Tuesday, November 10, 2015
የትምህርት ርዕስ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ንዑስ አርዕስት ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውሃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ………… ክፍል ሦስት በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ትርጉም ፦ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ሌባ የማያገኘው ብል ነቀዝ የማያበላሸው ሳጥናችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት ) የተወደዳችሁ አባቶች ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና የእግዚአብሔር ሕዝብ ምዕመናን በሙሉ የእግዚአብሔር ሰላም ከእናንተም ከእኔም ጋር ይሁን በማለት ከዚህ በመቀጠል በቀጥታ ወደ ክፍል ሦስት ትምህርቴ እገባለሁ ለክፍል ሦስት ትምህርቴ እንደ መነሻ ሃሳብ አድርጌ የወሰድኩት በ1ኛ ጴጥሮስ 3 ፥ 20 እና 21 ላይ የተጻፈልንን የመጽሐፍቅዱስ ክፍል ነው ከዚሁ ጋራ ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ፣ ምዕራፍ 7 እና ምዕራፍ 8 ን አያይዘን ብናጠናው መልካም ይሆናል በ1ኛ ጴጥሮስ 3 ቁጥር 20 እና 21 የተጻፈው ቃል እንዲህ የሚል ነው ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውሃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግስት በኖህ ዘመን በቆየበት ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም ይህም ውሃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል ይለናል የተወደዳችሁ ወገኖች ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ ወደ ተዘጋጀላቸው መርከብ በመግባት ከጥፋት ውሃ በኖህ ዘመን እንደዳኑ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል ታድያ የተዘጋጀው መርከብ ለእነዚህ ሊድኑ ላሉ ለጥቂት ማለት ለስምንት ነፍስ ብቻ ነው የተዘጋጀው ? የሚል ጥያቄ ስናነሳ መልሱ በአጭሩ አይደለም ነው ምክንያቱም መጽሐፍቅዱሳችን ላይ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖህ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም ተብሎ ተጽፎልናል ለምን እግዚአብሔር በዚያን ዘመን ታገሰ ? ስንል ደግሞ ሊድኑ እንዳሉት እንደነዚህ ጥቂትና ስምንት ነፍስ አምነው በመታዘዝ ወደ መርከቡ የሚገቡ ሌሎችም ካሉ በሚል ምክንያት ነው ነገር ግን ከእነዚህ ጥቂትና ስምንት ነፍስ በቀር ያመነ ፣ አምኖም በመታዘዝ ወደ መርከቡ የገባ የለም ትላንት በኖህ ዘመን በነበረው የጥፋት ውሃ ከነዚህ ከዳኑ ጥቂትና ስምንት ነፍስ ሌላ ሰዎች አምነው በመታዘዝ እና ወደ መርከቡም በመግባት እንዲድኑ እግዚአብሔር በትዕግሥቱ ከቆየ ዛሬስ አይታገስም ወይ የሚል ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን ትዕግሥት የእግዚአብሔር ባሕርይና መሠረታዊ ዓላማም ስለሆነ እግዚአብሔር በኖህ ዘመን ከታገሠበት በላይ ዛሬም ይታገሳል እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ አንድያ ልጁን እስኪሰጠን ድረስ ነው እንዲሁ የወደደን መጽሐፍ ሲናገር በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል እስመ ከመዝ አፍቀሮ እግዚአብሔር ለዓለም እስከ ወልዶ ዋሕደ መጠወ ወወሀበ ቤዛ ለኲሉ ከመ ኲሉ ዘየአምን ቦቱ ኢይትሐጐል አላ ይረክብ ሕይወተ ዘለዓለም ወደ አማርኛው ስተረጉመው በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና የሚል ቃል ተጽፎልናል የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ቊጥር 16 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንድን ዘንድ አንድያ ልጁን የሰጠን ስለሆነ ከፍቅሩ የተነሳ ዛሬም ይታገሣል የኃጢአት ደሞዝ ሞት ሆኖ ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች ተብሎ የተጻፈልን እንኳን ቢሆን ጌታ እግዚአብሔር የሟቹን ሞት አይወድም ለዚህም ነው የእስራኤል ቤት ሆይ ስለምን ትሞታላችሁ የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና ይላል ጌታ እግዚአብሔር ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ ሲል የተናገረን ሮሜ 3 ፥ 23 ፣ ሮሜ 6 ፥ 23 ፣ ሕዝቅኤል 18 ፥ 4 ፣ 31 እና 32 መጽሐፍ አሁንም ስላዳነን ጌታ ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲናገር ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለተስፋ ቃሉ አይዘገይም ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል አለን 2ኛ ጴጥሮስ 3 ፥ 9 ያዳነን ጌታ እንኳ ተመልሶ የማይመጣው ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ ነው ማለትም ንስሐ ገብተው በማመን ወደ እውነተኛው መርከብ ወደ ራሱ ወደ ኢየሱስ እንዲገቡ ነው እግዚአብሔርም እንደኖህ ዘመን ባለ ትዕግሥት ውስጥ ሆኖ የሚቆየንና የሚጠብቀን የጌታችንን የኢየሱስን ቃል አምነን በመታዘዝ ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ውስጥ እንድንገባ ነው በዚህ ጉዳይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት ይህ ነው አለን 1ኛ ጢሞቴዎስ 2 ፥ 3 ጌታ እግዚአብሔር የሰዎች መዳንና እውነትን ማወቅ ዘላለማዊ የሆነ ናፍቆቱና ውዴታው ነው በመሆኑም ለዚህ ለደኅንነቱ ጉዳይ ሰዎችን መውደዱም ሆነ መታገሱ እስከመጨረሻው ነው ነገር ግን የእግዚአብሔር ጉዳይ ይህ ሆኖ ሳለ ሰዎች ግን ይህንን አልተረዱም አለመረዳታቸው ደግሞ የሚያሳየን አለመታዘዛቸውን ነው ወደ ኖኅ መርከብ ለመግባት አምኖ መታዘዝ ከዚያን ዘመን ሰዎች የሚጠበቅ እንደነበር ሁሉ ወደ እውነተኛው መርከብ ወደ ኢየሱስም ለመግባት ዛሬም የአዳም ፍጥረት ከሆነው ከሰው ልጆች ሁሉ ይጠበቃል ኢየሱስ ሆይ ከማዕበልና ከወጀብ ከሞትና ከኩነኔ ከሰይጣን ግዛትና ከጨለማው መንግሥት ልታድነኝ የመጣህልኝ እውነተኛው መጠለያዬ የሞትን ድልድይ መሻገርያዬ ከሲኦል ገሃነም ማምለጫዬ እውነተኛው መርከቤ አንተ ኢየሱስ ነህ ስንል ለቃሉ ታዘን ወደዚሁ መርከባችን ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ከገባን መርከባችን ኢየሱስ ከዚህ ሁሉ አድኖን ወደ ታሰበልን ሥፍራ ያደርሰናል ወደዚህ ወደ እውነተኛው መርከብ የቃሉን እውነት አምኖ በመታዘዝ ያልገባ ግን ይሄ ሁሉ ለእርሱ አይሆንለትም ማለትም አይድንም በኖህ ዘመን ኖህ ወዳዘጋጀው መርከብ አምነው በመታዘዝ ያልገቡ ሰዎች የጥፋት ውሃ አግኝቶአቸዋል በዚያው ልክ ደግሞ ወደ እውነተኛው መርከብ ወደ ኢየሱስ ቃሉን አምነው በመታዘዝ ያልገቡ ሰዎች እንደኖህ ዘመን ዓይነቱ የጥፋት ውሃ ሳይሆን ከዛ በሃይል የተለየውና የባሰው ነገር ውስጥ ይገባሉ ያም የሲኦልና የገሃነመ እሳት እራት መሆን ለሰይጣንና ለሠራዊቱ ተላልፎ መሰጠት በጨለማው ግዛት ውስጥ ለዘላለም ተቀምጦ ሲሰቃዩ መኖርና የመሣሠሉት ናቸው ጌታ እግዚአብሔር ሁላችንንም ከዚህ ይጠብቀን ነገር ግን ከዚህ ይልቅ ዛሬውኑ ለቃሉ ታዘን ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ብንገባ ከነዚህ ሁሉ ጥፋቶች ለዘለዓለም ማምለጥ ይሆንልናል ኢየሱስ የናዝሬቱ ጌታ ወደዚህ ምድር የመጣው ለእኛም መርከብ የሆነልን በዚህ ምድር ሳለን ከሚያስቸግሩን ወቅታዊ ችግሮችና ማዕበሎች ሊያስመልጠን ብቻ አይደለም ለዘላለም ሊያሰቃየን ካለ ማዕበልና የሰይጣን የጨለማ መንግሥት ፣ ከዘላለም ሞት ፣ ከኩነኔ ሊያድነን ጭምር ነው ወደ እርሱ ወደ እውነተኛው መርከብ ወደ ኢየሱስ ገብተው የተጠለሉ ሁሉ ከዚህ ስቃይ ከዚህ ፍርድና ኩነኔ አምልጠዋል በኖህ ዘመን የነበረው የጥፋት ውሃ ጎድሎአል የቀለለም ሆኖአል ውሃው የቀለለ ለመሆኑም የተላከች ርግብ በአፍዋ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ በመምጣቷ ተረጋገጠ በሐዲስ ኪዳን ግን ያለው የጥፋት ውሃ ግን መቅለሉ የታወቀውና የተረጋገጠው በእውነተኛው መርከብ በኢየሱስ ውስጥ ለቃሉ ታዘን ለገባን ለእኛ ለአማኞች ነው በኢየሱስ አምነው ወደ መርከቡ ወደ ኢየሱስ ላልገቡ ግን የጥፋት ውሃው እንዲሁ እንዳለ ነው እንደ ኖህ ዘመን እንደነበረው የጥፋት ውሃ ጎደለ ወይም ቀለለ የምንለው ነገር አይደለም ከላይ በትምህርቴ መካከል እንደዘረዘርኩትም ኩነኔ ሲኦል ገሃነም የሰይጣን ጨለማ የዘላለም ሞት በኢየሱስ መርከብ ውስጥ ታዘንና ገብተን በመጠለል ያላመለጥነውና ወደፊትም በማመንና በመታዘዝ ወደዚሁ መርከባችን ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ገብተን የማናመልጠው ከሆነ መቼም ቢሆን መች የሚቀልም ሆነ የሚጎድል አይሆንም ስለዚህ ርግብዋ በአፍዋ ይዛ የመጣችውን የለመለመ የወይራ ቅጠል ብቻ በማየት አንታለል ዛሬ የብዙ ሰዎች ልብ ያለው እዚች የወይራ ቅጠል ላይ ነው ስለዚህ ዓመት በመጣ ቁጥር ብዙዎች ይህቺን ቅጠል ከአገልጋይ ካህናቶቻቸው ይቀበላሉ ለምለም ቄጠማም ሲሉ በራሳቸው ላይ ያስራሉ ለቤታቸውም ጉዝጓዝ ያደርጋሉ እንደገናም ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ይፈጽማሉ ለምለም ነገር መውደድ እና ተስፋ ማድረግ መልካም ነገር ቢሆንም ይቺ ርግብ በአፍዋ ይዛ የመጣችው የወይራ ቅጠል ግን በኖህ ዘመን የነበረውን የጥፋት ውሃ መጒደልና መቅለል ከሚያመለክት ውጪ ዛሬ በሐዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ ላለን ለእኛ የተለየ መረጃም ሆነ ፍንጭ የሚሰጠን አይደለም እኛን የሚያስፈራንን የጥፋት ውሃ በኖህ ዘመን ከነበረ የጥፋት ውሃ ጋር እያመሳሰልን በንጽጽር ብናቀርበውም በኖህ ዘመን የነበረ የጥፋት ውሃ በኖህ ዘመን የነበረና እዛው ላይ ታሪኩ ያበቃ የጥፋት ውሃ ነው ያ የጥፋት ውሃ ጐድሏል የቀለለም ሆኗል ይሄ በሐዲስ ኪዳን ዘመን ያለ የጥፋት ውሃ ግን ምንም ዓይነት መጉደል ወይንም መቅለልን ያላሳየና የማያሳይ የጥፋት ውሃ ነው በውስጡ የዘላለም ሞትን ፣ ኩነኔን በዘላለም ፍርድ ውስጥ ገብቶ በጨለማ መኖርን የሚያሳይ የጥፋት ውሃ ስለሆነ መጉደልም ሆነ መቅለልን የሚያሳይ ነገር አይደለም ይህንን የዘላለም ሞትንና ኩነኔን የያዘ ይህ የጥፋት ውሃ በኖህ ዘመን እንደነበረ የጥፋት ውሃ ይጐላል ወይንም መቅለልን ያመጣል ብለን አንጠብቅም ስለዚህ የሚያስፈልገው አንድና አንድ ነገር ነው ይህንን የዘላለም ሞትን ፣ ኩነኔንና የጨለማውን ግዛት የያዘ የጥፋት ውሃ ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ገብተን ብቻ ነው የምናመልጠው ቃሉን ሰምተን በመታዘዝ ወደዚህ ወደ እውነተኛው መርከብ ወደ ኢየሱስ ገብተን ለተጠለልንና ላመለጥን ለእኛ በመርከባችን በክርስቶስ ውስጥ ከመሆናችን የተነሣ የዘላለም ሞትን ያመጣው እና ወደፊትም የሚያመጣው አማናዊው የጥፋት ውሃ ፍጹም የሚያገኘን አይሆንም ከዚህ የተነሣ ይህ አማናዊው የጥፋት ውሃ ዛሬም ለኛ የጐደለና የቀለለ ነው ከዛ ውጪ ግን ጐደለ ወይም ቀለለ የምንለው ታሪክም ሆነ ምሳሌ የለም ስለዚህ አንዱን ነገር መምረጥ ለሕይወታችን ወሳኝና ዋና ነገር ነው ምክንያቱም እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኲነኔ የለባቸውም በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና በማለት ቃሉ ይናገረናል ሮሜ 8 ፥ 1 እና 2 እንደገናም በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል ይለናል የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ቊጥር 18 ሌሎችንም እንዲህ ዓይነት ተመሣሣይ ጥቅሶችን ማንሳት እንችላለን ታድያ እነዚህና የመሣሠሉት ጥቅሶች ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ለመግባታችንና በእርሱ በክርስቶስ ውስጥ ለመሆናችን የዘላለም ሞት ፍርድ ካለበት ከእውነተኛው የጥፋት ውሃም ለማምለጣችን ዋናና ወሳኝ ነገሮች ናቸው በእነዚህና በመሣሠሉት የቃሉ እውነቶች ውስጥ ከሌለን እውነተኛው የመዳኛ መርከብ ኢየሱስ ውስጥ ለመግባታችንና በዚያም ለመሆናችን እርግጠኞች አይደለንም እርግጠኛ ሆኖ በመርከቡ በኢየሱስ ውስጥ ለመሆን እነዚህን ቃሎች ማመን የግድ ነው በተሰጠን ዕድል ደግሞ አሁኑኑ አምነን ወደ መርከባችን ወደ ኢየሱስ ካልገባን ነገ የኛ አይደለምና ሌላ ጊዜ ብንል አይሆንም 2ኛ ቆሮንቶስ 6 ፥ 2 ስለዚህ የተወደደው ሰዓትና የመዳን ቀንም አሁን ነውና ዛሬ ነገ ሳንል አሁኑኑ ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ገብተን መዳን ይሁንልን የክፍል አራት ትምህርታችን ይቀጥላል እስከዚያው ሰላም ሁኑልኝ በማለት የምሰናበታችሁ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ የ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry መሪ እና አገልጋይ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment