Friday, November 13, 2015

ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ከክፍል አንድ _____ ክፍል አራት በተከታታይ የቀረበ

ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን በሚል አርዕስት ከክፍል አንድ እስከ ክፍል አራት የቀረበውን ተከታታይ ትምህርት ለእናንተ ለአንባቢዎቼ ይበልጥ እንዲመቻችሁና ሃሳቡንም ተከታትላችሁ እንድትይዙት በማሰብ በአንድ ላይ አያይዤ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ የትምህርት ርዕስ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ከክፍል አንድ  _____  ክፍል አራት በተከታታይ የቀረበ


የትምህርት ርዕስ










ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ


  
                                                                  
ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን  ክፍል አንድ   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን   የተወደዳችሁና የተከበራችሁ ብፁአን አባቶች አበው መምህራን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሕዝበ እግዚአብሔር ምዕመናን በሙሉ በቅድሚያ በፍቅሩና በርህራሄው የተቤዠን ለዘለዓለምም የወደደን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ ይክበር ይመስገን ከዚህ በመቀጠል ለዛሬ ወደ እናንተ ወደ ብፁአን አባቶች ወደ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና ወደ ቅዱሳን ምዕመናን የምትደርስ አጭር ትምህርት አዘል መልዕክት ትኖረኛለች እርስዋን በማስተዋል ሆናችሁ እንድትከታተሉኝ በፍጹም ትሕትና እና በተዋረደ ልብ ከታላቅ አክብሮት ጋር እጠይቃለሁ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ   ትርጉም ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ሌባ የማያገኘው ብል  ነቀዝ የማያበላሸው ሳጥናችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው                  ( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት )
  የተወደዳችሁ አባቶቼና ወንድሞቼ ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወገኖቼ በሙሉ ትምህርቴ የሚያጠነጥነው በዚህ ሃሳብ ዙርያ ነው ባለፈው ትምህርታችንም ከዚሁ ከመጽሐፈ ሰዓታት በመጥቀስ ፍኖት ለኀበ አቡሁ አንቀጽ ዘመንገለ ወላዲሁ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ይለናልና ወደ አማርኛው ስተረጉመው ወደ አባቱ የሚያደርስ መንገድ ወደ ወላጅ አባቱም የሚያስገባ በር ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ከመጽሐፍቅዱሳችን ሃሳብ ጋር በተለይም ከዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 6 ጋር በማገናኘት ዘርዘር አድርገን በሰፊው ተማምረናል የጥንቷ ኦርቶዶክሳዊትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ትክክለኛ ወንጌል የሰበከች መሆኑን የምናውቅበት መንገዱ ይህ ነው ብዙ ከእግዚአብሔር ቃል ሃሳብ ጋር የማይጋጩ ከመጽሐፈ ሰዓታት ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክስ ካሳተመቻቸው ከተለያዩ የጸሎትና የምሥጋና መጻሕፍቶችዋ ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት መንገድና እውነት ሕይወት መሆኑን እንደገናም የሕይወት በር መውጫና መግቢያ መሠማርያ በደሙ ኃጢአታችንን ያጠበልን  የኃጢአትንም ሥርየት የሰጠን ሊቀ ካህናችን መሆኑንና የመሣሠሉትን ሁሉ የሚገልጹ ቃሎች ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በፍጹም ሊጋጩ የማይችሉ ሃሳቦችን አግኝተናል ታድያ መጽሐፍቅዱሳችን በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈልን ብቸኛ መጽሐፋችን ነውና እነዚህን ሃሳቦች ስላገኘን እነዚህን መጻሕፍት በእግዚአብሔር መንፈስ ከተጻፈው ከመጽሐፍቅዱሳችን ጋር በእኩል ዓይን አስተያይተን የመጽሐፍቅዱስ ቃል ነው ብለን ባንወስደውም ወይም ስድሳ ሰባተኛ የመጽሐፍቅዱስ እትም ነው ባንለውም  ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይቃረን ቃል በውስጡ የተጻፈ ሃሳብ እስካገኘን ድረስ እውነቶችን ፈልቅቆ በማውጣትና ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በማገናኘት አሁን ላይ ላለው ትውልዳችን የቃሉን እውነት በብዙ እንዲረዳ ቤተክርስቲያኒቱንም ወደ ጥንተ መሠረቷ ወደ እግዚአብሔር ቃል እውነት እንዲመልስ እና   የራዕዩም ባለቤት ሆኖ በራዕይና በዓላማ ጭምር እንዲያገለግል ያላሰለሰ ትግል በማድረግ ብርቱ የሆነ ጥረት እያሳየን በጸሎትም ጭምር እየተጋን  ከማስተማር ከመስበክ ከመቀስቀስና ከማነቃቃት ወደኋላ አንልም ማለትም በመጽሐፎቹ ውስጥ ያሉትን የእግዚአብሔርም ቃል የደገፋቸውን እውነታዎች ከቃሉ ጋር እያገናኘን  የቃሉን እውነት እናስተምረዋለን ከተጻፈለት የመጽሐፉ ቃል ጋራም በብዙ እናስተዋውቀዋለን መልዕክተኛም ለላከው ነውና እንደሚል ቃሉ የተልዕኮም ሰው እናደርገዋለን ቤተክርስቲያኒቱ በወንጌል መሠረት ላይ በቆመችባቸው ዘመናት ሁሉ ከተረትና ልብ ወለድ ድርሰቶች ይልቅ የእግዚአብሔርን ቃል ያመነች እና  አምናም ቃሉን ብቻ ያስተማረች የምሥራቹን ቃልም በትክክል የሰበከች መሆኑን እንደሚገባ እናውጅለታለን  እንደገናም  ብዙዎች ይህን እውነት ካለማወቃቸው የተነሣ ቤተክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊት አይበሏት ወይንም ሊሏት አይውደዱ እንጂ እኛ ግን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይጋጩ እውነቶች በውስጧ ያገኘን በመሆኑ ይህቺ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ለመሆንዋ በጽኑ እንመሠክራለን ፣ እንናገራለን ወደ ሃሳባችን ስንመለስ ከላይ በመግቢያ ጥቅሳችን ላይ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሠራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን ሃሳብ አንስተን ነበር ትርጉሙም እንዲህ የሚል ነው ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ሌባ የማያገኘው ብል ነቀዝ የማያበላሸው ሳጥናችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚል ሃሳብ ይዟል       ዛሬ እንግዲህ ትኩረት አድርገን የምንመለከተው የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ እንደጠቆመን በግዕዙ ቃል ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ይላልና ሞገድ የማይቀርበው መርከባችን የሚል ትርጉም ስላለው ይህንን ሃሳብ ይዘን በማብራራት ይሆናል           ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ           ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ            ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን           ኢየሱስ ክርስቶስ ነው    ይህ የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲል ይህንን ሃሳብ ያገኘው ከየት ነው ? ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥም ማዕበል ያልቀረበው መርከብ ነው ወይ ? የሚለውንና ሌሎችንም ሃሳቦች ይዘን በመጠይቅ መልክ ስናቀርብ መልሱን የምናገኘው ከዚሁ ከመጽሐፍቅዱሳችን ነው በመጽሐፍቅዱሳችን በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ቊጥር 23 እስከ 27 በተጻፈው ሃሳብ መሠረት ኢየሱስ በታንኳይቱ ማለት በመርከብዋ ውስጥ ተኝቶ ሳለ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ  መናወጥ እንደሆነና ደቀመዛሙርቱም ጌታ ሆይ አድነን ጠፋን እያሉ እንዳስነሱት ክፍሉ ይናገራል አያይዞም ኢየሱስ ከተነሳ በኋላ በቀጥታ ያደረገው ነገር ይህ ነው እናንተ እምነት የጎደላችሁ ስለምን ትፈራላችሁ ? አላቸው ከዚህ በኋላ ተነስቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሰጸ ታላቅ ጸጥታም ሆነ ይለንና ቀጣዩን ሃሳብ በግዕዙ እናገረዋለሁ ወአንከሩ ሰብእ ወይቤሉ መኑ እንጋ ውእቱ ዝንቱ ዘይትኤዘዙ ሎቱ በሕርኒ ወነፋሳትኒ ወደ አማርኛው ስተረጉመው ሰዎቹም ነፋሳትና ባሕር ስንኳ የሚታዘዙለት ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው ? እያሉ ተደነቁ የሚል የቃሉን ትርጉም ሲሰጠን እናገኘዋለን ለዚህ ነው እንግዲህ የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ከፍ ባለ የቃለ አጋኖ ድምጽ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለን ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ማለቱ ነው ታድያ ይህንን አባባል በጥቅሉ ስናየው ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲል ደራሲው ሊል የፈለገው እውነታውን ከማስተባበል ወይንም ከመካድ አኳያ ተነስቶ በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ነው ለማለት ፈልጎ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕበል ቢቀርበውም በአንድ ቃል ትዕዛዝ ገስጾ ከሚያቆመው በስተቀር  ማዕበሉ በፊቱ ምንም ኃይል የሌለው እንደነበረ  ሊገልጽልንና  ሊያሳየን ወዶ ነው ታድያ  የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲል ደቀመዛሙርቱ ከተናገሩበት ሃሳብ በብዙ የተለየ ነው ደቀመዛሙርቱ  ነፋሳትና ባሕር ስንኳ የሚታዘዙለት ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው ? እያሉ መደነቃቸው አድራጎቱንና ክንውኑን አይተው ከመገረም የተነሳ ሳይሆን ፍጹም ያላወቁት በመሆናቸው ነው  የኢየሱስን ማንነትና ምንነት ገና በትክክል አልተረዱም የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ግን ጌታ በማዕበሉ ላይ ያሳየውን ሥልጣን ከመረዳት የተነሳ አድናቆቱን ከዚህ በተለየ መልኩ ሊቸረን ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ አለ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲል ተናገረ በእርግጥም የኛ ጌታ የኛን ሥጋ ከመልበሱ የተነሣ የተኛ የተቀሰቀሰና ከእንቅልፉም የተነሳ ቢሆንም ማዕበሉን ግን ዝም በል ጸጥ በል በማለት በአንድ ድምጽ ያቆመው ነበረና  የቀረበ የመሰለው ማዕበል በእርግጥም ሊቀርበው ያልቻለ ነበረ ይሄ ጌታ ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ እንደመሆኑ መጠን መገለጡን በራሱ ጊዜ ያሳያል ሲል መጽሐፉ የዘገበልን ቢሆንም እርሱ ግን ብቻውን የማይሞት ነውና አይደለም  ሐዋርያትን ያስጮኸ ስንጠፋ አይገድህምን ያስባለ ይህ ማዕበል ሊቀርበው እርሱ  ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራልና  አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን አሜን ሲል ሐዋርያው በ1ኛ ጢሞቴዎስ 6 13 _ 16 በተጻፈው መልዕክቱ ሲናገረን እንመለከታለን የክፍል ሁለት ትምህርት ይቀጥላል የምናነበውንም ሆነ የሰማነውን በልቡናችን ያሳድርልን አብርሆተ መንፈስቅዱስ ቃሉን በአብርሆት ይግለጽልን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry
 አገልጋይና ባለ ራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
 የትምህርት ርዕስ  ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ      
ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን  ክፍል ሁለት   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ   ትርጉም ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ሌባ የማያገኘው ብል  ነቀዝ የማያበላሸው ሳጥናችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው                  ( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት )
  የተወደዳችሁና የተከበራችሁ ብፁአን አባቶች አበው መምህራን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሕዝበ እግዚአብሔር ምዕመናን የክፍል ሁለት ትምህርታችንን አሁን እንቀጥላለን የእግዚአብሔር ጸጋና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ የሚለውን ሃሳብ አንስተን ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የተባለበትን ምክንያት መጽሐፍቅዱሳዊ ማስረጃ በመስጠት ማብራራታችን ይታወሳል ዛሬ ደግሞ ከዚሁ የቀጠለውን ሃሳብ እንመለከታለን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕበል ብቻ ሳይሆን ፈታኙም ቀርቦ ፈታኝ የሆኑ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን አንስቶበታል በመጨረሻ ግን ሂድ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው ያን ጊዜ ዲያብሎስ ተወው መላዕክትም ቀርበው ያገለግሉት ነበር በማለት የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል የማቴዎስ ወንጌል 4 1 _ 4 እንደገናም የሕግ መምህራን ፈሪሳውያንም ሊፈትኑት ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ወደ እርሱ ቀርበዋል በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ቊጥር 1 _ 11 በተጻፈው ቃል መሠረት ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርስዋን አቁመው  መምህር ሆይ ይህቺ ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች ሙሴም እንደዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ ? አሉት የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ ኢየሱስ ግን ጎንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው ደግሞም ጎንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንዳንድ እያሉ ወጡ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ ከሳሾችሽ የታሉ የፈረደብሽ የለም በማለት ኢየሱስ እንደማይፈርድባት ከነገራት በኋላ ሂጂ ደግመሽም ኃጢአት አትሥሪ ሲል ያሰናበታት ታድያ ኢየሱስን ብዙ ነገሮች መልካቸውን እየለወጡ የቀረቡት እንኳ ቢሆኑም ነገር ግን የእኛ ጌታ ለቀረበለት ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽን የሚሰጥ ጌታ ነውና ሁሉም አንዳንድ እያሉ እስኪወጡ ድረስ እንደ አመጣጣቸው መልሷቸዋል ኢየሱስ ነገሮችንም ሆነ ሁኔታዎችን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ እንዲሆኑለት እና እንዳይቀርቡትም አትቅረቡኝ ሲል ሰዎችን ያራቀና ያስፈራራ ዛሬም ላይ የሚያርቅ የሚያስፈራራ አምላክ አይደለም ማንኛውም ነገር በየትኛውም መንገድ ይምጣ ሁሉንም እንደየ አመጣጡ በመጣበት አኳኋን ልክና መልክ ሰጥቶ የአቅምንም ልክ አሳውቆ  በተገቢ ሁኔታ የሸኘና የሚሸኝም ጌታ ነው ከዚህም ሌላ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 22 ቊጥር 15 _ 22 ላይ የተጻፈልንን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ልጨምር እወዳለሁ የምንባቡም ክፍል እንዲህ ይላል ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ ደቀመዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ላኩበት እነርሱም መምህር ሆይ እውነተኛ እንደሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን ለማንም አታደላም የሰውን ፊት አትመለከትምና እንግዲህ ምን ይመስልሃል ? ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ? ወይስ አልተፈቀደም አሉት ወገኖቼ ታድያ እዚህ ላይ የኢየሱስስ መልስ ምን ነበር ? ተፈቅዶአል ወይንም አልተፈቀደም የሚሉ መልሶችን የሰጠ ይመስላል ? ወይስ ሌላ መልስ ነበረው ጌታችን ኢየሱስ ለዚሁ ጉዳይ መልስ ከመስጠቱ በፊት ጥያቄዎቹ በነገር እርሱን ለማጥመድ የመጡ ጥያቄዎች መሆናቸውን ገና ከመነሻ ሃሳባቸው እያሞጋገሱ ቀርበው ሲጠይቁት አውቋቸዋል ስለዚህ እርሱም መልስ ሲሰጥ ተፈቅዶአል ወይም አልተፈቀደም ያለ ሳይሆን እርሱ ያላቸው እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ በማለት ነው መልስ የሰጣቸው በመሆኑም እነርሱ በፈተና ሊያጠምዱት ወደ እርሱ ተጠግተው ካቀረቡለት ጥያቄ ይልቅ የኢየሱስ መልስ የበለጠ እና እጅግም አስደናቂ የሆነ ነበር የክፍል ሁለት ትምህርቴን ስደመድም እንግዲህ እነዚህን ሁሉ ጥቅሶች ያነሣሁበት ትልቁ ምክንያቴ የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ በመሆኑ ወደ አማርኛው ስተረጉመው ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚለውን ትርጉም ይሰጠናልና በዚያን ዘመን ኢየሱስ በነበረበት መርከብ ውስጥ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ መርከቢቱን ያናወጠ ማዕበል መጥቶ ከኢየሱስ በወጣ ቃል በአንድ ድምፅ ብቻ የተግሣጽ ቃል ተቀብሎና ተገስጾ የተመለሰ ቢሆንም ከዚያ መልስ የተለያዩ የሰይጣን ሥራዎችና በሰዎችም በኩል የመጡ የማጥመድ እንደገናም የተንኮል ፈተናዎች ወደ እርሱ ቀርበው ምንም ላያመጡ በመጡበት መንገድ መመለሳቸውን የተጻፉልን የመጽሐፍቅዱስ ክፍሎች በግልጽ ያሳዩናል ታድያ ይሄ ጌታ በሰማይ የሚኖር ቢሆንም በኛ ውስጥም ሊኖር ደግሞ እኛን ማደርያዎቹና መቅደሱ ስላደረገን በሰይጣንና ሰይጣን  በተጠቀመባቸው ወደፊትም በሚጠቀምባቸው ደካማ ሰዎች በኩል የሚመጣብንን ክስና የማጥመድ ፈተናም በውስጣችን ብቃት ሆኖ መልስን እየሰጠ የሚያሳፍርልንና ሰምተውንም ተደንቀው እስኪሄዱ ድረስ የሚያደርስልን ጌታ ነው መጽሐፍ ቅዱሳችን በዚሁ በማቴዎስ ወንጌል 22 22 ላይ ይህንም ሰምተው ተደነቁ ትተውትም ሄዱ በማለት ይናገራልና የተወደዳችሁ ወገኖቼ ሆይ ታንኳችንን ደፍኖ የሚያናውጠውን የማዕበል ዓይነት በአንድ መንገድ ብቻ መጠበቅ ሞኝነት እንደሆነ አበክሬ ልነግራችሁ እወዳለሁ የዛሬው ማዕበል በነገው ጊዜያችን እንደዛሬው ሆኖ አይመጣምና ይህን ማዕበል  በአንድ መንገድ ብቻ ልንጠብቀው አይገባም የሚመጣውም መልኩን ለውጦ በሌላ ዓይነት መልክ ነው ነገር ግን ያው የሆነው ኢየሱስ ለትላንቱ ማዕበል መገሰጫ ዝምና ጸጥ ማስባያ ቃል እንደነበረው ሁሉ ለነገው ፣ ከዚያም ባሻገር ለሚመጣው የተንኮልና የማጥመድ ማዕበል ልዩ የሆነ ፣ የበለጠ ፣ የተሻለም መልስ አለው ስለዚህ ትላንት ተገስጾ ዝም በል ጸጥ በል ተብሎ የሄደው ማዕበል በነገውም ሕይወታችን መልኩን ቀይሮ ቢመጣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ከዚህ ያላነሰና የበለጠ እርምጃ የሚወስድበት በመሆኑ ተገስጾ ይሄዳል በሰዎችም በኩል መጥቶ ከሆነ አሁንም እንደ ልማዱ እየፈራና እየተሸማቀቀ ሐፍረት ተከናነብኩ እኮ እያለና እየተደነቀም ትቶን ይሄዳል በመሆኑም ይህ ሁሉ በሕይወታችን እንዲሆን እኛም በእኛ በኩል የሚጠበቅብንን ነገር ማድረግ አለብን ከእኛ የሚጠበቀው ደግሞ መርከባችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ መጥተን  ወደ መርከቡ  ወደ ኢየሱስ ዛሬውኑ መግባት  ገብተንም ከሆነ አለመውጣት ነው መርከባችን ኢየሱስ ሕይወትን ደፍኖ ከሚያናውጥ ማዕበል እንደገናም በሰይጣንና በደካማ ሰዎች በኩል እየመጣ ከሚከሰንና በተንኮል ሊያጠምደንም ከሚፈልገን ባላንጣችን የሚያስጥለን እኛም ወደ መርከቡ ገብተን አለመውጣታችንን ስናሳውቅና እርሱም ሲያውቅልን ነው መርከብ በባሕር ላይ የሚመጡትን ችግሮች አልፎ አሳልፎም ወደ ወደቡ እንደሚያደርስ እውነተኛው መርከባችን ኢየሱስም እነዚህንና ወደፊትም የሚመጡብንን ማበሎች ትንኮሳዎች እንዲሁም ተንኮሎች እየገሰጸ አሳልፎ የፍጻሜ ወደብ ወደሆነው ያደርሰናል ያም ወደብ ወደ መርከቡ ወደ ኢየሱስ ከመግባታችን የተነሣ የገባንበት ገነት ነው የሉቃስ ወንጌል 19 1 _ 10 የሉቃስ ወንጌል 23 42 እና 43 1 ቆሮንቶስ 6 9 _ 11 የተወደደው ሰዓትና የመዳን ቀን አሁን ነውና 2 ቆሮንቶስ 6 2 እንደገናም በዓለም ፍጻሜ የአባቴ ቡሩካን ተብለን የምንወርሰው መንግሥተ ሰማያት አለን መርከባችን የሆነው የናዝሬቱ ኢየሱስ አስተማማኝ መርከባችን ሆኖ ወደ ገነት ያገባን ብቻ ሳይሆን የአባቱንም መንግሥት የሰጠን እንድንወርሳትም የፈቀደልን በመሆኑ የሉቃስ ወንጌል 12 12 የማቴዎስ ወንጌል 25 31 _ 46 ቆላስያስ 1 13 እና 14 ዛሬ ነገ ሳንል ማቅማማትና ማመንታትም ሳናደርግ ወደ መርከቡ ያልገባንና መርከቡንም ያልተሳፈርን ሰዎች ወደ መርከባችን ወደ ኢየሱስ አሁኑኑ መግባት ይሁንልን አባቶቼና ወንድሞቼ የክፍል ሁለት ትምህርቴን ጨርሻለሁ አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን  ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮወሰብሑ ወዘምሩ ሎቱወንግሩ ኩሎ መንክሮ መዝሙር 104 ( 105 ) 1 _ 3 የ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry
አገልጋይና ባለራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ  የትምህርት ርዕስ    
   ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ                                                                  
ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን  ንዑስ አርዕስት ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውሃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ…………
   ክፍል ሦስት   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን   ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ   ትርጉም ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ሌባ የማያገኘው ብል  ነቀዝ የማያበላሸው ሳጥናችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው                  ( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት )
   የተወደዳችሁ አባቶች ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና የእግዚአብሔር ሕዝብ ምዕመናን በሙሉ የእግዚአብሔር ሰላም ከእናንተም ከእኔም ጋር ይሁን በማለት ከዚህ በመቀጠል በቀጥታ ወደ ክፍል ሦስት ትምህርቴ እገባለሁ ለክፍል ሦስት ትምህርቴ እንደ መነሻ ሃሳብ አድርጌ የወሰድኩት በ1ኛ ጴጥሮስ 3 20 እና 21 ላይ የተጻፈልንን የመጽሐፍቅዱስ ክፍል ነው ከዚሁ ጋራ ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ፣ ምዕራፍ 7 እና ምዕራፍ 8 ን አያይዘን ብናጠናው መልካም ይሆናል  በ1ኛ ጴጥሮስ 3 ቁጥር 20 እና 21 የተጻፈው ቃል  እንዲህ የሚል ነው ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውሃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግስት በኖህ ዘመን በቆየበት ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል ይለናል የተወደዳችሁ ወገኖች ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ ወደ ተዘጋጀላቸው መርከብ በመግባት ከጥፋት ውሃ በኖህ ዘመን እንደዳኑ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል  ታድያ የተዘጋጀው መርከብ ለእነዚህ ሊድኑ ላሉ  ለጥቂት ማለት ለስምንት ነፍስ ብቻ ነው  የተዘጋጀው ? የሚል ጥያቄ ስናነሳ መልሱ በአጭሩ አይደለም ነው ምክንያቱም መጽሐፍቅዱሳችን ላይ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖህ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም ተብሎ ተጽፎልናል ለምን እግዚአብሔር በዚያን ዘመን ታገሰ ? ስንል ደግሞ ሊድኑ እንዳሉት እንደነዚህ ጥቂትና ስምንት ነፍስ አምነው በመታዘዝ ወደ መርከቡ የሚገቡ ሌሎችም ካሉ በሚል  ምክንያት ነው  ነገር ግን ከእነዚህ ጥቂትና ስምንት ነፍስ በቀር ያመነ አምኖም በመታዘዝ ወደ መርከቡ የገባ የለም ትላንት በኖህ ዘመን በነበረው የጥፋት ውሃ ከነዚህ ከዳኑ ጥቂትና ስምንት ነፍስ ሌላ  ሰዎች አምነው በመታዘዝ እና ወደ መርከቡም በመግባት እንዲድኑ እግዚአብሔር በትዕግሥቱ ከቆየ ዛሬስ አይታገስም ወይ የሚል ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን  ትዕግሥት የእግዚአብሔር ባሕርይና መሠረታዊ ዓላማም ስለሆነ እግዚአብሔር በኖህ ዘመን ከታገሠበት በላይ ዛሬም ይታገሳል እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ አንድያ ልጁን እስኪሰጠን ድረስ ነው እንዲሁ የወደደን መጽሐፍ ሲናገር በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል እስመ ከመዝ አፍቀሮ እግዚአብሔር ለዓለም እስከ ወልዶ ዋሕደ መጠወ ወወሀበ ቤዛ ለኲሉ ከመ ኲሉ ዘየአምን ቦቱ ኢይትሐጐል አላ ይረክብ ሕይወተ ዘለዓለም ወደ አማርኛው ስተረጉመው በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና የሚል ቃል ተጽፎልናል የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ቊጥር 16 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንድን ዘንድ አንድያ ልጁን የሰጠን ስለሆነ ከፍቅሩ የተነሳ ዛሬም ይታገሣል የኃጢአት ደሞዝ ሞት ሆኖ ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች ተብሎ የተጻፈልን እንኳን ቢሆን ጌታ እግዚአብሔር የሟቹን ሞት አይወድም ለዚህም ነው የእስራኤል ቤት ሆይ ስለምን ትሞታላችሁ የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና ይላል ጌታ እግዚአብሔር ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ ሲል የተናገረን ሮሜ 3 23 ሮሜ 6 23 ሕዝቅኤል 18 4 31 እና 32 መጽሐፍ አሁንም ስላዳነን ጌታ ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲናገር ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለተስፋ ቃሉ አይዘገይም ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል አለን 2 ጴጥሮስ 3 9   ያዳነን ጌታ እንኳ ተመልሶ የማይመጣው ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ ነው ማለትም ንስሐ ገብተው በማመን ወደ እውነተኛው መርከብ ወደ ራሱ ወደ ኢየሱስ እንዲገቡ ነው እግዚአብሔርም እንደኖህ ዘመን ባለ ትዕግሥት ውስጥ ሆኖ የሚቆየንና የሚጠብቀን የጌታችንን የኢየሱስን ቃል አምነን በመታዘዝ ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ውስጥ እንድንገባ ነው በዚህ ጉዳይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት ይህ ነው አለን 1 ጢሞቴዎስ 2 3 ጌታ እግዚአብሔር የሰዎች መዳንና እውነትን ማወቅ ዘላለማዊ የሆነ ናፍቆቱና ውዴታው ነው በመሆኑም ለዚህ ለደኅንነቱ  ጉዳይ ሰዎችን መውደዱም ሆነ መታገሱ እስከመጨረሻው ነው ነገር ግን የእግዚአብሔር ጉዳይ ይህ ሆኖ ሳለ ሰዎች ግን ይህንን አልተረዱም አለመረዳታቸው ደግሞ የሚያሳየን አለመታዘዛቸውን ነው ወደ ኖኅ መርከብ ለመግባት አምኖ መታዘዝ ከዚያን ዘመን ሰዎች የሚጠበቅ እንደነበር ሁሉ ወደ እውነተኛው መርከብ ወደ ኢየሱስም ለመግባት ዛሬም የአዳም ፍጥረት ከሆነው ከሰው ልጆች ሁሉ ይጠበቃል ኢየሱስ ሆይ ከማዕበልና ከወጀብ ከሞትና ከኩነኔ ከሰይጣን ግዛትና ከጨለማው መንግሥት ልታድነኝ የመጣህልኝ እውነተኛው መጠለያዬ የሞትን ድልድይ መሻገርያዬ ከሲኦል ገሃነም ማምለጫዬ እውነተኛው መርከቤ አንተ ኢየሱስ ነህ ስንል ለቃሉ ታዘን ወደዚሁ  መርከባችን ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ከገባን መርከባችን ኢየሱስ ከዚህ ሁሉ አድኖን ወደ ታሰበልን ሥፍራ ያደርሰናል ወደዚህ ወደ እውነተኛው መርከብ የቃሉን እውነት አምኖ በመታዘዝ ያልገባ ግን ይሄ ሁሉ ለእርሱ አይሆንለትም ማለትም አይድንም በኖህ ዘመን ኖህ ወዳዘጋጀው መርከብ አምነው በመታዘዝ ያልገቡ ሰዎች የጥፋት ውሃ አግኝቶአቸዋል በዚያው ልክ ደግሞ ወደ እውነተኛው መርከብ ወደ ኢየሱስ ቃሉን አምነው በመታዘዝ ያልገቡ ሰዎች  እንደኖህ ዘመን ዓይነቱ የጥፋት ውሃ ሳይሆን ከዛ በሃይል የተለየውና የባሰው ነገር ውስጥ ይገባሉ ያም የሲኦልና የገሃነመ እሳት እራት መሆን ለሰይጣንና ለሠራዊቱ ተላልፎ መሰጠት በጨለማው ግዛት ውስጥ ለዘላለም ተቀምጦ ሲሰቃዩ መኖርና የመሣሠሉት ናቸው ጌታ እግዚአብሔር ሁላችንንም ከዚህ ይጠብቀን ነገር ግን ከዚህ ይልቅ ዛሬውኑ ለቃሉ ታዘን ወደ  እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ብንገባ  ከነዚህ ሁሉ ጥፋቶች ለዘለዓለም ማምለጥ ይሆንልናል ኢየሱስ የናዝሬቱ ጌታ ወደዚህ ምድር የመጣው ለእኛም መርከብ የሆነልን በዚህ ምድር ሳለን ከሚያስቸግሩን ወቅታዊ ችግሮችና ማዕበሎች ሊያስመልጠን ብቻ አይደለም ለዘላለም ሊያሰቃየን ካለ ማዕበልና የሰይጣን የጨለማ መንግሥት ከዘላለም ሞት   ከኩነኔ ሊያድነን ጭምር ነው ወደ እርሱ ወደ እውነተኛው መርከብ ወደ ኢየሱስ ገብተው የተጠለሉ ሁሉ ከዚህ ስቃይ ከዚህ ፍርድና ኩነኔ አምልጠዋል በኖህ ዘመን የነበረው የጥፋት ውሃ ጎድሎአል የቀለለም ሆኖአል ውሃው የቀለለ ለመሆኑም የተላከች ርግብ በአፍዋ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ በመምጣቷ ተረጋገጠ በሐዲስ ኪዳን ግን ያለው የጥፋት ውሃ ግን መቅለሉ የታወቀውና የተረጋገጠው በእውነተኛው መርከብ በኢየሱስ ውስጥ ለቃሉ ታዘን ለገባን ለእኛ ለአማኞች ነው በኢየሱስ አምነው ወደ መርከቡ ወደ ኢየሱስ ላልገቡ ግን የጥፋት ውሃው እንዲሁ  እንዳለ ነው እንደ ኖህ ዘመን እንደነበረው የጥፋት ውሃ ጎደለ ወይም ቀለለ የምንለው ነገር አይደለም ከላይ በትምህርቴ መካከል እንደዘረዘርኩትም ኩነኔ ሲኦል ገሃነም የሰይጣን ጨለማ የዘላለም ሞት በኢየሱስ መርከብ ውስጥ ታዘንና ገብተን በመጠለል ያላመለጥነውና ወደፊትም በማመንና በመታዘዝ ወደዚሁ መርከባችን ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ገብተን የማናመልጠው ከሆነ መቼም ቢሆን መች የሚቀልም ሆነ የሚጎድል አይሆንም ስለዚህ ርግብዋ በአፍዋ ይዛ የመጣችውን የለመለመ የወይራ ቅጠል ብቻ በማየት አንታለል ዛሬ የብዙ ሰዎች ልብ ያለው እዚች የወይራ ቅጠል ላይ ነው ስለዚህ ዓመት በመጣ ቁጥር ብዙዎች ይህቺን ቅጠል ከአገልጋይ ካህናቶቻቸው ይቀበላሉ ለምለም ቄጠማም ሲሉ በራሳቸው ላይ ያስራሉ ለቤታቸውም ጉዝጓዝ ያደርጋሉ እንደገናም ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ይፈጽማሉ ለምለም ነገር መውደድ እና ተስፋ ማድረግ መልካም ነገር ቢሆንም ይቺ ርግብ በአፍዋ ይዛ የመጣችው የወይራ ቅጠል ግን በኖህ ዘመን የነበረውን የጥፋት ውሃ መጒደልና መቅለል ከሚያመለክት ውጪ ዛሬ በሐዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ ላለን ለእኛ የተለየ መረጃም ሆነ ፍንጭ የሚሰጠን አይደለም  እኛን የሚያስፈራንን የጥፋት ውሃ በኖህ ዘመን ከነበረ የጥፋት ውሃ ጋር እያመሳሰልን በንጽጽር ብናቀርበውም በኖህ ዘመን የነበረ የጥፋት ውሃ በኖህ ዘመን የነበረና እዛው ላይ ታሪኩ ያበቃ የጥፋት ውሃ ነው የጥፋት ውሃ ጐድሏል የቀለለም ሆኗል ይሄ በሐዲስ ኪዳን ዘመን ያለ የጥፋት ውሃ ግን ምንም ዓይነት መጉደል ወይንም መቅለልን ያላሳየና  የማያሳይ የጥፋት ውሃ ነው በውስጡ የዘላለም ሞትን ኩነኔን በዘላለም ፍርድ ውስጥ ገብቶ በጨለማ መኖርን የሚያሳይ የጥፋት ውሃ  ስለሆነ መጉደልም ሆነ መቅለልን  የሚያሳይ ነገር አይደለም  ይህንን የዘላለም ሞትንና ኩነኔን የያዘ ይህ የጥፋት ውሃ  በኖህ ዘመን እንደነበረ የጥፋት ውሃ ይጐላል ወይንም መቅለልን ያመጣል ብለን አንጠብቅም ስለዚህ የሚያስፈልገው አንድና አንድ ነገር ነው ይህንን የዘላለም ሞትን ኩነኔንና የጨለማውን ግዛት የያዘ የጥፋት ውሃ ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ገብተን ብቻ ነው የምናመልጠው ቃሉን ሰምተን በመታዘዝ ወደዚህ ወደ እውነተኛው መርከብ ወደ ኢየሱስ ገብተን ለተጠለልንና ላመለጥን ለእኛ   በመርከባችን በክርስቶስ ውስጥ ከመሆናችን የተነሣ የዘላለም ሞትን ያመጣው እና ወደፊትም የሚያመጣው አማናዊው የጥፋት ውሃ ፍጹም የሚያገኘን አይሆንም ከዚህ የተነሣ ይህ አማናዊው የጥፋት ውሃ ዛሬም ለኛ የጐደለና የቀለለ ነው ከዛ ውጪ ግን ጐደለ ወይም ቀለለ የምንለው ታሪክም ሆነ ምሳሌ የለም ስለዚህ አንዱን ነገር መምረጥ ለሕይወታችን ወሳኝና ዋና ነገር ነው ምክንያቱም እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኲነኔ የለባቸውም በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና በማለት ቃሉ ይናገረናል  ሮሜ 8 1 እና 2 እንደገናም በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል ይለናል የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ቊጥር 18 ሌሎችንም እንዲህ ዓይነት ተመሣሣይ ጥቅሶችን ማንሳት እንችላለን ታድያ እነዚህና የመሣሠሉት ጥቅሶች ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ለመግባታችንና በእርሱ በክርስቶስ ውስጥ ለመሆናችን የዘላለም ሞት ፍርድ ካለበት ከእውነተኛው የጥፋት ውሃም ለማምለጣችን  ዋናና  ወሳኝ ነገሮች ናቸው በእነዚህና በመሣሠሉት የቃሉ እውነቶች ውስጥ ከሌለን እውነተኛው የመዳኛ መርከብ ኢየሱስ ውስጥ ለመግባታችንና በዚያም ለመሆናችን እርግጠኞች አይደለንም እርግጠኛ ሆኖ በመርከቡ በኢየሱስ ውስጥ ለመሆን እነዚህን ቃሎች ማመን የግድ ነው በተሰጠን ዕድል ደግሞ አሁኑኑ አምነን ወደ መርከባችን ወደ ኢየሱስ ካልገባን ነገ የኛ አይደለምና ሌላ ጊዜ ብንል አይሆንም 2 ቆሮንቶስ 6 2 ስለዚህ የተወደደው ሰዓትና የመዳን ቀንም አሁን ነውና ዛሬ ነገ ሳንል አሁኑኑ ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ገብተን መዳን ይሁንልን  የክፍል አራት ትምህርታችን ይቀጥላል እስከዚያው ሰላም ሁኑልኝ በማለት የምሰናበታችሁ  ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
 Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry
መሪ እና አገልጋይ
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን   
  የትምህርት ርዕስ    
 ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ   
   ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን
  ንዑስ አርዕስት   የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ………………
  ወኢያእመሩ እስከ አመ መጽአ ማየ አይኅ ወአጥፍአ ኲሎ…………………
  ክፍል አራት    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን  ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ   ትርጉም ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ሌባ የማያገኘው ብል  ነቀዝ የማያበላሸው ሳጥናችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው                  ( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት )
          የተወደዳችሁ ወገኖች አበው መምህራን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በሙሉ ይህ የክፍል አራት ትምህርትና የማጠቃለያም ሃሳቤ ነው ዛሬ እንግዲህ እንደ መነሻ ሃሳብ አድርጌ የወሰድኩት የመጽሐፍቅዱስ ክፍል አለ እርሱም እንዲህ ይላል በመጀመርያ በግዕዙ ቃል እናገረዋለሁ ወኢያእመሩ እስከ አመ መጽአ ማየ አይኅ ወአጥፍአ ኲሎ ከማሁኬ ይከውን ምጽአቱ ለወልደ እጓለ እመሕያው ወደ አማርኛው ስተረጉመው እንዲህ የሚል ነው የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል ይለናል የተወደዳችሁ ወገኖቼ ያለማወቅ ጨለማ ትልቅ ጥፋትን ያመጣል ስለዚህ በማንኛውም የሕይወት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ባለማውቅ ማንነት ውስጥ ልንቀመጥ ፈጽሞ አይገባንም ባለማወቅ ሕይወት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ማጥፋት ብቻ ሳይሆን መጥፋትም አለ ስለዚህ አለማወቅ የሚወደድ ነገር አይደለም መጽሐፍቅዱሳችንም በትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 4 6 ላይ  ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆን እጠላሃለሁ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ በማለት ይናገራል እውቀት በሌለበት ቦታ ያለው ነገር ሁልጊዜ ጥፋት ነው በመሆኑም የማያውቅን ሰው ጌታ እግዚአብሔር ካህን  እንዳይሆን ይጠላል የእግዚአብሔርን ሕግ ስናውቅ የእግዚአብሔር እውቀት ይኖረናልና ትክክለኛ ካህን መሆን እንችላለን ከዚያ ውጪ ግን አይሆንም በነህምያ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ቊጥር 8 ላይ የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፥ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር ይለናል ስለዚህ ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያውቅና የሚያስተምር ትክክለኛ ካህን ነበር ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃል የተማረ ስለነበር የሚነበበውን ያስተውል ነበር ይለናል ካልተማርንና ካላወቅን ሌሎችን ማሳወቅ አንችልም ያልተማረ ሕዝብ ደግሞ ያልተማረ ነውና የሚነበብለትን ማስተዋል አይችልም ስለዚህ ቅዱሱን ማወቃችንን ማስቀደም ከሁላችን የሚጠበቅ ጉዳይ ነው የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነውና ምሣሌ 9 10 ወገኖቼ ስናውቅ እና ስንረዳ ነው ያለማወቅ ወራት ከእኛ የሚያልፍልን ካላወቅን ግን እዚያው ነን ጥፋትም መጥቶ ይወስደናል ለዚህ ነው መጽሐፍቅዱሳችን አሁንም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17 30 ላይ እንዲህ የሚለን  በመጀመርያ በግዕዙ ቃል  እናገረዋለሁ ወዘቀዲሙሰ መዋዕለ ኢያእምሮ  አሰሰለ እግዚአብሔር ወይእዜ ባሕቱ አዘዘ ለኲሉ ሰብእ ይነስሑ በኲለሄ ወደ አማርኛው ስተረጉመው እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል ቀን ቀጥሮአልና እያለ ይናገራል የተቀጠረው ቀን ደግሞ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሳቱ ሁሉን አረጋግጦአል ይለናልና ቀን  ጌታ እግዚአብሔር በዓለሙ ላይ በጽድቅ የሚፈርድበት ቀን ነው እነዚህን የእግዚአብሔር ቃል ሃሳቦች ዘርዘር አድርጌ የተናገርኩበት ምክንያት ስለ እውቀት በተለይም እግዚአብሔርን ስለማወቅ ያለን ግንዛቤ እንዲጨምርና ያለማወቅ ወራታችን አልፎ እኛም በየቦታችን ንስሐ እንድንገባ ነው ንስሐ ደግሞ የማወቅና የግንዛቤ ምልክት እንጂ የሽንፈት ምልክት አይደለም ሰው ንስሐ የሚገባው ሲያውቅ ነው ካላወቀ ግን ይጠፋል እንጂ የንስሐ እድል የለውም ማለትም ለንስሐ አይበቃም ወደ መነሻው ታሪካችን ስንመጣም  በኖህ ዘመን የነበሩ ሰዎች ትልቁ ችግራቸው ያለማወቅ ችግር ነው ይሄ ያለማወቅ ችግራቸው የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም እስኪወስድ ድረስ አደረሳቸው ታድያ እነዚህ ሕዝቦች ያላወቁት እንዳያውቁ ሆነው ስለተፈጠሩ ነው ? ወይስ ማወቅን እንደ ትልቅ ኃጢአት ስለቆጠሩት ? አንዳንዴ እኮ በእኛ ኅብረተሰብ ማወቅ እንደ ኃጢአት ተቆጥሮ እንዲህ እንዲህ ይታሰባል ስለዚህ የሚያውቅ ሰው ብዙ አይወደድም እንደገናም በማኅበረሰባችን ዘንድ ብዙ እንድናውቅ አንገፋም አንበረታታም ምን ያደርግልሃል ? ይበቃሃል ይቅርብህ ብዙ ርቀህ አትሂድ አትመራመርና የመሳሰሉትን ስንባል ኖረናል ዛሬም እየተባልን አለን ይህ ግን ሕይወታችንን በብዙ የጎዳ ትውልድን ባለማወቅ ጨለማ ያስቀመጠና ያደናቆረ የሰይጣን ሃሳብ እንጂ ከእግዚአብሔር የሆነ ሃሳብ አይደለም እግዚአብሔር እንድናውቅ አውቀንም እንድንድን ይፈልጋል የማያውቅን ሰው እግዚአብሔር እንደውም አይወድም ከላይ እንደጠቀስኩትም አገልጋዩም አያደርገውም በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍቅዱሳችንን ይበልጥ ወደ ውስጥ ገብተን በማንበብና በማጥናት ይህንን  እውነት ከቃሉ ሃሳብ ትገነዘቡ ዘንድ ይህን ትምህርት ለምትከታተሉ ሁሉ በትሕትናና በፍቅር ሆኜ ለማሳሰብ እወዳለሁ እነዚህ በኖህ ዘመን የነበሩ ሰዎች የጥፋት ውኃ መጥቶባቸው ሁላቸውንም የመውሰዱ ጉዳይ እንዲያውቁ ሆነው ስላልተፈጠሩ ወይንም አለማወቅ ዕድል ፈንታቸውና የወጣባቸው ዕጣ ስለሆነ ሳይሆን እንዲያውቁ ፈቃደኞች ስላልሆኑና ለማወቅም ጆሮ ስላልሰጡ ወይንም በሌላ አነጋገር ጆሮ ዳባ ልበስ ስላሉ ነው  እግዚአብሔርማ የሚያሳውቃቸውንና ወደ መርከቡም እንዲገቡ የሚጋብዛቸውን የጽድቅ ሰባኪ ኖህን ልኮላቸው ነበር 2 ጴጥሮስ 2 5 ይህንንም የጽድቅ ስብከት ሰምተው ወደ መርከቡ በመግባት ከጥፋት ውኃ ከሚድኑ ይልቅ ማግባትንና መጋባትን መብላትንና መጠጣትን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርገው ወሰዱ በዚህም ምክንያት በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል ተብለው አሁን ዘመን ላይ ሆነን የኢየሱስን መምጣት ለምንጠባበቀው ለእኛ ሳይቀር የመጣፋት ምሣሌ ሆነው ቀረቡልን የማቴዎስ ወንጌል ምራፍ 24 38 _ 40 ወገኖቼ  ወደ መሠረታዊው ወደ እግዚአብሔር ቃል እውነት  ስንመጣ ጌታ እግዚአብሔር ማግባትንና መጋባትን መብላትንና መጠጣትን የሚቃወም ሆኖ አይደለም ማግባትና መጋባት መብላትና መጠጣት ግን የሰዎች የመጀመርያ ጉዳያቸውና ተቀዳሚ ምርጫቸው ሊሆን አይገባም መጽሐፍቅዱሳችን በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ መልስ ይሰጠናል በ1ኛ ቆሮንቶስ 7 29 _ 31 ላይ ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና ይለናል የተወደዳችሁ ወገኖቼ እዚህ ላይ አንድ ነገር ማስተዋል ያለብን በኖህ ዘመን ጠፍቶ ያለ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ በሙሉ ይህንን የተጻፈ እውነት ካልተገነዘበ ሕይወት ለእርሱ የሚመስለው ማግባት መጋባት መደሰትና የመሣሠሉት ነገር ነው ነገር ግን ለእኛ ሕይወት ይሄ ብቻ እንደሆነ ካሰብን ትልቅ ውድቀትና ኪሣራ ውስጥ እንደሆንን ልናውቅ ይገባል በኖህ ዘመን ለነበሩ ሕዝቦች ትልቁ እሴታቸው ማግባት መጋባት መብላትና መጠጣት ስለነበረ ይህ ሁኔታቸው ለንስሐ እንኳ ሳይቀር እድል ሳይሰጣቸው ኪሳራና ጥፋት ውስጥ ጣላቸው ስለዚህ ወገኖቼ አገባን ተጋባንም በላን ጠጣንም ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ዛሬውኑ መነሣት ይገባናል  1 ቆሮንቶስ 10 31 ከትዳራችን ከማግባት ከመጋባታችን ከመብላት ከመጠጣታችንና በዚችም ዓለም ከመጠቀማችን በፊት እግዚአብሔርን ልናስቀድም ያስፈልጋል የሉቃስ ወንጌል 14 15 _ 24 የማቴዎስ ወንጌል 6 24 _ 33 እነዚህን ጥቅሶች መጽሐፍቅዱስዎትን ከፍተው ያንብቡአቸው ዘንድ እጋብዛለሁ ወዳጆቼ ሆይ ወደ እውነተኛው መርከብ ቀድመን መግባትና መዳን ከማንኛውም ሰው ይጠበቃልና ያልዳንን ከሆንን በመጀመርያ በዚህ ምድር ካለ ከሁሉና ከማንኛውም ነገር በፊት ለቃሉ በመታዘዝ ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ገብተን መዳን ይሁንልን ለምን ስንል የዚህች ዓለም መልኳ ኃላፊ ነውና በዚህች ዓለም ባገኘነው ባተረፍነውም ነገር ጠልቀን መቅረት የለብንም በሉቃስ ወንጌል በምሣሌ የቀረበልን ባለጸጋ ሰው ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን አከማቻለሁ ነፍሴንም አንቺ ነፍሴ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ ዕረፊ ብዪ ጠጪ ደስ ይበልሽ በማለቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምን ትዕዛዝ እንደወጣበት የክፍሉን መጽሐፍ አውጥተን በመመልከት መረዳት እንችላለን የሉቃስ ወንጌል 12 13 _ 21 ወደ መርከቡ ገብተን ድነን ከሆነ ደግሞ ከዳንበት መርከብ ላለመውጣት ውሳኔ አድርገን በዚያው በመርከቡ በኢየሱስ ውስጥ መጽናት እና ከፍጻሜው ወደብ ላይ መድረስ የሁላችንም ጸሎት  ልመናና ምልጃም ሊሆን ይገባል የተወደዳችሁ ወገኖች  የክፍል አራት ትምህርቴን በዚሁ አጠቃልያለሁ  ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን በሚለው ዋና የትምህርት አርዕስት እስከ ክፍል አራት ድረስ የቀጠለው ትምህርት  በዚሁ የተደመደመ ሲሆን ከክፍል አንድ ጀምሮ እስከ ክፍል አራት ቀጥለው ፖስት የተደረጉትን ሁሉንም ትምህርቶች ተከታትላችሁ ካነበባችሁ ከሰማችሁና ከተጠቀማችሁ በኋላ ለሌሎች ሊጠቀሙ ለሚፈልጉ ሁሉ ሼር እንድታደርጉትና እንድታስተላልፉት ከትልቅ አክብሮትና ትሕትና ጋር እጠይቃለሁ ጌታ እግዚአብሔር የተማርናቸውን ቃሎቹን በልቡናችን አሳድሮ በትክክለኛው የቃሉ መንገድ  ይምራን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
 Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ  ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ     

No comments:

Post a Comment