Friday, March 13, 2015

የቤተክርስቲያን የስብከት ሥራ በየግላችን ያለውን የሕይወት ምስክርነት ሳይቀር የሚያጠቃልልና የሚጨምር ነገር ነው

ቤተክርስቲያን


ክፍል አራት


የተወደዳችሁ ወገኖች ዛሬ የምንቀጥለው ክፍል ስምንትን ነበር ነገር ግን ክፍል አራትን በመሃል ሳልጽፍ ዘንግቼው ስለነበር ክፍል አራትን ለመጻፍ ተገድጃለሁ ለዚህ ነው ወደኋላ ወደ ክፍል አራት የመለስኳችሁ በዚህ አጋጣሚ ሳልጽፍ ስለዘነጋሁት የክፍል አራት ትምህርት አንባቢዎቼን ይቅርታ ልጠይቅ እወዳለሁ አሁን የምጽፈው ሃሳብ ግን የተዘነጋውን የክፍል አራት ትምህርት ነውና እንድትከታተሉ በጌታ ፍቅር አሳስባለሁ
    የቤተክርስቲያን የስብከት ሥራ በየግላችን ያለውን የሕይወት ምስክርነት ሳይቀር የሚያጠቃልልና የሚጨምር ነገር ነው የእግዚአብሔርን ቃል ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ከዚሁ ከእግዚአብሔር ቃል ጋራ መልካም በሆነ በሕይወት ምስክርነትን ውስጥ ተጠንጥኖ የቀረበ ስብከት ትምህርት ወይንም መዝሙር ልትሉት ትችላላችሁ በቀረበ ጊዜ መልዕክቱ ኃይል ያለው ይሆንና በጨለማው ዓለም ላይ ተስፋን የሚሰንቅ ብርሃንን የሚያበራ ይሆናል መጸሐፍቅዱስ ሲናገር እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ ይለናል የማቴዎስ ወንጌል 5 14 _ 16 ታድያ መጽሐፍቅዱሳችን የዓለም ብርሃን ናችሁ ስላለን ሙሉ ለሙሉ የዓለም ብርሃን ሆነናል ስለዚህ ከእንቅብ በታች አይደለንም ማለት አንችልም ከእንቅብ በታች ሆነን እንድንቀር እንዳናበራም የሚያደርጉን ብዙ ያልተሠሩ ነገሮቻችን አሉ እነርሱ ሲስተካከሉ በተራራ ላይ ያለች ልትሠወር የማትችል ከተማ እንሆናለን ብርሃናችንም ከፍ ብሎ ሲበራ ለሰዎች የሚታይ ይሆናል ይህ እንዲሆን ነው እንግዲህ በፊልጵስዩስ 2 14 እና 15 ላይ በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል ሐዋርያው የነገረን እንግዲህ በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረብን ሊሆን ይችላል ነገር ግን ብርሃናችን እንዳይበራ እንደ ብርሃን ልጆችም እንዳንታይ በእጅጉ የሚከለክሉን ነገሮች አሉ እነርሱም በዚሁ በፊልጵስዩስ መጽሐፍ ላይ እንደተጻፈልን የዋህ አለመሆን ነውረኛ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ማንጎራጎር ክፉ ማሰብ ሁሉን አለማድረግና  የመሳሰሉት ናቸው በተለይ ነውረኞች በምንሆንበት ጊዜ ክፉዎች አንጎራጓሪዎች የሰውን ሥጋ የምንበላ ሐሜተኞች ተጠራጣሪዎች ሰውን የምንጠላና ከሰውም ጋር የምንጠላላ ጠበኞች እንሆናለን እንዲህ ዓይነት ሰዎች በምንሆንበት ጊዜ ለእግዚአብሔር ሳይቀር የማንመለስ ሕዝቦች ሆነን እንገኛለን በዘዳግም 32 6 ላይ እግዚአብሔር እሥራኤልን እንዲህ ብሎት ነበር ደንቆሮ ብልሃተኛም ያልሆንህ ሕዝብ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ይህንን ትመልሳለህ ?  የገዛህ አባትህ  አይደለምን ? የፈጠረህና ያጸናህ እርሱ ነው በዘዳግም 32 5 ላይ ደግሞ  እነርሱ ረከሱ ልጆቹም አይደሉም ነውርም አለባቸው፤ ጠማማና ገልበጥባጣ ትውልድ ናቸው አለ በዘዳግም 32 20 ላይ እርሱም አለ፦ ፊቴን እሰውርባቸዋለሁ ፍጻሜያቸው ምን እንደ ሆነ አያለሁ ጠማማ ትውልድ ያልታመኑም ልጆች ናቸው አለን መዝሙረኛው ዳዊት ደግሞ እንዲህ ሲል ተናገረ እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ ጠማማና የምታስመርር ትውልድ፥ ልብዋን ያላቀናች ትውልድ፥ ነፍስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነች መዝሙር 78 8 ጠማማ በምንሆንበት ጊዜ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ይገኙብናል የእሥራኤል ጠማማነት ድንቁርና የታከለበት በመሆኑ መልሳቸው ለእግዚአብሔር ሳይቀር የማይሆን ነበር ለእግዚአብሔር ያልሆነን መልስ የሚሰጥ ደግሞ ለሰውማ ከዚያ የበለጠ ውልግድግድ ያለና ቅጡ የጠፋ መልስን ለሁላችን ሳይቀር የተገለጸ ነገር ነው ከእኛ አንዳንዶቻችን እንደዚህ ነን መልሳችን ጥያቄያችን  በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ፊት ያለ አቀራረባችን ለምንም የማይሆን ቅጥ የለሽ ይሆናል እግዚአብሔር አይከብርበትም ሰዎችም አይታነጹበትም እንደውም ከሚታነጹ ይልቅ ባደረግነው ነገር በብዙ ይሰናከላሉ ኢየሱስ ግን ለሚያሰናክል ሰው ይህንን ተናገረ በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት አለ የማቴዎስ ወንጌል 18 6 እና 7 ጠማማነት በሐዲስ ኪዳን ጌታ ሳይቀር የተጸየፈው ሕይወት ነው ኢየሱስም መልሶ፦ የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ የማቴዎስ ወንጌል 17 17 በተለይ በአማኙ መካከል ጠማማነትን ማቃናትና መመለስ የማይቻል ሆኖ ስለሚገኝ በቲቶ 3 10 እና 11 ላይ መለያየትን የሚያነሣ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ኃጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ፥ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ ይለናል ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ጠማማን ሰው ከጥመቱ እንዲመለስ እግዚአብሔር ካልረዳው በስተቀር ለምንም የማይሆን ይሆናል ስለዚህ በዚህ ነገር  ቅዱሳን ወገኖች እግዚአብሔር ይርዳን እላለሁ ሌላው የወንጌልን ብርሃን እንዳናበራ  ከእንቅብም በታች እንድናደርግ  እኛም እንደ ብርሃን ልጆች እንዳንመላለስ የሚከለክል ክፋት ነው የፊልጵስዩስ መጽሐፍ አሁንም ሳታንጎራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ ይለናል ክፋት ሰውን በእግዚአብሔር ላይ ሳይቀር አጉረምራሚ እንዲሆን የሚያደርገው ነው በዘኁልቁ 11 1 ላይ ሕዝቡም ክፉ ሆነው በእግዚአብሔር ላይ አጕረመረሙ እግዚአብሔርም ሰምቶ ተቈጣ የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ነደደች፥ የሰፈሩንም ዳር በላች ይለናል ስለዚህ ክፋት አጉረምራሚዎች እንጂ የወንጌልን ብርሃን እንድናበራ የሚያስችለን እንደገናም እንደብርሃን ልጆች የሚያመላልሰን አይሆንም ክፋት በግልጥ የሚታይ ነገር ብቻ ሳይሆን ይፋ ወጥቶ በአደባባይ ሊታይ በሥውር የሚካሄድ ነው ለዚህ ነው ጳውሎስ ሕይወቱ በጌታ ቃል የተለወጠና የተነካ በመሆኑ ምክንያት ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን ያለው 2 ቆሮንቶስ 4 2 የሰው ልጅ ሁሉ ሕይወቱ በወንጌል ተነክቶ የሚያሳፍረውንና ሥውሩን ነገር ሲጥል ሰውን ለመጉዳት የሚያስችለውን የተንኮል ምልልስ ቶሎ ብሎ ያቆመዋል በምትኩ የእግዚአብሔርን ቃል በግልጥነት ሳይቀላቅልና ሳይሸቃቅጥ መስበክ ይጀምራል ዛሬ የተሸቃቃጠና የተቀላቀለ ነገር የምንሰማው ያልተጣለ የሚያሳፍር ሥውር ነገር ተንኮለኝነትና ተንኮል ሳይቀር ስላለ ነው ሲሞን የሚባል ጠንቋይ በፊልጶስ አገልግሎት ያመነና የተጠመቀ ሊመስል አምኖ በመጠመቅ ከፊልጶስ ጋር መተባበሩን መጽሐፍቅዱሳችን ይነግረናል ነገር ግን ውሎ ሳያድር በነጴጥሮስ አገልግሎት የመንፈስቅዱስ ስጦታ ለሕዝቡ ሲመጣ ገንዘብ አመጣላቸውና  እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ በዚህን ጊዜ ነበር ጴጥሮስ የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንስሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና ሲለው ሲሞንም መልሶ፦ ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ አላቸው የሚለን የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 በሙሉ እናንብብ ክፋት ሲገለጥ እንዲህ ነው መራራ መርዝና የዓመጽ እሥራት አለበት ክፋት በልብ የሚበቅል ክፉ ሃሳብ ነው ስለዚህ በንስሐ ልናስወግደውና ይዘነውም ከሆነ በጊዜ ልንለቀው  ልንተወው ያስፈልጋል አይሆንም ብለን መንፈሳዊ በሚመስል ሽፋን ብንገፋበት  በጊዜ ውስጥ መገለጡ አይቀርምና ያሳፍረናል ለዚህ ነው ሲሞን የውስጥ እሥራቱ እጅግ የከፋ መሆኑን ስለተረዳ ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ ሲል ሐዋርያቱን የተማጸነው በ1ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 2 ፥ 1 _ 3 በተጻፈልን ቃል መሠረት ክፋት የጌታን ቸርነት የቃሉን ወተት በመቅመስና በማጣጣም ሊወገድ የሚገባው ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ኛ ጢሞቴዎስ 3 13 ላይ ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፥ እያሳቱና እየሳቱ፥ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ ይለናል ስለዚህ ክፋት የቃሉን ሕይወት አጣጥመው የተለወጡና ያደጉ ክርስቲያኖች ተግባር ሳይሆን  የክፉዎችና የአታላዮች እንዲሁም የአሳቾች ተግባር ነው የወንጌልን ብርሃን የሚያበራና እንደ ብርሃን ልጅም የሚታይ ግን ሳታንጎራጉሩና ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ ተብሎ የተጻፈለት ስለሆነ ከነዚህ ክፉ ተግባሮች ሁሉ የራቀ ነው ለእኛም እንግዲህ ጌታ እግዚአብሔር የማያንጎራጉርና ክፉም የማያስብ ሕይወት ይስጠን ይህንን ሕይወት ስናገኝ ነው እንግዲህ ወንጌል በሰዎች ሕይወት ውስጥ ሁሉ የሚበራው ያኔ ሰዎችም መልካሙን ሥራችንን አይተው የሰማዩ አባታችንን ማክበር ይጀምራሉ ወገኖች የትምህርቱ መልዕክት በዚህ ያበቃ አይደለም በሚቀጥለው በክፍል ስምንት ላይ አጠቃልለዋለሁ እስከዚያው ግን በዚሁ እሰናበታችኋለሁ ጌታ ይባርካችሁ


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ







No comments:

Post a Comment