃሳብ ይዘን በማብራራት ይሆናል

          ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ
           ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ



          ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን
           ኢየሱስ ክርስቶስ ነው

   ይህ የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲል ይህንን ሃሳብ ያገኘው ከየት ነው ? ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥም ማዕበል ያልቀረበው መርከብ ነው ወይ ? የሚለውንና ሌሎችንም ሃሳቦች ይዘን በመጠይቅ መልክ ስናቀርብ መልሱን የምናገኘው ከዚሁ ከመጽሐፍቅዱሳችን ነው በመጽሐፍቅዱሳችን በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ቊጥር 23 እስከ 27 በተጻፈው ሃሳብ መሠረት ኢየሱስ በታንኳይቱ ማለት በመርከብዋ ውስጥ ተኝቶ ሳለ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ  መናወጥ እንደሆነና ደቀመዛሙርቱም ጌታ ሆይ አድነን ጠፋን እያሉ እንዳስነሱት ክፍሉ ይናገራል አያይዞም ኢየሱስ ከተነሳ በኋላ በቀጥታ ያደረገው ነገር ይህ ነው እናንተ እምነት የጎደላችሁ ስለምን ትፈራላችሁ ? አላቸው ከዚህ በኋላ ተነስቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሰጸ ታላቅ ጸጥታም ሆነ ይለንና ቀጣዩን ሃሳብ በግዕዙ እናገረዋለሁ ወአንከሩ ሰብእ ወይቤሉ መኑ እንጋ ውእቱ ዝንቱ ዘይትኤዘዙ ሎቱ በሕርኒ ወነፋሳትኒ ወደ አማርኛው ስተረጉመው ሰዎቹም ነፋሳትና ባሕር ስንኳ የሚታዘዙለት ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው ? እያሉ ተደነቁ የሚል የቃሉን ትርጉም ሲሰጠን እናገኘዋለን ለዚህ ነው እንግዲህ የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ከፍ ባለ የቃለ አጋኖ ድምጽ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለን ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ማለቱ ነው ታድያ ይህንን አባባል በጥቅሉ ስናየው ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲል ደራሲው ሊል የፈለገው እውነታውን ከማስተባበል ወይንም ከመካድ አኳያ ተነስቶ በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ነው ለማለት ፈልጎ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕበል ቢቀርበውም በአንድ ቃል ትዕዛዝ ገስጾ ከሚያቆመው በስተቀር  ማዕበሉ በፊቱ ምንም ኃይል የሌለው እንደነበረ  ሊገልጽልንና  ሊያሳየን ወዶ ነው ታድያ  የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲል ደቀመዛሙርቱ ከተናገሩበት ሃሳብ በብዙ የተለየ ነው ደቀመዛሙርቱ  ነፋሳትና ባሕር ስንኳ የሚታዘዙለት ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው ? እያሉ መደነቃቸው አድራጎቱንና ክንውኑን አይተው ከመገረም የተነሳ ሳይሆን ፍጹም ያላወቁት በመሆናቸው ነው  የኢየሱስን ማንነትና ምንነት ገና በትክክል አልተረዱም የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ግን ጌታ በማዕበሉ ላይ ያሳየውን ሥልጣን ከመረዳት የተነሳ አድናቆቱን ከዚህ በተለየ መልኩ ሊቸረን ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ አለ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲል ተናገረ በእርግጥም የኛ ጌታ የኛን ሥጋ ከመልበሱ የተነሣ የተኛ የተቀሰቀሰና ከእንቅልፉም የተነሳ ቢሆንም ማዕበሉን ግን ዝም በል ጸጥ በል በማለት በአንድ ድምጽ ያቆመው ነበረና  የቀረበ የመሰለው ማዕበል በእርግጥም ሊቀርበው ያልቻለ ነበረ ይሄ ጌታ ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ እንደመሆኑ መጠን መገለጡን በራሱ ጊዜ ያሳያል ሲል መጽሐፉ የዘገበልን ቢሆንም እርሱ ግን ብቻውን የማይሞት ነውና አይደለም  ሐዋርያትን ያስጮኸ ስንጠፋ አይገድህምን ያስባለ ይህ ማዕበል ሊቀርበው እርሱ  ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራልና  አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን አሜን ሲል ሐዋርያው በ1ኛ ጢሞቴዎስ 6 13 _ 16 በተጻፈው መልዕክቱ ሲናገረን እንመለከታለን የክፍል ሁለት ትምህርት ይቀጥላል የምናነበውንም ሆነ የሰማነውን በልቡናችን ያሳድርልን አብርሆተ መንፈስቅዱስ ቃሉን በአብርሆት ይግለጽልን


ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry


አገልጋይና ባለ ራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment