Thursday, November 26, 2015
M2U00059 መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሠራቂ ሌባ የማያገኘው መዝገባችን ክፍል አራት መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ትርጉም ፦ ሌባ የማያገኘው ብል ነቀዝ የማያበላሸው መዝገባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት ) በክፍል አራት ትምህርታችን ላይ ደግሞ የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሠራቂ ወደ አማርኛው ስተረጉመው ሌባ የማያገኘው መዝገባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲል ደፍሮ መናገሩ ምንን የሚያሳይ ነው ? ስንል ምሕረታችን ጽድቃችን ቅድስናችን ቤዛችን በአጠቃላይ የተከፈለልን የጽድቅ ዋጋ ያለው እርሱ ውስጥ ነው ማለትን የሚያሳይ ነው ታድያ እነዚህን በኢየሱስ ውስጥ ታምቀውና ፓኬጅ ሆነው ለእኛ ለጽድቃችን ለምሕረታችን ለቅድስናችንና ለመሣሠሉት ሁሉ የተቀመጡልንን የከበሩ መዝገቦች ነው ሌባ ሊሰርቃቸው ብል ነቀዝም ላያገኛቸው የቻለው ከኢየሱስ ትንሣኤ የተነሳ እነዚህ ሁሉ ዛሬ ሞትን ድል በመንሳት በአብ ቀኝ በተቀመጠልን በኢየሱስ ውስጥ አሉ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ የዳንበትና የምንድንበት ጸጋችን ፣ የኃጢአትን ሥርየት መቀበያችን ፣ ከጨለማው ሥልጣን መዳኛችን ፣ ምሕረታችን ፣ ቤዛችን ፣ ጽድቃችን ፣ ቅድስናችን ፣ ጥበባችን ነው ማለታችን ነው ኤፌሶን 2 ፥ 8 ፣ ቲቶ 2 ፥ 11 ፤ የሉቃስ ወንጌል 7 ፥ 36 _ 50 ፤ የዮሐንስ ወንጌል 8 ፥ 1 _ 11 ፤ ሮሜ 3 ፥ 25 እና 26 ፤ ዕብራውያን 9 ፥ 22 ፤ ቆላስያስ 1 ፥ 13 እና 14 ፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1 ፥ 16 ፤ ሮሜ 9 ፥ 16 ፤ ሮሜ 3 ፥ 24 ፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 1 ፥ 30 እና 31 ፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 5 ፥ 21 ፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6 ፥ 9 _ 11 እነዚህ ጥቅሶች ስለ ኢየሱስ ማንነት የሰጠሁበትን ማብራርያዎች ግልጽ የሚያደርጉ እውነቶች ስለሆኑ በማስተዋል ያንብቡአቸው ታድያ የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ትርጉም ፦ ሌባ የማያገኘው ብል ነቀዝ የማያበላሸው መዝገባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው በማለቱ ከእነዚህ በጥቅስና በማስረጃ ካቀረብኩዋቸው የኢየሱስ ተግባሮች የተነሳ የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ እንደ ቃሉ የሆነውን እውነታ ያስቀመጠልን በመሆኑ ልባችንን በእጅጉ አረስርሶታል ይህን ያልኩበት ምክንያት አሁንም ታድያ ጥቂት ያይደሉ ሰዎች የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ በትክክል ያስቀመጠልንን እውነት ካለመረዳት የተነሳ ጽድቅና ምሕረት እንዲሁም ቤዛነትን ፍለጋ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይወጡት አቀበት የማይወርዱት ቁልቁለት የለም እና ነው ይህንን ጽድቅና ምሕረት ከመፈለግ የተነሣ ጫካ ገብተው ይደበቃሉ በዱር ምድረበዳ ይወድቃሉ ድንጋይ ተንተርሰው ዳዋ ለብሰው ይተኛሉ ሠንሠለት ይታጠቃሉ የጣፈጠ የጣመ ምግብ አይበሉም አሁንም ይህንኑ ምሕረትና ጽድቅን ለመፈለግ ሲሉ በዓላትን ያከብራሉ አሻሮ ይቆላሉ ድግስ ይደግሳሉ ለተራበ ለተጠማ አብልተንና አጠጥተን እንጸድቃለን ይላሉ የማያደርጉት ነገር የለም የተቻላቸውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ ያደርጋሉ ምሕረትና ጽድቅን ባለመከልከል ለሰው ልጆች ሁሉ በነጻ የሰጠው ፣ የኃጢአትን ሥርየት በመስጠት ኃጢአትን ይቅር ያለው ፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ቤዛ ወይንም ምትክ ሆኖ በመስቀል ላይ ሞታችንን የሞተው እንደገናም በሦስተኛው ቀን በመነሣት ወደ አባቱ ያረገውና በአባቱም ቀኝ ተቀምጦ ለእኛ የሚማልደው እንደገናም ተመልሶ የሚመጣው ሌባ ያላገኘው ብል ነቀዝም ያላበላሸው እውነተኛው መዝገባችን ኢየሱስ ግን ቤዛችን ፣ ጽድቃችንና ምሕረታችን ሆኖ በሰማይ አለ ታድያ ይህን ሁሉ ለሰው ልጆች ጥቅም የሚሰጥ መዝገብ በሰማይ የያዘና መዝገባችንም የሆነ ኢየሱስ በሰማይ እያለ ይህንኑ ጽድቅና ምሕረት ቤዛነትንም ጭምር ለማግኘት በምድር መኳተኑ ጥሻ ጉድጓድ ውስጥ መደበቁ ሰውነትን ማጎሳቆሉ መገርጣት መጠውለጉ ጥቅሙ ምን ይሆን ? ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ሲሉ አበው እንደሚተርቱ ጽድቅ ምሕረት ይቅርታ በሌለበትና በማናገኝበት ሥፍራ ጽድቅን ምሕረትን ይቅርታንና የመሣሠሉትን ሁሉ መፈለጉ አሁንም ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆንብናልና ልናስብበት ይገባል መዝገባችን ኢየሱስ በሌለበት ሥፍራ ሁሉ ጽድቅ ምሕረት ሥርየትም ሆነ ቤዛነት የለም ይህን ሁሉ ጉዳይ የያዘልን ማለትም የምሕረትን የይቅርታን የሥርየትንና የቤዛነትን መዝገብ ይዞ ሌባ ነቀዝና ብል ሳያበላሸውና ሳይሰርቀው በአብ ቀኝ የተቀመጠልን ኢየሱስ በሰማይ ነው ያለው መጽሐፍቅዱሳችን በአንድ ሥፍራ ላይ እንዲህ ሲል ይናገረናል ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው፦ ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ፥ 5 ን ይመልከቱ የእነዚህ ሰዎች ፍለጋ የተስተካከለ አልነበረም የተሰቀለውንና በመቃብር ያለውን ኢየሱስን ነበር የሚፈልጉት የማቴዎስ ወንጌል 28 ፥ 5 ነገር ግን መልአኩ ባመጣው መልዕክት አማካኝነት ፍለጋቸው ተስተካከለ ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ ? ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም ተባሉ በእርግጥም ኢየሱስ ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም ስለዚህ ኢየሱስ በሌለበት ቦታ የምንፈልገው ምንም ነገር የለም መጽሐፍቅዱሳችን አሁንም እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ይለናል ሮሜ 9 ፥ 16 ስለዚህ ተሽቀዳድመን ዋጋ ከፍለን ሮጠንና ተሯሩጠን አቀበት ቁልቁለት ጋራ ሸንተረሩን ወጥተን ወርደን የምናገኘው ምሕረት የለም ምሕረት ከሚምር ከእግዚአብሔር ስለሆነ ምሕረትን ወደሚሰጠን ወደ መዝገባችን ወደ ኢየሱስ መጥተን ንስሐ በመግባትና ሸክምንም በእርሱ ላይ በመጣል ከእርሱ ብቻ የምናገኘው ነው የማቴዎስ ወንጌል 11 ፥ 28 ጌታ እግዚአብሔር ሁላችንንም በዚህ እውነት ያግዘን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን የ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment