Friday, March 13, 2015

ቤተክርስቲያን የኅብረትና የመገጣጠም ትርጉሙ

ቤተክርስቲያን


ክፍል አስር



የኅብረትና የመገጣጠም ትርጉሙ


የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥
ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥
ይመግበዋል ይከባከበውማል

ኤፌሶን 5 29


እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና
በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል

ቆላስያስ 2 19


ኅብረታችንና መገጣጠማችን የሚጀምረው ከትዳራችን ነው ትዳር የቤተክርስቲያን ትንሹ ተቋምና ማዕከል ነው ትዳር ለሀገርና ለዓለማችን ሳይቀር የሕይወት ተቋምና የኑሮ ማዕከል ተምሳሊት መሆኑን በዓለማችን ላይ የሚገኙ አዋቂዎች  ጠበብቶች እንዲሁም ሜሬጅ ካውንስለሮች እና የመሣሠሉት ከሚናገሩት ከሚጽፉት ከሚወያዩባቸውና ሃሳብ ከሰጡባቸው ጉዳዮች ተነስተን መናገር እንችላለን ሰዎች ለሃላፊነት በቅተው ቤተክርስቲያንን ሀገርን ልዩ ልዩ ድርጅቶችንና መንግሥታዊ ተቋሞችን እንዲመሩ የሚለኩትና የሚመዘኑት ለቦታውም ብቁ ናቸው ተብለውም ቦታውን በሃላፊነት የሚረከቡት በቤታቸው ማለት በትዳራቸው ውስጥ ባለ የኅብረትና የመገጣጠም ሕይወት ጤናማነታቸው ለትዳራቸውም ያለ ታማኝነታቸው ትጋታቸው ለሃላፊነት መብቃታቸው ተለክቶና ታይቶ ነው ይህንን በተመለከተ መጽሐፍቅዱሳችን ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል ? በትዕቢት ተነፍቶ በዲያብሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል ይለናል 1 ጢሞቴዎስ 3 5 _ 7 የትዳር ጤናማነትን እኛ በትዳር ውስጥ ያለን ባልና ሚስት በትዳራችን ዙርያ የሚገኙ ወዳጆች እንዲሁም ዘመድና አዝማድ ብቻ ሳይሆን በውጪ ባሉት ሰዎች ሳይቀር የሚመጣ ምስክርነት ስለሆነ ብርቱ ጥንቃቄ የእግዚአብሔርም እርዳታ ሳይቀር የሚያሻው ነው ትዳር ሲፈርስ ሁሉም ነገር አብሮ ይፈርሳል የትዳር ቀውስ ችግሩ ለባለ ትዳሮችና ለተጋቢዎች ብቻ ሳይሆን ለቤተክርስቲያን ለሀገርና ለዓለማችን ሳይቀር የተረፈ በመሆኑ ዛሬ የሱስ እስረኞችን በንጥቂያና በዝርፊያ የተሰማሩትን ከዚህም ሌላ በችግር ምክንያት ሜዳ ላይ የወደቁ ወላጅ አልባ ሕጻናትን ብንመለከት  የዚሁ ችግር ሰለባዎች መሆናቸውን  በቀላሉ ለመገመት አያዳግተንም ከዚህ የተነሳ ሐዋርያው የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል አለን ስለዚህ ሚስት ለባልዋ ሚስት ብቻ ሳትሆን ሥጋና አካል ናት ስለዚህ የባሎች ሚስቶቻቸውን መውደድ ከሚስትነት ወይም ከተቃራኒ የጾታ ፍቅር በእጅጉ የዘለለና ያለፈ ሊሆን ይገባል ምክንያቱም የሚስትነትና የባልነት ፍቅር አንዳንድ ጊዜ በውጪያያዊ ሁኔታዎች ላይ ያጠነጠነ ሊሆን ይችልና ፍቅር ያልቃል እንደገናም የተዋደድንበት ውጪያዊ የሆነ ፍቅር እንደነበረ ላይቀጥል ስለሚችል በሰዎች ሕይወት ውስጥ ደግሞ ብዙ ዓይነት ውጣ ውረዶችና ለውጦች ይታያሉና ከመዋደዳችን የተነሳ ለዓይናችን ሳይቀር መጠጋገብ እስኪያቅተን እንዳልደረስን ከሆነው ለውጥ የተነሳ እኛም ጊዜያዊ ከሆንን ወዲያው እንሰለቻቻለን እንጠላላለን ደግሞም እንገፋፋለን አምኖን ትዕማርን ከወደደበት ፍቅር እርሷን የጠላበት አይሎና በርትቶ ነበር በ2ኛ ሳሙኤል 13 15 ላይ የተጻፈውን ሄደን ስንመለከት ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ አምኖንም ተነሥተሽ ሂጂ አላት እርስዋም፦ አይሆንም ቀድሞ ከሠራኸው ክፋት ይልቅ እኔን በማውጣት የበለጠ ክፋት ትሠራለህ አለችው እርሱ ግን አልሰማትም የሚያገለግለውንም ብላቴና ጠርቶ ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት አለው ብዙ ኅብር ያለውንም ልብስ ለብሳ ነበር፥ እንዲህ ያለውን ልብስ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ ይለብሱ ነበርና አገልጋዩም አስወጥቶ በሩን ዘጋባት ትዕማርም በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ፥ ብዙ ኅብርም ያለውን ልብስዋን ተርትራ፥ እጅዋንም በራስዋ ላይ ጭና እየጮኸች ሄደች ይለናል የተወደዳችሁ ወገኖች የአምኖንንና የትዕማርን ነገር ስንመለከት አምኖን ለትእማር ወንድሟ ነው በዚህ ላይ እንዲህ ዓይነት አስነዋሪ ነገር አደረገባት እንግዲህ ጊዜያዊ እና ከላይ የሆነ ውጪያዊ ፍቅር ዓይን የሌለው ዕውር ነው በዚህ ላይ የሚያልቅ በመሆኑ የሚያመጣብን መዘዝ እንዲህ ዓይነቱን የከፋ ነገር ነው   ከእኛ ደግሞ አንዳንዶች እንደዚህ ነን ትላንት በነበረን የተዋበ የእጮኝነት ዘመን የጫጉላ ሕይወትና ጥቂት የሆኑ የአብሮነት  የትዳር ጊዜያት ጊዜያዊ ውጪያዊም በሆነ አምኖናዊ ዓይን ያጣ ፍቅር ተይዘን ታውረን አብደንና ከንፈን የትዳር ጓደኞቻችንን የተዋቡ መልኮችና ቁመናዎችን ብቻ ሳይሆን ስሞቻቸውን ሳይቀር አልጠግብ ብለን በየጓደኞቻችን ቤት በልዩ ልዩ የጥሪ ቦታዎች እንዲሁም በአገኘነው አጋጣሚዎችና ትልልቅ  መድረኮች ሳይቀር ተወዳጅ በማድረግ አግንነንና አቆላምጠን እንዳልጠራን በዛሬው በተለወጠው ነገር ዓይንህን ዓይንሽን ለአፈር በማለት ለእርቅና ለሰላም ሳይቀር አሻፈረኝ ያልነውን ተገፋፍተንም በር ዘግተን የተቀመጥነውን ቤት ይቁጠረን ከማለት በቀር የምለው የለም እግዚአብሔር ከዚህ ዓይነቱ አስከፊና አስነዋሪ ነገር ይመልሰን ደግሞም ይጠብቀን ነገር ግን ከሚስትነትና ከባልነት ባለፈ ሁኔታ ሥጋዬና አካሌ ብለን የተቀበልነውን ትዳር ጊዜያዊ በሆነ ውጪያዊ ፍቅር ብቻ በመያዝ ከሳ ጠቆረ አጣ ገረጣ ነጣ ወደቀ ከሰመ አለቀለት ብለን በውጪ አንጥለውም በበሩም አስወጥተን ደጅ አንዘጋበትም ሥጋችንና አካላችን ነውና በቤታችን እንዳለ ማንም ሳይሰማ እናክመዋለን እንጠግነዋለን  እንመግበዋለን እንንከባከበዋለን የብዙ ሰዎች የትዳር ሕይወት የታደሰው የተለወጠውና የተገነባው በዚህ ሁኔታ ነው ለዚህ ነው መጽሐፍቅዱሳችን እጮኝነትም ሆነ ትዳር ጊዜያዊ የሆነ ጥቅም ማግኛ በሆነበት በዚህ አስከፊ ዘመን የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና ያለን ስለዚህ ሚስታችን ወይም ባላችን ጊዜያዊ የሆነ ወረተኛ ፍቅራችንን የምናሳልፍባት መሸጋገርያ መወጣጫ ድልድያችን ሳትሆን ወይም ሳይሆን የገዛ ሚስቱን የሚወድ ስለሚል የኔ የራሴ የምንላት ባልም ከሆነ የኔ የራሴ የምትለው ልጥላው ልጥላት ብንል እንኳ ልንጠላት ልንጠላው የማንችል የራሳችን የሆነ የሆነች ሥጋችንና አካላችን ናት ነው ከዚህ የእግዚአብሔር ቃል እውነት የተነሳም አንዳንድ ጊዜ ሚስቶችም ሳይቀር አምኖናዊ ሆነው ባሎቻቸውን በማስወጣት በባሎቻቸው ላይ በር የሚዘጉ አይጠፉምና እኛም  ባሎች እግዚአብሔር የሰጠንን ይህን ትልቅ አደራና ሃላፊነት አውቀን አምኖናዊ የሆነ ባሕርያችንን በክርስቶስ ሁለንተናዊ የሆነ የፍቅር ባሕርይ ለውጠን ሚስቶቻችንን የመንከባከብና የመመገብ ግዴታ አለብን ያኔ በቤታችን ውስጥ እውነተኛ ፍቅር ሰላምም የሰፈነበት ትልቅ የትዳር ሕብረትና መገጣጠም ይሆናል ሐዋርያው እንዲህ ዓይነቱን ሕብረትና መገጣጠም በትዳር ዙርያ ብቻ አልተመለከተውም ይህ የአካል መገጣጠም በቤተክርስቲያንም ስለሆነ በቆላስያስ 2 19 ላይ የተጻፈውን ሃሳብ መሠረት በማድረግ እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ካለን በኋላ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል ሲል ነገረን ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ ባላየውም ያለፈቃድ እየገባ በሥጋዊ አእምሮ የሚፈርድ ሰው ራስ ወደሚሆነው ወደ ክርስቶስ ያልተጠጋና መጥቶም የአካል ብልት በመሆን ያልተገጠመ ነው ጌታ ኢየሱስ እንድንሆንለት የወደደው ራስ ከሆነው ከእርሱ ጋር የአካል ብልት በመሆን ተገጣጥመን እግዚአብሔር በሚሰጠን ማደግ እንድናድግለት ነው እንጂ እይታ በሌለው ጋዊ አእምሮ ተይዘን ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደድን እርስ በእርስ እንድንፈራረድ አይደለም ዛሬ ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ መጥቶ የመገጣጠምና የማደግ ጊዜ እንጂ ለራስ የሆነን ክብርንና አምልኮ ወዶ የመፈራረድ ጊዜ አይደለም ይህ ደግሞ በውጪ ያለ ችግር ብቻ ሳይሆን በቤት ውስጥም ባሉ አንዳንድ ያልገባቸው አገልጋዮች እና መሪ ነን ባዮች ሕይወት ውስጥ ያለም ችግር ነው ልናመልከው አክሊላችንንም አውርደን ሰግደንና ዝቅ ብለን ክብርን ልንሰጠው የሚገባው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ብቻ ነው ለታረደው በግ ለጌታ ለኢየሱስ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁንለት ስለዚህ በዚህ እስራት ውስጥ ያለን አካሉም ወዳደረገንና እንድንገጠምም ወደፈቀደልን ወደ ኢየሱስ መጥተን ያልተገጠምን ሰዎች ዛሬ ላይ ባይሰጡን ነገና ተነገ ወዲያ በምናደርገው ትግልና ተጽእኖ እናገኘዋለን ብለን ያሰብነውን የወደድነውንም ከንቱ የሆነ አዕምሮአዊ ትሕትናንና  አምልኮትን ጥለን በብልቶች መካከል ባለ ኅብረት ውስጥ ተጠቅልለንና ተካተን እግዚአብሔር ለሚሰጠው እድገት እራሳችንን በመስጠት መጥተን ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር በአካልነት ብንገጠም ይህ ከንቱ የሆነ አመለካከታችን ይቀረፋል እናድጋለን በብዙም እናተርፋለን ራስን አለመስጠትና መመለክ ግን የዲያብሎስ ሥራ ነው እውነተኛውን ትሕትናንና ልባዊ የሆነውን የአምልኮ ምሥጢር የምናገኘው መጥተን በተገጠምንበት የአካል ብልቶች መካከል ነው ያኔ ዓይናችን ተከፍቶ የምናመልከውን እናውቃለን ለእርሱም ብቻ ክብርን እንሰጣለን በተገጠምንበት አካል ውስጥ በኅብረትም መከካከል የትሕትናንም ነገር እናደርጋለን ሮሜ 12  16 በአካል ወስጥ መጥተን መገጠማችን ግን እውነተኛ የሆነና አማራጭ ልንሰጠውም የማንችለው ጉዳይ ነው አካል ሆኖ በመገጠም ውስጥ እርስ በእርስ መመካከር አለ በኤፌሶን 5  29 በተጻፈልን ቃል መሠረት ተመግቦም ማደግ አለ የእግዚአብሔር ቃል እውነት የሚያሳየን ይህንን ነው በዚህ ጉዳይ ላይ እነዚህን ጥቅሶች እንድታዩአቸው በጌታ ፍቅር አሳስባለሁ በዕብራውያን 3  13 ላይ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ ይለናል በዕብራውያን 10  24 ላይ ደግሞ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ በማለትም ይነግረናል 

እግዚአብሔር የምናነበውን ቃል ይባርክልን


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ



No comments:

Post a Comment