Monday, March 9, 2015

ወአመ በጽሐ ዕድሜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት ወገብረ በሕገ ኦሪት ነገር ግን የዘመኑ ፍ ጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ ገላትያ 4 ፥ 4

ይህ  Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry  ሥር እየተዘጋጀ የሚቀርብላችሁ ትምህርት ነው


ውእቱሂ ከዊኖ ሰብአ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ወነስአ ሥጋ መዋቴ
ዘእም አዳም ለተወልዶቱ ውእቱ ቀዳማዊ ዘመጽአ ለተወልዶ ሥጋዊ


ትርጉም ሰውም ቢሆን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ሥጋዊ ልደትን
            ለመወለድ የመጣ ቀዳማዊ እርሱ ለመወለድ ከአዳም የተገኘ መዋቲ
            ሥጋን ነሣ

                    ሃይማኖተ አበው


                     እልመስጦግያ


                      ምዕራፍ 3
                     

ወአመ በጽሐ ዕድሜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት ወገብረ
በሕገ ኦሪት

ትርጉም፦ ነገር ግን የዘመኑ ጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን
           ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ

                   ገላትያ 4 4

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይህንን መልዕክት የምታነቡ ወገኖች በሙሉ የጥንቷ ኦርቶዶክሳዊት ሐዋርያዊትና ዓለማቀፋዊት የሆነችው ቤተክርስቲያናችን መሠረተ እምነቷ ይሄ ነው ኢየሱስ ከአብ የተወለደ በመሆኑ መጀመርያና መጨረሻ የሌለው ከአብ ጋር በቅድምና የነበረ ቀዳማዊ የእግዚአብሔር  የባሕርይ ልጁ ሲሆን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ከሴት በመወለዱ ደግሞ የለበሰው ከአዳም የተገኘ መዋቲ ወይም ሟች የሆነውን ሥጋ ነውና የሰው ልጅ መሆኑን ጠንቅቃ የምታውቅ በመሆንዋ ሳታዛባ የሰው ልጅ የሆነበትንና የእግዚአብሔር ልጅ የተባለበትን ምስጢር ለሰዎች ሁሉ ታስተምራለች በአሁኑ ዘመን እንዳለችዋ ቤተክርስቲያን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነ እግዚአብሔር ብቻ ነው ብላ መዋቲ ሥጋን በመልበሱ ምክንያት የሰው ልጅ የተባለበትን ምስጢር ሽምጥጥ አድርጋ በመካድ የሰው ልጅ በመባሉ ምክንያትና በሰውነቱም የሰራልንን የማዳን ሥራ እንደገናም ሰው ሆኖም በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠ ነውና ሰው በመሆኑም በአባቱ ፊት ለሰው ልጆች እየሰጠ ያለውን የአማላጅነት ሥራ ስታስተባብልና አማላጁ ኢየሱስ  በሰማይ የሚገኝ ብቻውን የሰው ልጆች ሁሉ  አማላጅ ሆኖ ሳለ ሌሎች ሞት የከለከላቸውን አማላጆች ሕያዋን አድርጋ ዛሬም ያማልዳሉ በማለት በአማላጅነቱም ሆነ በጌትነቱ የሚተካከለው የሌለ ጌታ እያለ እነዚሁኑ ሙታን አማላጆቼ ናቸው ስትል ከጎኑ ኮልኩላና ሰብጥራ ስታመልካቸውና ስትማጽናቸው ትኖራለች ይህ ግን የመጀመርያይቱ ሐዋርያዊት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምሕሮም ሆነ እምነት አይደለም እውነተኛይቱ ጥንታዊት ሐዋርያዊትና ዓለማቀፋዊት ኦርቶዶክስ  ቤተክርስቲያናችን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ ሳይሆን የሰውም ልጅ በመሆኑ ሞትን አሸንፎ በአብ ቀኝ የተቀመጠ ነውና ምንም እንኳ ዛሬ ላይ ያለችው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሃይማኖተ አበው ሳይቀር የተጻፈላትን የኢየሱስን ብቸኛ አማላጅነት ከመጽሐፍቅዱሱ ቃል ጋር አገናዝባ በውል ያልተረዳች ሆና ዛሬም ያማልዱኛል ስትል አግባብነት በሌለው ከኢየሱስ ጎን የኮለኮለቻቸውን የማይሰሙ ሙታን አማላጆችን የምታምንና የምትጣራ ብትሆንም ጥንታዊቷና ሐዋርያዊቷ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናችን ግን ይህ ነገር የማይነካካት ነውና እነዚህን ያለቦታቸው ገብተው ከኢየሱስ ጎን በሰው የተደረደሩ ተማላጅም ሆነ አማላጅ መሆን የማይችሉ ሙታን አማላጆችን በቃሉ ጉልበት ወዲያ አሽቀንጥራ ጥላ ብቻውን በአብ ፊት ለሰው ልጆች ሁሉ የሚማልድ ብቸኛ አማላጅ እርሱ ኢየሱስ ብቻ ነው ስትል የምታምንና የምታስተምርም ናት  ከላይ በመግቢያዬ ላይ በጠቀስኩት ቃል መሠረት የሃይማኖተ አበው መጽሐፍ እንደነገረን ሰው ቢሆንም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ሥጋዊ ልደትን ለመወለድ የመጣ ቀዳማዊ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ሟች የሆነውን የአዳምን ሥጋ የለበሰበት ምክንያት በገላትያ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ ይለናልና ከሕግ እርግማን ለመዋጀት ነው ገላትያ 3 10 በኃጢአታችን ምክንያት ሕጉ እርግማንን አምጥቶብን ነበር ስለዚህ ኢየሱስ ከሴት መወለድ ብቻ አይደለም እኛ ከሕግ በታች ነበርንና  ከሕግም በታች ሳይቀር ለእኛ ተወለደ በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ከሕግ በታች ስለእኛ መወለድ ብቻ ሳይሆን ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን ገላትያ 3 13 ከሴት የመወለዱ ከሕግም በታች የመወለዱና ሰው የመሆኑ የሰውንም ሥጋ የመልበሱ ምስጢር እንግዲህ ከዚህ የተነሳ ነው ይህ ሰው የሆነው ክርስቶስ ከሕግ እርግማን ሲዋጀን እንዲሁ ዝም ብሎ አይደለም በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን ስለ እኛ ኃጢአት ሆኖ 2 ቆሮንቶስ 5 21 ስለ በደላችን ደቆ ስለ መተላለፋችን ቆስሎ ከዓመጸኞች ጋር ተቆጥሮ እግዚአብሔር ሳይቀር በደዌ ያደቀው ዘንድ ፈቅዶ የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸክሞና ስለ ዓመጸኞችም ማልዶ ነው ለዚህ ነው አሁንም መጽሐፍቅዱሳችን ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን የሚለን ኢሳይያስ ፶፫ በሙሉ እንመልከት ወገኖቼ ታድያ ይሄ ሁሉ ደኅንነትና ፈውስ እንዲሁ የመጣ ይመስላችኋል ? በቃላት ሊገለጽ የማይችለውን ይህንን ሁሉ ዋጋ እኮ ኢየሱስ ከፍሎልን ነው ያዳነን በመሆኑም ሰው የሆነው ክርስቶስ የፈጸመልን ይህን የመሠለ የደኅንነት ሥራ እያለልን ዋጋው እንዳልተከፈለለት ሰው ሆነን ለመዳናችን ሌሎች መንገዶችን መፈለግ ከዚህም ሌላ በዱር በገደሉ መንከራተት ክርስቶስ ሰው ሆኖ የመጣበትንና ለመዳናችንም የከፈለውን ዋጋ ከንቱ አድርጎ መቁጠር ነውና አይበጀንም እግዚአብሔርም ከዚህ ሌላ ያዘጋጀው የደኅንነት መንገድ የለም ለዚህ ነው  ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ያለው ዮሐንስ ወንጌል 14 ፥ 6 ይሄን ሁሉ ዋጋ የከፈለው ስለ እኛ የቆሰለው የደማው መርገምም የሆነው እርሱ ነውና ይሄ ጌታችን ወደ አብ የሚወስደን ብቸኛ መንገዳችን ነው እንደገናም ከሞት የተነሣው በአምላክነቱ ብቻ ሳይሆን በሰውነቱም ስለሆነ በማቴዎስ ወንጌል 26 64 በተጻፈው ቃል መሠረት ኢየሱስም፦ አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው ይላልና ስለ እኛ ሊያማልድ በሰማይ የሚኖር ነው ዕብራውያን 7 23 _ 25 እንግዲህ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ተብሎና ሰው ሆኖም ወደ ሰማይ መውጣቱ በኃይል ቀኝ መቀመጡና ዳግመኛም በሰማይ ደመና መምጣቱ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት መኖሩን  በእርሱም ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው የሚችል መሆኑን የሚጠቁሙ እውነቶች በመሆናቸው ብቸኛ አዳኝነቱንና አማላጅነቱን አምኖ ለመቀበል ጥርጥር አይግባን ጌታ የምናነበውን ቃል በልቡናችን ያሳድርብን ጌታ ኢየሱስንም ጌታችንና አዳኛችን አድርገን በመቀበል ዛሬውኑ መዳን ይሁንልን

ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና ሙታን ግን አንዳች አያውቁም መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም መጽሐፈ መክብብ  9 : 5


ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን



ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment