የትምህርት ርዕስ
ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ
ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን
ንዑስ አርዕስት
የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ………………
ወኢያእመሩ እስከ አመ መጽአ ማየ አይኅ ወአጥፍአ ኲሎ…………………
ክፍል አራት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ
ትርጉም ፦ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ሌባ የማያገኘው ብል
ነቀዝ የማያበላሸው ሳጥናችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው
( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት )
የተወደዳችሁ ወገኖች አበው መምህራን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በሙሉ ይህ የክፍል አራት ትምህርትና የማጠቃለያም ሃሳቤ ነው ዛሬ እንግዲህ እንደ መነሻ ሃሳብ አድርጌ የወሰድኩት የመጽሐፍቅዱስ ክፍል አለ እርሱም እንዲህ ይላል በመጀመርያ በግዕዙ ቃል እናገረዋለሁ ወኢያእመሩ እስከ አመ መጽአ ማየ አይኅ ወአጥፍአ ኲሎ ከማሁኬ ይከውን ምጽአቱ ለወልደ እጓለ እመሕያው ወደ አማርኛው ስተረጉመው እንዲህ የሚል ነው የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል ይለናል የተወደዳችሁ ወገኖቼ ያለማወቅ ጨለማ ትልቅ ጥፋትን ያመጣል ስለዚህ በማንኛውም የሕይወት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ባለማውቅ ማንነት ውስጥ ልንቀመጥ ፈጽሞ አይገባንም ባለማወቅ ሕይወት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ማጥፋት ብቻ ሳይሆን መጥፋትም አለ ስለዚህ አለማወቅ የሚወደድ ነገር አይደለም መጽሐፍቅዱሳችንም በትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 4 ፥ 6 ላይ
ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆን እጠላሃለሁ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ በማለት ይናገራል እውቀት በሌለበት ቦታ ያለው ነገር ሁልጊዜ ጥፋት ነው በመሆኑም የማያውቅን ሰው ጌታ እግዚአብሔር ካህን
እንዳይሆን ይጠላል የእግዚአብሔርን ሕግ ስናውቅ የእግዚአብሔር እውቀት ይኖረናልና ትክክለኛ ካህን መሆን እንችላለን ከዚያ ውጪ ግን አይሆንም በነህምያ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ቊጥር 8 ላይ የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፥ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር ይለናል ስለዚህ ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያውቅና የሚያስተምር ትክክለኛ ካህን ነበር ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃል የተማረ ስለነበር የሚነበበውን ያስተውል ነበር ይለናል ካልተማርንና ካላወቅን ሌሎችን ማሳወቅ አንችልም ያልተማረ ሕዝብ ደግሞ ያልተማረ ነውና የሚነበብለትን ማስተዋል አይችልም ስለዚህ ቅዱሱን ማወቃችንን ማስቀደም ከሁላችን የሚጠበቅ ጉዳይ ነው የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነውና ምሣሌ 9 ፥ 10 ወገኖቼ ስናውቅ እና ስንረዳ ነው ያለማወቅ ወራት ከእኛ የሚያልፍልን ካላወቅን ግን እዚያው ነን ጥፋትም መጥቶ ይወስደናል ለዚህ ነው መጽሐፍቅዱሳችን አሁንም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17 ፥ 30 ላይ እንዲህ የሚለን በመጀመርያ በግዕዙ ቃል
እናገረዋለሁ ወዘቀዲሙሰ መዋዕለ ኢያእምሮ
አሰሰለ እግዚአብሔር ወይእዜ ባሕቱ አዘዘ ለኲሉ ሰብእ ይነስሑ በኲለሄ ወደ አማርኛው ስተረጉመው እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል ቀን ቀጥሮአልና እያለ ይናገራል የተቀጠረው ቀን ደግሞ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሳቱ ሁሉን አረጋግጦአል ይለናልና ያ ቀን
ጌታ እግዚአብሔር በዓለሙ ላይ በጽድቅ የሚፈርድበት ቀን ነው እነዚህን የእግዚአብሔር ቃል ሃሳቦች ዘርዘር አድርጌ የተናገርኩበት ምክንያት ስለ እውቀት በተለይም እግዚአብሔርን ስለማወቅ ያለን ግንዛቤ እንዲጨምርና ያለማወቅ ወራታችን አልፎ እኛም በየቦታችን ንስሐ እንድንገባ ነው ንስሐ ደግሞ የማወቅና የግንዛቤ ምልክት እንጂ የሽንፈት ምልክት አይደለም ሰው ንስሐ የሚገባው ሲያውቅ ነው ካላወቀ ግን ይጠፋል እንጂ የንስሐ እድል የለውም ማለትም ለንስሐ አይበቃም ወደ መነሻው ታሪካችን ስንመጣም በኖህ ዘመን የነበሩ ሰዎች ትልቁ ችግራቸው ያለማወቅ ችግር ነው ይሄ ያለማወቅ ችግራቸው የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም እስኪወስድ ድረስ አደረሳቸው ታድያ እነዚህ ሕዝቦች ያላወቁት እንዳያውቁ ሆነው ስለተፈጠሩ ነው ?
ወይስ ማወቅን እንደ ትልቅ ኃጢአት ስለቆጠሩት ?
አንዳንዴ እኮ በእኛ ኅብረተሰብ ማወቅ እንደ ኃጢአት ተቆጥሮ እንዲህ እንዲህ ይታሰባል ስለዚህ የሚያውቅ ሰው ብዙ አይወደድም እንደገናም በማኅበረሰባችን ዘንድ ብዙ እንድናውቅ አንገፋም አንበረታታም ምን ያደርግልሃል ? ይበቃሃል ይቅርብህ ብዙ ርቀህ አትሂድ አትመራመርና የመሳሰሉትን ስንባል ኖረናል ዛሬም እየተባልን አለን ይህ ግን ሕይወታችንን በብዙ የጎዳ ትውልድን ባለማወቅ ጨለማ ያስቀመጠና ያደናቆረ የሰይጣን ሃሳብ እንጂ ከእግዚአብሔር የሆነ ሃሳብ አይደለም እግዚአብሔር እንድናውቅ አውቀንም እንድንድን ይፈልጋል የማያውቅን ሰው እግዚአብሔር እንደውም አይወድም ከላይ እንደጠቀስኩትም አገልጋዩም አያደርገውም በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍቅዱሳችንን ይበልጥ ወደ ውስጥ ገብተን በማንበብና በማጥናት ይህንን እውነት ከቃሉ ሃሳብ ትገነዘቡ ዘንድ ይህን ትምህርት ለምትከታተሉ ሁሉ በትሕትናና በፍቅር ሆኜ ለማሳሰብ እወዳለሁ እነዚህ በኖህ ዘመን የነበሩ ሰዎች የጥፋት ውኃ መጥቶባቸው ሁላቸውንም የመውሰዱ ጉዳይ እንዲያውቁ ሆነው ስላልተፈጠሩ ወይንም አለማወቅ ዕድል ፈንታቸውና የወጣባቸው ዕጣ ስለሆነ ሳይሆን እንዲያውቁ ፈቃደኞች ስላልሆኑና ለማወቅም ጆሮ ስላልሰጡ ወይንም በሌላ አነጋገር ጆሮ ዳባ ልበስ ስላሉ ነው እግዚአብሔርማ የሚያሳውቃቸውንና ወደ መርከቡም እንዲገቡ የሚጋብዛቸውን የጽድቅ ሰባኪ ኖህን ልኮላቸው ነበር 2ኛ ጴጥሮስ 2 ፥ 5 ይህንንም የጽድቅ ስብከት ሰምተው ወደ መርከቡ በመግባት ከጥፋት ውኃ ከሚድኑ ይልቅ ማግባትንና መጋባትን መብላትንና መጠጣትን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርገው ወሰዱ በዚህም ምክንያት በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል ተብለው አሁን ዘመን ላይ ሆነን የኢየሱስን መምጣት ለምንጠባበቀው ለእኛ ሳይቀር የመጣፋት ምሣሌ ሆነው ቀረቡልን የማቴዎስ ወንጌል ምራፍ 24 ፥ 38 _ 40 ወገኖቼ ወደ መሠረታዊው ወደ እግዚአብሔር ቃል እውነት ስንመጣ ጌታ እግዚአብሔር ማግባትንና መጋባትን መብላትንና መጠጣትን የሚቃወም ሆኖ አይደለም ማግባትና መጋባት መብላትና መጠጣት ግን የሰዎች የመጀመርያ ጉዳያቸውና ተቀዳሚ ምርጫቸው ሊሆን አይገባም መጽሐፍቅዱሳችን በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቅ መልስ ይሰጠናል በ1ኛ ቆሮንቶስ 7 ፥ 29 _ 31 ላይ ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና ይለናል የተወደዳችሁ ወገኖቼ እዚህ ላይ አንድ ነገር ማስተዋል ያለብን በኖህ ዘመን ጠፍቶ ያለ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ በሙሉ ይህንን የተጻፈ እውነት ካልተገነዘበ ሕይወት ለእርሱ የሚመስለው ማግባት መጋባት መደሰትና የመሣሠሉት ነገር ነው ነገር ግን ለእኛ ሕይወት ይሄ ብቻ እንደሆነ ካሰብን ትልቅ ውድቀትና ኪሣራ ውስጥ እንደሆንን ልናውቅ ይገባል በኖህ ዘመን ለነበሩ ሕዝቦች ትልቁ እሴታቸው ማግባት መጋባት መብላትና መጠጣት ስለነበረ ይህ ሁኔታቸው ለንስሐ እንኳ ሳይቀር እድል ሳይሰጣቸው ኪሳራና ጥፋት ውስጥ ጣላቸው ስለዚህ ወገኖቼ አገባን ተጋባንም በላን ጠጣንም ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ዛሬውኑ መነሣት ይገባናል 1ኛ ቆሮንቶስ 10 ፥ 31 ከትዳራችን ከማግባት ከመጋባታችን ከመብላት ከመጠጣታችንና በዚችም ዓለም ከመጠቀማችን በፊት እግዚአብሔርን ልናስቀድም ያስፈልጋል የሉቃስ ወንጌል 14 ፥ 15 _ 24 ፣ የማቴዎስ ወንጌል 6 ፥ 24 _ 33 እነዚህን ጥቅሶች መጽሐፍቅዱስዎትን ከፍተው ያንብቡአቸው ዘንድ እጋብዛለሁ ወዳጆቼ ሆይ ወደ እውነተኛው መርከብ ቀድመን መግባትና መዳን ከማንኛውም ሰው ይጠበቃልና ያልዳንን ከሆንን በመጀመርያ በዚህ ምድር ካለ ከሁሉና ከማንኛውም ነገር በፊት ለቃሉ በመታዘዝ ወደ እውነተኛው መርከባችን ወደ ኢየሱስ ገብተን መዳን ይሁንልን ለምን ስንል የዚህች ዓለም መልኳ ኃላፊ ነውና በዚህች ዓለም ባገኘነው ባተረፍነውም ነገር ጠልቀን መቅረት የለብንም በሉቃስ ወንጌል በምሣሌ የቀረበልን ያ ባለጸጋ ሰው ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን አከማቻለሁ ነፍሴንም አንቺ ነፍሴ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ ዕረፊ ብዪ ጠጪ ደስ ይበልሽ በማለቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምን ትዕዛዝ እንደወጣበት የክፍሉን መጽሐፍ አውጥተን በመመልከት መረዳት እንችላለን የሉቃስ ወንጌል 12 ፥ 13 _ 21 ወደ መርከቡ ገብተን ድነን ከሆነ ደግሞ ከዳንበት መርከብ ላለመውጣት ውሳኔ አድርገን በዚያው በመርከቡ በኢየሱስ ውስጥ መጽናት እና ከፍጻሜው ወደብ ላይ መድረስ የሁላችንም ጸሎት ልመናና ምልጃም ሊሆን ይገባል የተወደዳችሁ ወገኖች የክፍል አራት ትምህርቴን በዚሁ አጠቃልያለሁ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን በሚለው ዋና የትምህርት አርዕስት እስከ ክፍል አራት ድረስ የቀጠለው ትምህርት በዚሁ የተደመደመ ሲሆን ከክፍል አንድ ጀምሮ እስከ ክፍል አራት ቀጥለው ፖስት የተደረጉትን ሁሉንም ትምህርቶች ተከታትላችሁ ካነበባችሁ ፣ ከሰማችሁና ከተጠቀማችሁ በኋላ ለሌሎች ሊጠቀሙ ለሚፈልጉ ሁሉ ሼር እንድታደርጉትና እንድታስተላልፉት ከትልቅ አክብሮትና ትሕትና ጋር እጠይቃለሁ ጌታ እግዚአብሔር የተማርናቸውን ቃሎቹን በልቡናችን አሳድሮ በትክክለኛው የቃሉ መንገድ
ይምራን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
የJoshua Breakthrough Renewal Teaching
and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
No comments:
Post a Comment