Monday, November 30, 2015
M2U00061 መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሠራቂ ሌባ የማያገኘው መዝገባችን ክፍል ሰባት መዝገብነ ዘኢይረክቦ ሰራቂ ወኢያማስኖ ፃፄ ወቊንቊኔ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ትርጉም ፦ ሌባ የማያገኘው ብል ነቀዝ የማያበላሸው መዝገባችን ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ( ምንጭ መጽሐፈ ሰዓታት ) መዝገብን በተመለከተ አሁንም ከእግዚአብሔር ቃል የምናየው እውነት አለ ሰዎች ሕይወታቸውን ለጌታ ለኢየሱስ በሚሰጡበት ጊዜ የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲም እንደነገረን ብል ነቀዝ ሌባም ሊሰርቀው የማይችለውን መዝገባችን ኢየሱስንና በእርሱም መዝገብ ውስጥ ያለውን ደኅንነት የኃጢአት ሥርየት ምሕረትና ይቅርታ የዘለዓለምንም ሕይወት ባገኙ ሰዎች ውስጥ ጌታ የሚያስቀምጠው መዝገብ አለ በኦርቶዶክስ ወንጌል የገባቸው አባቶቻችን ይህንን ሁኔታ እንዲህ ሲሉ ያስቀምጡታል በሀብተ መንፈስቅዱስ የተገኘ ክህሎት ይሉታል በመንፈስቅዱስ ሀብት የተገኘ ችሎታ ማለትን የሚያሳይ ነው በመሆኑም የእነዚህ አባቶች አባባል ትክክልና መጽሐፍቅዱሳዊም ነው ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍቅዱስን ከመሠረቱ ስንመለከት እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን 2ኛ ቆሮንቶስ 4 ፥ 7 _ 10 ይህ ቃል ታድያ እነዚህ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ከተናገሩት ቃል ጋር የተያያዘ ነው እኛ ሸክላ ስንሆን ሽክላ በሆነው በእኛ ውስጥ የተቀመጠው መዝገብ ግን በሀብተ መንፈስቅዱስ የተገኘ ክህሎት ነው ስለዚህ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምርም ይስበክም ተአምራታዊ ኃይልና ፈውስ ያካሂድም ትንቢት ይናገር ይዘምርም መዝገቡ የጌታና በሀብተ መንፈስቅዱስ የተገኘ ክህሎት ነው ሌላው ቀርቶ ሰዎች ምድራዊ ችሎታ ኖሮአቸው በተሰጣቸው ችሎታ የሚሰማሩት ያንን ችሎታውን እግዚአብሔር ስለሰጣቸው ነው ከእነርሱነታቸው የሆነ ግን ምንም ነገር የለም እነዚህ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች በሀብተ መንፈስቅዱስ የሚመጣውን ክህሎት በሀብተ መንፈስቅዱስ የሚመጣ በሰዎች ውስጥ ያለ ክህሎት ወይንም በአማርኛው ችሎታ ነው ማለታቸው አንደኛው ሊናገሩበት የፈለጉት ሃሳብ ከሰው ችሎታ ውጪ የሆነውን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ያለውን መዝገብ ሊጠቁሙን ፈልገው ሲሆን ሁለተኛው ሃሳብ ግን በ1ኛ ቆሮንቶስ 12 ፥ 4 _ 11 በተጻፈው ቃል መሠረት ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል ይለናልና ይህንንም ሃሳብ ለመግለጽ ነው የጥንቷ ኦርቶዶክሳዊትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በመንፈስቅዱስ አሠራርም የምታምን ቤተክርስቲያን ናትና ከዚህ የተነሳ በትርጓሜ ወንጌልዋ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ በሐዋርያት ላይ የመጣውን ርደተ መንፈስቅዱስ ማለትም የመንፈስቅዱስን መውረድ አስመልክቶ የተናገረችውን ለአብነት ያህል ጥቂቱን ማቅረብ የፈለግሁት መጽአ ግብተ እምሰማይ ድምጽ ከመ ድምጸ አውሎ ነፋስ ከወደ ሰማይ እንደ አውሎ ነፋስ ያለ ድምጽ ነጉዶ ተሰማ አለ መንፈስቅዱስ ነው ነፋስ ረቂቅ ነው መንፈስቅዱስ ረቂቅ ነውና ነፋስ ኃያል ነው መንፈስቅዱስም ኃያል ነውና ነፋስ ፍሬውን ከገለባ ይለያል መንፈስቅዱስም ጻድቃንን ከኃጥአን ይለያልና ነፋስ በምልዓት ሳለ አይታወቅም ባሕር ሲገስጽ ነፋስ ሲያናውጥ ነው እንጂ መንፈስቅዱስም በምልአት ሳለ አይታወቅም ቋንቋ ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጉም ነውና ነፋስ መንቅሒ ነው መንፈስቅዱስም መንቅሒ ነው መንቅሒ ማለት የሚያነቃ ማለት ነው ነፋስ መዓዛ ያመጣል መንፈስቅዱስም መዓዛ ጸጋን ያመጣል ( የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ፥ 2 ትርጓሜ ወንጌልን ይመልከቱ ) ታድያ መንፈስቅዱስ የሚያነቃ ሆኖ መዓዛ ጸጋን ያመጣል ምሥጢርን ያስተረጉማል ማለት በ1ኛ ቆሮንቶስ 12 ፥ 4 _ 11 በተጠቀሰው ቃል መሠረት ለጥቅም የሚሰጠውን የመንፈስቅዱስን መግለጥ የሚያስታውሰን ነው ስለዚህ ክሂሎት እንግዲህ የሀብተ መንፈስቅዱስ ውጤት ስለሆነ ማለትም ችሎታ የመንፈስቅዱስ ሃብት ነውና የሚገኘው ከመንፈስቅዱስ ብቻ ነው ነገር ግን አንዳንድ መድኃኒት ቀማሚዎችና አዋቂ ነን ባዮች ክሂሎት ወይም ችሎታን እንሰጣለን ፣ ትምህርት እንዲገባችሁ እናደርጋለን ፣ ንግዳችሁ ፣ ሥራችሁ ፣ ትዳራችሁ የሰመረ ይሆናል ከሰው በላይ ትሆናላች ማስፈራት በላያችሁ ይሆናል ፣ ግርማ ሞገስንና የመሣሠሉትን እንሰጣለን ዕድል ፈንታችሁንም በዚህ እንነግራለን እያሉ ክታብ ይጽፋሉ መድኃኒት ቀምመው ይሰጣሉ ሲያስፈልግም ያጠጣሉ ያስጐነጫሉ ይህንን ግን የእግዚአብሔር ቃል አይደግፈውም መንፈስቅዱስም ይቃወመዋል ይህ የሰይጣን ሥራ ነው በመንፈስቅዱስ የምታምን ቤተክርስቲያን ክርስቶስንም በማመን ከእግዚአብሔር ዳግመኛ መወለድን ያገኘች ቤተክርስቲያን ይህንን ሰይጣናዊ አሠራር በጽኑ ትቃወማለች መጽሐፍ ሲናገር ወንድ ልጁን ሴት ልጁን በእሳት የሚያሳልፍ፥ ምዋርተኛም፥ ሞራ ገላጭም አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፤ ስለዚህም ርኵሰት አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ያሳድዳቸዋል አንተ ግን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ሁን የምትወርሳቸው እነዚህ አሕዛብ ሞራ ገላጮችንና ምዋርተኞችን ያዳምጣሉ፤ አንተ ግን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ከልክሎሃል ይላል ዘዳግም 18 ፥ 10 - 14 እንደገናም እርሱም፦ የሚጮኹትንና ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሉአችሁ ጊዜ፥ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን ? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን ? ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም ይለናል ትንቢተ ኢሳይያስ 8 ፥ 19 እስከ 21 በመሆኑም ይህ ድርጊት የሙታን ሳቢና የጠንቋይ የመናፍስት ጠሪነት ድርጊት ነው እኛ ክርስቲያኖች ጠይቁ ስንባል መጠየቅ ያለብን በተጻፈልን ቃል መሠረት አምላካችንን ነው እንደገናም ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም ተብለናልና ሕጉና ምስክሩ ደግሞ ንጋትን የሚያመጣልን ቃሉ ስለሆነ መሄድ የሚገባን ወደ ቃሉ ነው ወደነዚህ ሰዎች መሄድ ግን እንደ ንጉሥ ሳኦል ለጠላት ተላልፎ መሰጠት ነው ንጉሥ ሳኦል ወደመናፍስት ጠሪ ቤት በመሄዱ ለጠላት ተላልፎ የተሰጠ ነበረ 1ኛ ሳሙኤል 28 ፥ 8 _ 25 እንደ እግዚአብሔር ቃል ያልሆነ ፣ ቃሉም የሌለበትን ማንኛውንም ነገር መቀበል የለብንም መናፍስት ጠሪና ጠንቋይን እንድንጠይቅ ወደ እነርሱም እንድንሄድ መጽሐፍቅዱሳችን አይነግረንም እንደገናም ብርሃን ከጨለማ ጋር ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ኅብረትና መስማማት የለውም 2ኛ ቆሮንቶስ 6 ፥ 14 _ 18 በመሆኑም እግዚአብሔር በሌለበትና በማይፈቅደው ነገር ውስጥ ገብተንና በሰይጣን ውስጥ ተጥለን የጠላት መጫወቻ ከምንሆን ክሂሎት ወይም ችሎታ የመንፈስቅዱስ ሃብት ነውና ሕይወታችንን ለጌታ ለኢየሱስ በመስጠት ደኅንነትን አግኝተን ከመንፈስቅዱስ የሆነውን ክህሎት በየጊዜው ከራሱ ከባለቤቱ ከእግዚአብሔር በመቀበል በእግዚአብሔርም እርዳታ ሥር ተጠልሎ መኖር ለሁላችንም የተገባ ነገር ነው ከጠንቋዮች ምክር ከሰይጣን እስራትና ትብታብ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሕዝባችንን ይፍታ ይጠብቅልን ለተጨማሪ ማስረጃ እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡአቸው ዘሌዋውያን 19 ፥ 31 ፤ የማቴዎስ ወንጌል 8 ፥ 16 እና 17 ፤ የማቴዎስ ወንጌል 10 ፥ 1 ፤ የማርቆስ ወንጌል 6 ፥ 7 ፤ ራዕይ 18 ፥ 2 የተወደዳችሁ ወገኖች ትምህርቴን በዚህ እጠቀልላለሁ ሌባ የማይሰርቀው መዝገባችን በሚል አርዕስት ከክፍል አንድ እስከ ክፍል ሰባት የተዘጋጀው ትምህርት በዚሁ ተጠቃሎአል እንግዲህ እነዚህን ከክፍል አንድ እስከ ክፍል ሰባት የተለቀቁትን ትምህርቶች በሚገባ ከተከታተላችኋቸው በኋላ ለሌሎችም ሊጠቀሙ ለሚችሉ ሁሉ ሼር እንድታደርጉ በጌታ ፍቅር ለማሳሰብ እወዳለሁ ጌታ ዘመናችሁን ይባርክ የ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment