መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሠራቂ
ሌባ የማያገኘው መዝገባችን
ክፍል አንድ
መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ
ትርጉም ፦ ሌባ የማያገኘው ብል
ነቀዝ የማያበላሸው መዝገባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው
( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት )
ባለፈው ጊዜ በተከታታይ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን በሚል የትምህርት አርዕስት የዚሁ የመጽሐፈ ሰዓታትን ሃሳብ መነሻ አድርገን ከመጽሐፍቅዱሳችን ጋር በማመሳከር ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ማን እንደሆነና ማዕበል የማይቀርበው የተባለበትም ምክንያት ከምን አንፃር እንደሆነ ፣ የመርከቡን ማንነትና የሰጠውን ጠቀሜታ፣ ወደ መርከቡም ተጋብዘው የገቡት ሰዎች ቊጥር ልክና ባለመታዘዝ ምክንያትም በዚሁ የጥፋት ውሃ የጠፉትን በማንሳት ፣ ከዛሬው ጌታችንን ከምንጠብቅ ከእኛም ጋር በማገናዘብ ከእግዚአብሔር እውነት ጋር ካልተስማማን የእኛም የወደፊት ዕጣችን ምን ሊሆን እንደሚችል በአራት ተከታታይ ክፍል በየተራ ከፍለን እንደሚገባ በሰፊው ማቅረባችን እና መማማራችንም ይታወሳል እናንተም ወገኖች በዚህ ተከታታይ ትምህርት በብዙ እንደተባረካችሁ እናምናለን ደግሞም ተስፋ እናደርጋለን አሁን ደግሞ ከዚሁ የቀጠለውን መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን ወደ አማርኛው ስተረጉመው ሌባ የማያገኘው ብል
ነቀዝ የማያበላሸው መዝገባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚል ትርጉም ይሰጠናልና ይህንኑ የመጽሐፈ ሰዓታት ሃሳብ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ቊጥር 19 እስከ 21 ከተጻፈው ሃሳብ ጋር በማገናኘትና በማመሳከር እንመለከተዋለን በዚህ ትምህርት ውስጥ እንግዲህ ይህ የመጽሐፈ ሰዓታት ሃሳብ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይጋጭ ሃሳብ ያለው በመሆኑ ቤተክርስቲያኒቱ ከዚህ በፊት በነበራት ትክክለኛ የእግዚአብሔር ቃል መረዳት ትክክለኛውን የእግዚአብሔር ቃል እውነት ለሰዎች የምታስተምር መሆኑን ከነዚህ ሃሳቦች ተነስተን በጥልቀት መረዳት እንችላለን የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በማለት ሌባ የማያገኘው ብል
ነቀዝ የማያበላሸው መዝገባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚል ትርጉም የሚሰጠን ነውና ይህንን
ከማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ፥ 19 _ 21 ጋር በማመሳከር ግልጽ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል እውነት እንማማራለን የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ በዘገበው ሃሳብ መሠረት ሌባ የማያገኘው ብል
ነቀዝ የማያበላሸው መዝገባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲለን ማቴዎስ በወንጌሉ ደግሞ ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና አለን የማቴዎስ ወንጌል 6 ፥ 19 _ 21 ስለዚህ በምድር ላይ ላይ በሥጋው ወራት አስተምሮና ሰብኮ ሕሙማንን ፈውሶ ፣ አጋንንትን አውጥቶ የኃጢአትንም ሥርየት ሰጥቶ በመጨረሻም ለሰው ልጆች ኃጢአት በመስቀል ላይ ሞቶ እና ተቀብሮ
በመቃብር ጉድጓድ ውስጥ በመቅረት ብል ፣ ነቀዝ ያላበላሸው
ሌቦችም ቆፍረው ያልሰረቁት አንዱና እውነተኛው የሰማይ መዝገባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው በመሆኑም መዝገባችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ባለበት የእኛም ልባችን ደግሞ በዚያ ሊሆን ይገባል ታድያ ብል ፣ ነቀዝ ስላላበላሸው ሌቦችም ቆፍረው ስላልሰረቁት ስለዚህ እውነተኛው መዝገባችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ዝርዝር ሃሳብ ከማቅረባችን እና ከመማማራችን በፊት መዝገብ የሚለውን ጥሬ ቃል በማንሳት በቀላሉ ስንት ዓይነት መዝገብ እንዳለ የሚጠቁመንን የእግዚአብሔር ቃል መረጃም በማቅረብ የቀረቡትን የመዝገብ ዓይነቶች በቀጣይነት እንደሚከተለው እንመለከታለን አንደኛው የመዝገብ ዓይነት
1ኛ _ የእግዚአብሔር የተለየ ሀብት ያለበት ሥፍራን የሚያሳይ መዝገብ ነው
በዘዳግም 28 ፥ 12 ላይ እግዚአብሔርም ለምድርህ በወራቱ ዝናብ ይሰጥ ዘንድ፥ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርክ ዘንድ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ ለብዙ አሕዛብም ታበድራለህ፥ አንተ ግን ከማንም አትበደርም ይለናል
በዘዳግም 33 ፥ 19 ላይ ደግሞ የተሰወረውን የአሸዋውን መዝገብ የባሕሩንም ባለጠግነት ይጠባሉና አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ በዚያ የጽድቅ መሥዋዕት ይሠዋሉ ይላል
በመዝሙር 17 ፥ 14 ም በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል እግዚኦ እምውኁዳነ ምድር ንፍቆሙ በሕይወቶሙ እምኅቡአቲከ ጸግበት ከርሦሙ ጸግቡ ደቂቆሙ ወኃደጉ ትራፋቲሆሙ ለሕጻናቲሆሙ ወአንሰ በጽድቅከ እሬኢ ገጸከ ወእጸግብ በርእየ ስብሐቲከ ትርጉም አቤቱ፥ ከሰዎች፥ እድል ፈንታቸው በሕይወታቸው ከሆነች ከዚህ ዓለም ሰዎች በእጅህ አድነኝ፤ ከሰወርኸው መዝገብህ ሆዳቸውን አጠገብህ፤ ልጆቻቸው ብዙ ናቸው የተረፋቸውንም ለሕፃናቶቻቸው ያተርፋሉ እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ ብሎናል
በትንቢተ ኢሳይያስ 45 ፥ 3 ላይ ደግሞ በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ ይላል
በቆላስያስ 2 ፥ 1 _ 3 ላይም በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል ወእፈቅድ ታእምሩ መጠነ እትጋደል በእንቲአክሙ ወበእንተ እለ በሎዶቅያ ወበእንተ ኲሎሙ እለ ኢርእዩኒ ገጽየ በሥጋየ ከመ ይትፈሥሖሙ ልቦሙ ወይጽናዕ ትምህርቶሙ በተፋቅሮ ወበኲሉ ብዕለ ፍጻሜ ወጥበብ ወበሃይማኖት ወበአእምሮ ምክሩ ለእግዚአብሔር ዘበእንተ ክርስቶስ ዘኀቤሁ ሀሎ ኲሉ መዝገበ ጥበብ ወምክር ኅቡእ ወደ አማርኛው ስተረጉመው ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ፊቴንም በሥጋ ስላላዩት ሁሉ እንዴት ያለ ትልቅ መጋደል እንዳለኝ ልታውቁ እወዳለሁና ልባቸው እንዲጸና፥ በፍቅርም ተባብረው በማስተዋል ወደሚገኝበት ወደ መረዳት ባለ ጠግነት ሁሉ እንዲደርሱ የእግዚአብሔርንም ምሥጢር እርሱንም ክርስቶስን እንዲያውቁ እጋደላለሁ የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና ይለናል
የተወደዳችሁ ወገኖች ብዙ ዓይነት መዝገቦች ቢኖሩም በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ የተመለከት
ነው እንግዲህ ከመዝገቦቹ መካከል አንደኛውን መዝገብ በመምረጥ ነው ትምህርቱ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ሌሎች ቀጣይነት ያላቸውን መዝገቦችም በሚከተለው መንገድ በተከታይነት አቀርበዋለሁ ለዛሬ ግን የክፍል አንድ ትምህርቴን በዚህ እጠቀልላለሁ ጌታ እግዚአብሔር በምናነበውና በምንሰማውም ቃል ተጠቃሚዎች ያድርገን አሜን
የ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and
Preaching Ministry
አገልጋይና ባለ ራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
No comments:
Post a Comment