Friday, March 13, 2015

ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ድርጅት ናት The church is a spiritual organism 1 Corinthians 12 : 12 _ 13

ቤተክርስቲያን



ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ድርጅት ናት



The church is a spiritual organism

1 Corinthians 12 : 12 _ 13


ክፍል ሦስት


ቤተክርስቲያን በምድር ላይ እንዳሉ ልዩ ልዩ ድርጅቶች ወይም የድርጅት ተቋሞች በምድር ላይ ተደራጅታ ያለች አንድ ተቋም ወይም ድርጅት ብቻ  ሳትሖን እግዚአብሔርም  ሊያደራጃት እያደራጃት ያለ ተደራጅታም የምትገኝና እየተደራጀችም ያለች የራሱ የባለቤቱ የእግዚአብሔር ትልቁ ተቋም ወይም ድርጅት ናት ጌታ እግዚአብሔር የራሴ ብሎ ለይቶ የሚያውቃትን ቤተክርስቲያን የራሱና የመንፈሱ መኖርያ ሊያደርጋት ያዋሕዳታል እያዋሃዳትም ይገኛል ለዚህም ነው በ1ኛ ቆሮንቶስ 12 1 ላይ ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ በማለት ይጀምርና አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል በማለት የሚነግረን 1 ቆሮንቶስ 12 12 እና 13 እንዲህ ዓይነቱ የአካል አንድነትና ውሕደት ሲመጣ የእግዚአብሔር መኖርያው ልንሆን እንጀምራለን ስለዚህም በዮሐንስ ወንጌል 14 23 ላይ ኢየሱስም መለሰ አለውም የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን ይለናል በ1ኛ ዮሐንስ  መልዕክት 3 24 ላይ ደግሞ ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን በማለት ከዚሁ ከዮሐንስ ወንጌል ጋር በጣምራነት ያለ ተመሣሣይ ሃሳብ ይናገራል የእግዚአብሔር የመንፈሱና የጌታችንም መኖርያ ሊሆን የሚወድ ሁሉ ቃሉን የሚጠብቅ ነው ቃሉን በመጠበቅ ውስጥ ደግሞ የአካል አንድነትና ውሕደት ይመጣል ዛሬ ታድያ በቅዱሳን መካከል መገነጣጠል መከፋፈልና መለያየት ያለው ሰዎች ከቃሉ ይልቅ የግል ፍላጎታቸውን ስለሚያስቀድሙ የቃሉ ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን ስለማይሰሙ እርሱ የሚለውንም ስለማይከተሉ እንዲህ ዓይነቱ መከፋፈል በእኛም ዘመን ሳይቀር ጎልቶና ሰፍቶ ይታያል በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያለ የግል ፍላጎት በጊዜ በእግዚአብሔር ቃል ካልታከመ ወይም ጨርሶ የተፈወሰ ካልሆነ የሚያመጣው መዘዝ የከፋ ነው የግል ፍላጎት በብዙ ነገር ተሸፍኖ ያለ በመሆኑ በአንድ ጊዜ ተገልጦ ልናውቀው አንችልም በዮሐንስ ወንጌል 12 1 _ 8  ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው ያለው የስምዖን ልጅ የአስቆሮቱ ይሁዳ ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው፧ አለ ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው ይለናል የስምዖን ጴጥሮስን ታሪክ ስናጠና ደግሞ እርሱም ቃሉን አበርትቶ ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ ይለናል የማርቆስ ወንጌል 14 31 የማቴዎስ ወንጌል 26 35 ስምኦን ጴጥሮስ ይህንን ማለቱ ለተመለከተው ሰው  ለጌታ ያለውን ጽኑ ፍቅር ለማሳየት  የተናገረው ነገር ይመስላል ነገር ግን አይደለም ፊተኝነትን አለቅነትን ታላቅነትንና  የበላይነትን የማሳየት ነገርን የሚያመለክት ነው ይሁን እንጂ ይህንን ነገር በመንፈሳዊው ዕይታ ስናየው በጌታ ጉዳይ ሰው እኔ አልክድህም ? ብሎ ስለራሱ መናገር አይችልም ስለ ራሱ መናገር የሚችል የራሱ የሆነ ብቻ ነው የጌታ የሆነ ግን የራሱ የሆነ ምንም ታሪክ ስለሌለው የጌታን ነገር ከሚናገር ውጪ እኔ የሚለው ነገር የለውም ጴጥሮስ ከዚህ በፊት በነበረው ነገር ከእኔነቱ የወጣ ስላልነበረ እንደገናም በግል የውስጥ ፍላጎቶቹ የታጠረም ስለነበረ ጌታ እርሱን ከሚያውቀው በላይ ራሱን ያወቀ መስሎት ስለራሱ መናገር ጀመረ ስለራስ መናገር ማለት ደግሞ እኔ እበልጣለሁ እኔ እሻላለሁ እኔ አልክድም ? ማለት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ይክዳሉ ማለትም ነው አንድ ሰው ስለራሱ ብቻ የሚናገር ከሆነ እኔ ትክክል ነኝ ሌሎቹ ግን የተሳሳቱ ናቸው ወይም  ይሳሳታሉ እየተሳሳቱም ይገኛሉ ማለቱ ነው የጴጥሮስ ነገር እንግዲህ እንደዚህ ነው ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም ማለቱ ሌሎች ግን ይክዱሃል ማለቱን የሚያመለክት ነው ስለራሱ የማያውቅ ሰው ግን ስለ ሌሎች ማወቅ አይችልም ታድያ ጴጥሮ የደቀ መዛሙርቱን ነገር ሊያውቅ ቀርቶ የራሱን ነገር እንኳ በቅጡ ያወቀ አይደለም የሚያውቀው ኢየሱስ ግን  ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው እኛ እራሳችንን ከምናውቅ በላይ ኢየሱስ እኛን ያውቀናል ስለዚህ እንደ ጴጥሮስ ለጌታም ሆነ ለሰዎች ስለራሳችን ብዙ በመናገር ጊዜ ማጥፋት የለብንም ለዚህ ነው በመጽሐፈ ምሳሌ 27 2 ላይ ሌላ ያመስግንህ እንጂ አፍህ አይደለም ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይደለም በማለት የነገረን በመሆኑም እንግዲህ በሰዎች ውስጥ ያለ የግል ፍላጎት እንደሚገባ ተለይቶ እስኪታውቅ ድረስ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በቅዱሳን መካከል ብዙ ነገርን ያመጣል ቤተክርስቲያን እንደሚገባ ወቅቷን ጠብቃ እንዳታድግ እንዳትሰፋ እንዳትበዛም የሚያደርጋት በሰዎች መካከል አስቸጋሪ የሆነ የግል ፍላጎት ስላለ ነው የግል ፍላጎት ቤተክርስቲያንን ሕዝብን የሀገርንም ዕድገት ሳይቀር ወደ ኋላ የሚጎትት ነው በመንገድ ላይ የነበረውን የእስራኤልን ሕዝብ ጉዞ ያዘገየ ያልተሳካውና ውጤት አልባም የነበረው  የማርያምና የአሮን ደብቀውት ያለ የግል ፍላጎት ነው ማርያምና አሮን በግል ፍላጎታቸው ላይ ብቻ ያተኮሩ ራስ ወዳድ ዝናንና ክብርን ናፋቂ ለምን ፊተኛ አልሆንኩም ? ለምንስ ተቀደምኩ ? ባይ ስለነበሩ በዘኁልቁ 12 2 ላይ በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን ? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን ? አሉ እግዚአብሔርም ሰማ ይለናል አያይዞም ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ ይለናል አሮንና ማርያም በሙሴ ቀንተውና ሙሴን ተፎካክረው በሙሴ ላይ ይህንን ነገር ይናገሩ እንጂ ሙሴ ግን በሕይወቱ በአስተሳሰቡም ሆነ በአካሄዱ የነማርያምና የነአሮን ዓይነት ሰው አልነበረም ለዚህ ነው መጽሐፍቅዱስ እኛም እርግጠኛውን ነገር እንድናውቅና እንድንይዝ ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ ያለን ዛሬ ያለው ሰው ግን ከጥቂቶች በቀር ትንሽ እንኳ በሕይወቱ እንደ ሙሴ እልፍ ያለ ሕይወት ኖሮት ምላሹ አካሄዱ ትሕትናን የተሞላ ሳይሆን አንድ ዓይነትና መለየትም እስከማይቻል ድረስ ሁሉም በግል ፍላጎቱ ብቻ ተይዞ እርስ በእርሱ እኔ እበልጥ እኔ እሻል ሲል የሚከራከር ነው በመካከል ያለ ጋፕ የሕይወት ከፍታም ሆነ የሕይወት ልዩነት አናይም አባቶች ሲተርቱ ከእጅ አይሻል ዶማ እንዲሉ አሁንም ከጥቂቶች በቀር ሁሉም ያውና አንድ ነው በዚህ ነገራችን ታድያ አሁንም እግዚአብሔር ይፈውሰን ከሚባል በቀር የተለየ መልስ የለም ከላይ እንደገለጥኩት የግል ፍላጎት ቶሎ ብሎ የተገለጠ የሚታወቅም አይደለምና  ማርያምና አሮን ሙሴን ሊወዳደሩትና ከሙሴም አናንስም ሊሉ ያነሱት የመጀመርያ ሃሳብ በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን ? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን ? የሚለው ሃሳብ ሳይሆን ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ የሚለው ነው ታድያ ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና የሚለው ሃሳብ ለዋነኛው ሃሳባቸው እንደመሸፈኛ የተጠቀሙበት ሃሳብ እንጂ ሙሴን ለመቃወም የተጠቀሙበት ትክክለኛው ሃሳባቸው አይደለም በእግዚአብሔርም የተሰማው ሃሳብ ወይም እግዚአብሔር የሰማው ሃሳብ ማርያምና አሮን ለዋናው ሃሳባቸው ማሳክያ እንደ መሸፈኛ የተጠቀሙበትን ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ የሚለውን ሳይሆን በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን ? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን ?  የሚለውን ነው በመሆኑም ዛሬም ይሄ እግዚአብሔር አላረጀም ሰዎች ለተደበቀው የግል ፍላጎታቸው የሚጠቀሙበትን  ከላይ የሆነ ተሸፍኖ ያለ የተቀመመ የጣፈጠ የተቀናጀ እውነት የሚመስለውን  በእግዚአብሔር ፊት ግን ተራና መናኛ የሆነውን የተኮለኮለና የተሰካካ የውሸት ቃላት ሳይሆን በልብ ውስጥ የበቀለውን ትክክለኛ ሃሳብ ይሰማል ለዚህ ነው እንግዲህ እግዚአብሔርም ተቈጥቶባቸው ሄደ ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ እነሆም፥ ማርያም ለምጻም ሆነች፥ እንደ አመዳይም ነጭ ሆነች አሮንም ማርያምን ተመለከተ፥ እነሆም፥ ለምጻም ሆና ነበር የሚለን ይህን የተመለከተ አሮንም ወዲያው በንስሐ መንፈስ ተሞልቶ  ሙሴን፦ ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህ፥ ኃጢአት አታድርግብን  ከእናቱ ሆድ በወጣ ጊዜ ግማሽ ሥጋው ተበልቶ እንደ ሞተ እርስዋ አትሁን ብሎ ለመነ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር እየጮኸ አቤቱ፥ እባክህ፥ አድናት አለው እግዚአብሔርም ሙሴን፦ አባትዋ ምራቁን በፊትዋ ቢተፋባት ስንኳ ሰባት ቀን ታፍር ዘንድ ይገባት ነበር ሰባት ቀን ከሰፈር ውጭ ተዘግታ ትቀመጥ፥ ከዚያም በኋላ ትመለስ አለው ማርያምም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ተዘግታ ተቀመጠች ማርያምም እስክትመለስ ድረስ ሕዝቡ አልተጓዙም ሲል የሚነግረን ሙሉ ማስረጃውን ለማግኘት ዘኁልቁ ምዕራፍ 12 በሙሉ ያንብቡ እግዚአብሔር ዛሬም እንደኛ እንደ ሰዎች  ሳይሸወድ ውይ እገሌ እገሊት እነእገሌ እኮ ትክክለኛ ናቸው  በማለት ሳይፈርድና ከንፈርም ሳይመጥ የነእገሌ እገሊት እገሌን ትክክለኛ ሃሳባቸውን ያውቃል ያነባል እንደ አስፈላጊነቱም ትክክለኛ የሆነ እርምጃን ይወስዳል ሮሜ 2 4 እና 5 በሌላ ስፍራም ላይ ሄደን መጽሐፍቅዱሳችንን ስናነብ የሚያጕረመርምብኝን ይህን ክፉ ሕዝብ እስከ መቼ እታገሠዋለሁ ? በእኔ ላይ የሚያጕረመርሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ሰማሁ እንዲህ በላቸው እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ የተቆጠራችሁ ሁሉ፥ እንደቁጥራችሁ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ፥ እናንተ ያጕረመረማችሁብኝ ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርስዋ አስቀምጣችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም ምርኮኛ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን አገባቸዋለሁ፥ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቃሉ በማለት ተናግሮአል ዘኁልቁ 14 26 _ 32 በመሆኑም በትክክለኛውና እግዚአብሔርም በቃሉ ውስጥ እንድንሆንለት በሚፈልገው ነገር ውስጥ ገብተን ከፉክክር ከውዽድር እኔ እበልጥ ከሚል ሽኩቻና የማጉረምረም ሥራ በተላቀቀ ሁኔታ ነፃ ወጥተን በአካል ውስጥ ያለውን መንፈሳዊ ሕብረትና ትሥስር በመረዳት ጌታ በሰጠን ጸጋ በትሕትና ቤተክርስቲያንን እንድናደራጅ እኛም እንድንደራጅ እግዚአብሔር ይርዳን


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment