Sunday, November 8, 2015
M2U00035 የትምህርት ርዕስ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ክፍል ሁለት በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የተወደዳችሁና የተከበራችሁ ብፁአን አባቶች አበው መምህራን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሕዝበ እግዚአብሔር ምዕመናን የክፍል ሁለት ትምህርታችንን አሁን እንቀጥላለን የእግዚአብሔር ጸጋና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ የሚለውን ሃሳብ አንስተን ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የተባለበትን ምክንያት መጽሐፍቅዱሳዊ ማስረጃ በመስጠት ማብራራታችን ይታወሳል ዛሬ ደግሞ ከዚሁ የቀጠለውን ሃሳብ እንመለከታለን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕበል ብቻ ሳይሆን ፈታኙም ቀርቦ ፈታኝ የሆኑ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን አንስቶበታል በመጨረሻ ግን ሂድ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው ያን ጊዜ ዲያብሎስ ተወው መላዕክትም ቀርበው ያገለግሉት ነበር በማለት የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል የማቴዎስ ወንጌል 4 ፥ 1 _ 4 እንደገናም የሕግ መምህራን ፈሪሳውያንም ሊፈትኑት ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ወደ እርሱ ቀርበዋል በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 ቊጥር 1 _ 11 በተጻፈው ቃል መሠረት ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርስዋን አቁመው መምህር ሆይ ይህቺ ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች ሙሴም እንደዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ ? አሉት የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ ኢየሱስ ግን ጎንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው ደግሞም ጎንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንዳንድ እያሉ ወጡ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ ከሳሾችሽ የታሉ የፈረደብሽ የለም በማለት ኢየሱስ እንደማይፈርድባት ከነገራት በኋላ ሂጂ ደግመሽም ኃጢአት አትሥሪ ሲል ያሰናበታት ታድያ ኢየሱስን ብዙ ነገሮች መልካቸውን እየለወጡ የቀረቡት እንኳ ቢሆኑም ነገር ግን የእኛ ጌታ ለቀረበለት ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽን የሚሰጥ ጌታ ነውና ሁሉም አንዳንድ እያሉ እስኪወጡ ድረስ እንደ አመጣጣቸው መልሷቸዋል ኢየሱስ ነገሮችንም ሆነ ሁኔታዎችን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ እንዲሆኑለት እና እንዳይቀርቡትም አትቅረቡኝ ሲል ሰዎችን ያራቀና ያስፈራራ ዛሬም ላይ የሚያርቅ የሚያስፈራራ አምላክ አይደለም ማንኛውም ነገር በየትኛውም መንገድ ይምጣ ሁሉንም እንደየ አመጣጡ በመጣበት አኳኋን ልክና መልክ ሰጥቶ የአቅምንም ልክ አሳውቆ በተገቢ ሁኔታ የሸኘና የሚሸኝም ጌታ ነው ከዚህም ሌላ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 22 ቊጥር 15 _ 22 ላይ የተጻፈልንን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ልጨምር እወዳለሁ የምንባቡም ክፍል እንዲህ ይላል ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ ደቀመዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ላኩበት እነርሱም መምህር ሆይ እውነተኛ እንደሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን ለማንም አታደላም የሰውን ፊት አትመለከትምና እንግዲህ ምን ይመስልሃል ? ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ? ወይስ አልተፈቀደም አሉት ወገኖቼ ታድያ እዚህ ላይ የኢየሱስስ መልስ ምን ነበር ? ተፈቅዶአል ወይንም አልተፈቀደም የሚሉ መልሶችን የሰጠ ይመስላል ? ወይስ ሌላ መልስ ነበረው ጌታችን ኢየሱስ ለዚሁ ጉዳይ መልስ ከመስጠቱ በፊት ጥያቄዎቹ በነገር እርሱን ለማጥመድ የመጡ ጥያቄዎች መሆናቸውን ገና ከመነሻ ሃሳባቸው እያሞጋገሱ ቀርበው ሲጠይቁት አውቋቸዋል ስለዚህ እርሱም መልስ ሲሰጥ ተፈቅዶአል ወይም አልተፈቀደም ያለ ሳይሆን እርሱ ያላቸው እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ በማለት ነው መልስ የሰጣቸው በመሆኑም እነርሱ በፈተና ሊያጠምዱት ወደ እርሱ ተጠግተው ካቀረቡለት ጥያቄ ይልቅ የኢየሱስ መልስ የበለጠ እና እጅግም አስደናቂ የሆነ ነበር የክፍል ሁለት ትምህርቴን ስደመድም እንግዲህ እነዚህን ሁሉ ጥቅሶች ያነሣሁበት ትልቁ ምክንያቴ የመጽሐፈ ሰዓታት ደራሲ ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ በመሆኑ ወደ አማርኛው ስተረጉመው ማዕበል የማይቀርበው መርከባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚለውን ትርጉም ይሰጠናልና በዚያን ዘመን ኢየሱስ በነበረበት መርከብ ውስጥ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ መርከቢቱን ያናወጠ ማዕበል መጥቶ ከኢየሱስ በወጣ ቃል በአንድ ድምፅ ብቻ የተግሣጽ ቃል ተቀብሎና ተገስጾ የተመለሰ ቢሆንም ከዚያ መልስ የተለያዩ የሰይጣን ሥራዎችና በሰዎችም በኩል የመጡ የማጥመድ እንደገናም የተንኮል ፈተናዎች ወደ እርሱ ቀርበው ምንም ላያመጡ በመጡበት መንገድ መመለሳቸውን የተጻፉልን የመጽሐፍቅዱስ ክፍሎች በግልጽ ያሳዩናል ታድያ ይሄ ጌታ በሰማይ የሚኖር ቢሆንም በኛ ውስጥም ሊኖር ደግሞ እኛን ማደርያዎቹና መቅደሱ ስላደረገን በሰይጣንና ሰይጣን በተጠቀመባቸው ወደፊትም በሚጠቀምባቸው ደካማ ሰዎች በኩል የሚመጣብንን ክስና የማጥመድ ፈተናም በውስጣችን ብቃት ሆኖ መልስን እየሰጠ የሚያሳፍርልንና ሰምተውንም ተደንቀው እስኪሄዱ ድረስ የሚያደርስልን ጌታ ነው መጽሐፍ ቅዱሳችን በዚሁ በማቴዎስ ወንጌል 22 ፥ 22 ላይ ይህንም ሰምተው ተደነቁ ትተውትም ሄዱ በማለት ይናገራልና የተወደዳችሁ ወገኖቼ ሆይ ታንኳችንን ደፍኖ የሚያናውጠውን የማዕበል ዓይነት በአንድ መንገድ ብቻ መጠበቅ ሞኝነት እንደሆነ አበክሬ ልነግራችሁ እወዳለሁ የዛሬው ማዕበል በነገው ጊዜያችን እንደዛሬው ሆኖ አይመጣምና ይህን ማዕበል በአንድ መንገድ ብቻ ልንጠብቀው አይገባም የሚመጣውም መልኩን ለውጦ በሌላ ዓይነት መልክ ነው ነገር ግን ያው የሆነው ኢየሱስ ለትላንቱ ማዕበል መገሰጫ ዝምና ጸጥ ማስባያ ቃል እንደነበረው ሁሉ ለነገው ፣ ከዚያም ባሻገር ለሚመጣው የተንኮልና የማጥመድ ማዕበል ልዩ የሆነ ፣ የበለጠ ፣ የተሻለም መልስ አለው ስለዚህ ትላንት ተገስጾ ዝም በል ጸጥ በል ተብሎ የሄደው ማዕበል በነገውም ሕይወታችን መልኩን ቀይሮ ቢመጣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ከዚህ ያላነሰና የበለጠ እርምጃ የሚወስድበት በመሆኑ ተገስጾ ይሄዳል በሰዎችም በኩል መጥቶ ከሆነ አሁንም እንደ ልማዱ እየፈራና እየተሸማቀቀ ሐፍረት ተከናነብኩ እኮ እያለና እየተደነቀም ትቶን ይሄዳል በመሆኑም ይህ ሁሉ በሕይወታችን እንዲሆን እኛም በእኛ በኩል የሚጠበቅብንን ነገር ማድረግ አለብን ከእኛ የሚጠበቀው ደግሞ መርከባችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ መጥተን ወደ መርከቡ ወደ ኢየሱስ ዛሬውኑ መግባት ገብተንም ከሆነ አለመውጣት ነው መርከባችን ኢየሱስ ሕይወትን ደፍኖ ከሚያናውጥ ማዕበል እንደገናም በሰይጣንና በደካማ ሰዎች በኩል እየመጣ ከሚከሰንና በተንኮል ሊያጠምደንም ከሚፈልገን ባላንጣችን የሚያስጥለን እኛም ወደ መርከቡ ገብተን አለመውጣታችንን ስናሳውቅና እርሱም ሲያውቅልን ነው መርከብ በባሕር ላይ የሚመጡትን ችግሮች አልፎ ፣ አሳልፎም ወደ ወደቡ እንደሚያደርስ እውነተኛው መርከባችን ኢየሱስም እነዚህንና ወደፊትም የሚመጡብንን ማበሎች ትንኮሳዎች እንዲሁም ተንኮሎች እየገሰጸ አሳልፎ የፍጻሜ ወደብ ወደሆነው ያደርሰናል ያም ወደብ ወደ መርከቡ ወደ ኢየሱስ ከመግባታችን የተነሣ የገባንበት ገነት ነው የሉቃስ ወንጌል 19 ፥ 1 _ 10 ፣ የሉቃስ ወንጌል 23 ፥ 42 እና 43 ፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 6 ፥ 9 _ 11 የተወደደው ሰዓትና የመዳን ቀን አሁን ነውና 2ኛ ቆሮንቶስ 6 ፥ 2 እንደገናም በዓለም ፍጻሜ የአባቴ ቡሩካን ተብለን የምንወርሰው መንግሥተ ሰማያት አለን መርከባችን የሆነው የናዝሬቱ ኢየሱስ አስተማማኝ መርከባችን ሆኖ ወደ ገነት ያገባን ብቻ ሳይሆን የአባቱንም መንግሥት የሰጠን እንድንወርሳትም የፈቀደልን በመሆኑ የሉቃስ ወንጌል 12 ፥ 12 ፣ የማቴዎስ ወንጌል 25 ፥ 31 _ 46 ፣ ቆላስያስ 1 ፥ 13 እና 14 ዛሬ ነገ ሳንል ማቅማማትና ማመንታትም ሳናደርግ ወደ መርከቡ ያልገባንና መርከቡንም ያልተሳፈርን ሰዎች ወደ መርከባችን ወደ ኢየሱስ አሁኑኑ መግባት ይሁንልን አባቶቼና ወንድሞቼ የክፍል ሁለት ትምህርቴን ጨርሻለሁ አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ወሰብሑ ወዘምሩ ሎቱ ወንግሩ ኩሎ መንክሮ መዝሙር 104 ( 105 )፥ 1 _ 3 የ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለራዕይ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment