Monday, November 23, 2015
M2U00055 መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሠራቂ ሌባ የማያገኘው መዝገባችን ክፍል ሁለት መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ትርጉም ፦ ሌባ የማያገኘው ብል ነቀዝ የማያበላሸው መዝገባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት ) የተወደዳችሁ ወገኖች በክፍል አንድ ትምህርታችን መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በማለት በግዕዙ ቃል ይናገራልና ወደ አማርኛው ስተረጉመውም ሌባ የማይሰርቀው ብል ነቀዝ የማያበላሸው መዝገባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ሲል የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ነግሮናል ይህንንም ሃሳብ ከማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ቊጥር 19 እስከ 21 ከተጻፈው ሃሳብ ጋር በማገናዘብ ብል ነቀዝ የማያበላሸው አንዱና እውነተኛው መዝገባችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ከጠቆምኩ በኋላ ይህንን ሃሳብ በቀጣይነትና በተከታታይነት ከማቅረባችን በፊት በቀጥታ መዝገብ የሚለውን ጥሬ ቃል አንስተን በቀላሉ ስንት ዓይነት መዝገብ እንዳለ የሚጠቁመንን የእግዚአብሔር ቃል መረጃ በማቅረብ የመጀመርያውን የመዝገብ ዓይነት ተመልክተናል እርሱም : ----------------- 1ኛ _ የእግዚአብሔር የተለየ ሀብት ያለበት ሥፍራን የሚያሳይ መዝገብ ነው ብለናል በመቀጠልም ሁለተኛውንና ከዚያም የሚቀጥሉትን እንመለከታቸዋለን 2ኛ _ ሁለተኛው መዝገብ ሰዎች በየስማቸው የሚቆጠሩበት መዝገብ ነው በዘመኑ አነጋገር አቴንዳንስ መቆጣጠርያ ማለትን ያመለክታል በአንድ ስብሰባ የነበረን ሕዝብ ሰዎች በትክክል ማወቅ ሲፈልጉ የመቆጣጠርያ መዝገብን አዘጋጅተው በመመዝገብ የሚከታተሉበት መንገድ ነው እንደገናም በተለያዩ ሕጋዊ አካላት ባሉበት ሥፍራዎች ሁሉ ሕጋዊ የሆኑ የመቆጣጠርያ መዝገቦች አሉ ታድያ ይህ የመቆጣጠርያ መዝገብ ሕጋዊ ሰነድ የያዙ ጉዳዮችን ማለትም ሀብትንና ንብረትን ሕጋዊ የመኖርያ ቤቶችንና የመገበያያ ሱቆችን ፣ ሸቀጦችን ፣ የንግድ ፈቃዶችን የሰዎችን ኃይል ገንዘብን እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ልዩ ልዩ ቊሳቊሶችን ሁሉ ያካተተ ሊሆን ይችላልና መዝገብ የሚለውን ሃሳብ እንዲሁ በቀላሉ የምናየው ነገር አይደለም ወደ መጽሐፍቅዱሳዊ የትምህርት ክፍሌ ስመጣም በ1ኛ ዜና 5 ፥ 7 _ 9 ላይ ወንድሞቹ በየወገናቸው የትውልዶቻቸው መዝገብ በተቈጠረ ጊዜ አንደኛው ኢዮኤል ዘካርያስ፥ እስከ ናባውና እስከ በኣልሜዎን ድረስ በአሮዔር የተቀመጠው የኢዮኤል ልጅ የሽማዕ ልጅ የዖዛዝ ልጅ ቤላ በገለዓድ ምድር እንስሶቻቸው በዝተው ነበርና በምሥራቅ በኩል ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምድረ በዳው መግቢያ ድረስ ተቀመጠ ይለናል በ1ኛ ዜና 7 ፥ 9 ላይም በየትውልዳቸው መዝገብ የተቈጠሩ፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ሀያ ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ በማለት ይናገራል በ1ኛ ዜና 27 ፥ 24ም ላይ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ መቍጠር ጀመረ፥ ነገር ግን አልፈጸመም፤ ስለዚህም በእስራኤል ላይ ቍጣ ሆነ፥ ቍጥራቸውም በንጉሡ በዳዊት መዝገብ አልተጻፈም ይላል ከዚህም ሌላ በሐዲስ ኪዳን ኢየሱስ ከመወለዱ በፊትም መጻፍ ነበረና ዮሴፍ ፀንሳ ከነበረችው ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ በማለት ይናገርና በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል ወእምዝ እንከ እንዘ ሀለዉ ህየ በጽሐ ዕለተ ወሊዶታ ወወለደት ወልደ ዘበኲራ ወአሰረቶ መንኮብያቲሁ ወአስከበቶ ውስተ ጎል እስመ አልቦሙ መካነ ውስተ ማኅደሮሙ ትርጉም በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው በማለት ይናገራል የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ፥ 1 _ 7 የተጻፈውን ይመልከቱ 3ኛ _ ሦስተኛው መዝገብ ደግሞ የእግዚአብሔር ቤት መዝገብ እና የንጉሥ ቤት ነው ይህንንም በመቀጠል እንመለከተዋለን 2ኛ ዜና 16 ፥ 2 ላይ በተጻፈው ሃሳብ መሠረት አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከንጉሡ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ ወስዶ በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረው ቃል ኪዳን በእኔና በአንተ መካከል ይሆናል፤ እነሆ ብርና ወርቅ ሰድጄልሃለሁ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ ብሎ በደማስቆ ወደተቀመጠው ወደ ሶሪያ ንጉሥ ወደ ወልደ አዴር ሰደደ ይልና ቊ 7 _ 14 በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ በሶሪያ ንጉሥ ታምነሃልና፥ በአምላክህም በእግዚአብሔር አልታመንህምና ስለዚህ የሶሪያ ንጉሥ ጭፍራ ከእጅህ አምልጦአል ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ጭፍራ አልነበሩምን ? በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና አሁንም ስንፍና አድርገሃል፥ ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ሰልፍ ይሆንብሃል አሳም በባለ ራእዩ ላይ ተቈጣ፤ ስለዚህም ነገር ተቈጥቶአልና በግዞት አኖረው፤ በዚያን ጊዜም አሳ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎችን አስጨነቀ የአሳም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል በነገሠም በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት አሳ እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በታመመ ጊዜ ባለ መድኃኒቶችን እንጂ እግዚአብሔርን አልፈለገም አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቱ በተሞላ አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የመቃብር ወግ አደረጉለት በማለት ይናገራል በ2ኛ ዜና 36 ፥ 18 እና 19 ላይም የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃ ሁሉ ታላቁንና ታናሹን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዝገብ፥ የንጉሡንና የአለቆቹን መዝገብ፥ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ፥ አዳራሾችዋንም በእሳት አቃጠሉ፥ መልካሙንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፉ በማለትም ይናገራል 4ኛ _ አራተኛው መዝገብ በኃጢአት የሚገኝ መዝገብ ነው በምሳሌ 10 ፥ 2 ላይ በኃጢአት የተገኘ መዝገብ ጥቅም የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ያድናል ይለናል ምሳሌ 15 ፥ 6 ላይ ደግሞ በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፤ የኀጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው ይላል ምሳሌ 21 ፥ 6 ፣ 20 በሐሰተኛ ምላስ መዝገብ ማከማቸት የሚበንን ጉም ነው፤ ይህን የሚፈልጉ ሞትን ይፈልጋሉ ፣ የከበረ መዝገብና ዘይት በጠቢብ ሰው ቤት ይኖራል፤ አእምሮ የሌለው ሰው ግን ይውጠዋል ይለናል 5ኛ _ በኃጢአት በተገኘ መዝገብ እግዚአብሔር የሚወስደው እርምጃ አለ በኤርምያስ 15 ፥ 13 ላይ በዳርቻህ ሁሉ ስላለ ኃጢአትህ ሁሉ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ለመበዝበዝ በከንቱ እሰጣለሁ ብሎአል በኤርምያስ 17 ፥ 3ም ላይ በሜዳ ያለው ተራራዬ ሆይ፥ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችም ስለ ኃጢአት በድንበሮች ሁሉ ለመበዝበዝ እሰጣለሁ በማለት ይናገራል በኤርምያስ 20 ፥ 5 ላይ የዚህችንም ከተማ ባለጠግነት ሁሉ ጥሪትዋንም ሁሉ ክብርዋንም ሁሉ የይሁዳንም ነገሥታት መዝገብ ሁሉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እነርሱም ይበዘብዙአቸዋል ይዘውም ወደ ባቢሎን ያፈልሱአቸዋል ይላል በኤርምያስ 48 ፥ 7 ላይ ደግሞ በሥራሽና በመዝገብሽ ታምነሻልና አንቺ ደግሞ ትያዢያለሽ፤ ካሞሽም ከካህናቱና ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ይማረካል ይለናል በኤርምያስ 49 ፥ 4 እና 5 ማን ይመጣብኛል ብለሽ በመዝገብሽ የታመንሽ አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፥ በሸለቆችሽ፥ ውኃ በሚያረካቸው ሸለቆችሽ፥ ስለ ምን ትመኪያለሽ፧ እነሆ፥ በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ ፍርሃትን አመጣብሻለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እያንዳንዳችሁም በፊታችሁ ወዳለው ስፍራ ትሰደዳላችሁ፥ የሚሸሹትንም የሚሰበስብ የለም በማለትም ይናገራል በኤርምያስ 50 ፥ 37 ሰይፍ በፈረሶቻቸውና በሰረገሎቻቸው ላይ በመካከልዋም ባሉት በልዩ በልዩ ሕዝብ ሁሉ ላይ አለ፥ እነርሱም እንደ ሴቶች ይሆናሉ፤ ሰይፍም በመዝገብዋ ላይ አለ ለብዝበዛም ይሆናል ይላል በኤርምያስ 51 ፥ 13 አንቺ በብዙ ውኃ አጠገብ የተቀመጥሽ፥ በመዝገብም የበለጠግሽ ሆይ፥ እንደ ስስትሽ መጠን ፍጻሜሽ ደርሶአል ይለናል በትንቢተ ናሆም 2 ፥ 9 መዝገብዋ መጨረሻ የለውምና፥ የከበረውም የዕቃዋ ሁሉ ብዛት አይቈጠርምና ብሩን በዝብዙ፥ ወርቁንም በዝብዙ በማለት ይናገራል ለዚህም ነው እንግዲህ በኃጢአት በተገኘ መዝገብ እግዚአብሔር የሚወስደውን እርምጃ ሚክያስ ስለሚያውቅ በውኑ በኃጢአተኛ ቤት የኃጢአት መዝገብ፥ የተጸየፈም ውሸተኛ መስፈሪያ ገና አለ ይሆን ? በማለት በጥያቄ መልክ ያስቀመጠልን ትንቢተ ሚክያስ 6 ፥ 10 መዝገብን በተመለከተ እንግዲህ ለእያንዳንዳችንም መዝገብ አለንና መዝገባችን በየትኛው በኩል ሊሆን እንደሚገባው እንድናስብ የሚያደርገን ትምህርት ነው ታድያ በዚህ ትምህርት ውስጥ እራሳችንን እያየን እኔስ ከየትኛው መዝገብ ውስጥ ነኝ በማለት ትክክለኛውን መንገዳችንን ልናይና የሕይወት ሥርዓት አካሄድ የያዘውን መዝገባችንንም ልናስተካክል ይገባል በመሆኑም ይህንን ትምህርት የተከታተልን ሁላችን በተለይም በኃጢአት በሚገኝ መዝገብ ምክንያት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚወሰደውን እርምጃ የከፋ ያደርገዋልና ሁላችንም ራሳችንን መጠበቅ እንዲሆንልን ፣ በእግዚአብሔር ቤት ላለ መዝገብም በብዙ መጠንቀቅ እንዳለብን የሚናገር ፣ የሚያስተምርና የሚመክርም ትምህርት ነው በዚህ ትምህርት ደግሞ ሁላችሁም እንደምትጠቀሙ እንደምትባረኩበትና እንደምትጽናኑበትም አምናለሁ ጌታ እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment