Friday, March 13, 2015

ቤተክርስቲያን ክፍል አስራ ሁለት በአካል መገጣጠም ውስጥ ያለ የችሎታዎችና የስጦታዎች አስፈላጊነት

ቤተክርስቲያን


ክፍል አስራ ሁለት


በአካል መገጣጠም ውስጥ ያለ የችሎታዎችና የስጦታዎች አስፈላጊነት


ክርስቶስ ራስ በሆነባት ቤተክርስቲያን ውስጥ ላለ የአካልና የብልቶች መገጣጠም ዓይነተኛ ምክንያት የሆኑ ስጦታዎችና መክሊቶች በቤተክርስቲያን ፈሰዋል እንዲሁም ተሰጥተዋል እነዚህ መክሊቶችም ሆነ ስጦታዎች ከእግዚአብሔር የተሰጡ ችሎታዎች ናቸው እንጂ ሰዎች በኃይላቸው ወይም በጥበባቸውና በብልሃታቸው ያገኟቸው ያስገኟቸው ክሂሎቶች  ችሎታዎችና ስጦታዎች አይደሉም ችሎታውም ሆነ ስጦታው የሰጪው የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ ስላልሆነ ይህንን ለአካሉ መታነጽ ለቤተክርስቲያን ጥቅም የሆነውን ስጦታ የሰጠ እግዚአብሔር ክብር ይሁንለት ለዚህም ነው መጽሐፍቅዱሳችን በኤፌሶን 4 7 ላይ ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ የሚለን እንደገናም በዚሁ ክፍል ከቁጥር 11 _ 16 ላይ የስጦታዎችን ስያሜያቸውን አገልግሎታቸውንና የሚሰጡትን ጥቅም እንዲህ ሲል በሰፊው ያብራራል እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል ይለናል እነዚህ ስጦታዎች አካሉን ለማነጽም ሆነ የክርስቶስ ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ ለማድረስ የተሰጡ ቢሆኑም እነዚህ ስጦታዎች በጸጋ የተገኙ ስጦታዎች ናቸው የሰዎች የትጋትና የሥራ ውጤት አይደሉም ይህንን ስል ግን ትጋትና ሥራ አያስፈልጉም እያልኩ እንዳልሆነ ለሁላችንም ሊታወቅና ግልጽ ሊሆን ይገባል ትጋትና ሥራ የሚያስፈልግበት ቦታ አለ በነዚያ ቦታዎች ላይ ሁላችንም ልንተጋ ያስፈልጋል ደግሞም እንተጋለን በጸጋ የተገኙ ስጦታዎች ስንል ግን ምን ማለታችን እንደሆነ  መልሱን እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ  በጸጋ የተገኙ ስጦታዎች የሰው ነገር የሌለባቸው ጌታ እንዲሁ በቸርነቱ ለአካሉ መታነጽ እያካፈለ የሚሰጠው በዋጋ ወይንም በክፍያ ያልተገኘ ነጻ ስጦታ ነው ስለዚህ ይሄ ነጻ የሆነ ስጦታ ወይም ጸጋ የእግዚአብሔርና ከእግዚአብሔርም እንዲሁ በነጻ የተሰጠን ስለሆነ እንዲያው የሰጠንን የጸጋውን ክብር እያመሰገንን አካሉን በማነጽ ሥራ ላይ ጌታ በሰጠን ጸጋ በትሕትና ፣ የማልጠቅም ባርያ ነኝ እያልንና ለጌታም የሚገባውን ክብር እየሰጠን ከምናገለግል ውጪ እራሳችንን ከሌላው ጋር የምናስተያይበትና የምናወዳድርበት እርስ በእርስም ብልጫውንና ቦታውን ለማግኘት የምንወዳደርበት የአገልግሎት ድርሻና መድረክ አይደለም በ1ኛ ቆሮንቶስ 4 ፥ 6 እና 7 ላይ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል ? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው ? የሚለን ለዚህ ነው  ከእነዚህ እውነቶች የተነሳም ለዚህ ነው በዚሁ ክፍል ላይ እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ የሚለን እንደገናም ከእርሱ የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል ይለናል ስለዚህ ክርስቶስ የእድገታችን ግብና ፍጻሜ  ሆኖ እውነትን በፍቅር እንድንይዝ እርስ በእርሳችንም ተገጣጥመን እንድንያያዝ ራሳችንን በፍቅር ለማነጽና አካሉንም ለማሳደግ የሚያደርገን የተሰጠን ጸጋ የተሰጠን ሕይወት  ባለቤት ያለው በመሆኑ የባለቤቱ የእግዚአብሔር ብቻ ነውና ከእኛ እንዳልሆነ ስናውቅ እንደገናም በእውቀት ብቻ ሳይሆን በጥልቀትም ስንረዳ  ያኔ እውነትን በፍቅር ለመያዝ ተገጣጥሞም ለመያያዝ ራስን በፍቅር ለማነጽ አካልን ለማሳደግም ሆነ እኛም አብሮ ለማደግ አንቸገርም በ1ኛ ቆሮንቶስ 13 ፥ 1 _ 3 ላይ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም ስለሚል እነዚህን ስጦታዎች በፍቅር መለማመድና ማድረግ አለብን  እነዚህ ስጦታዎች አካሉን ለማስታጠቅ  ለማሳደግና ወደ ሙላቱም ለማድረስ ለአገልግሎቱ ለተለዩ ሰዎች በተለየ ሁኔታ የተሰጠ ቢሆንም ጸጋ ግን የሌለው ማንም ክርስቲያን የለምና በአካሉም መካከል ማለት በእያንዳንዱ ቅዱሳን ሕይወት ውስጥ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን አድርጓል በሮሜ 12 3 _ 8 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎአል እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር ይለናል ታድያ ለብዙዎቻችን ግን አገልግሎት  መድረክ ላይ ወጥቶ መስበክ መዘመር ማስተማር ብቻ ሊመስለን ይችልና እዚያ ላይ ትኩረታችንን እናደርጋለን  አገልግሎት ግን መስበክ ማስተማር መዘመር ብቻ አይደለም መምከር በልግስና መስጠት መማርና የመሣሠሉት ነገሮች ሁሉ አገልግሎቶች ናቸው እኛ የሚታየን ማስተማር መስበካችን መዘመራችን የመድረክ ላይ አገልግሎታችን ነው እግዚአብሔር ግን ከመድረክ መልስ ያለውን እኛነታችንን ማለት የምንምር ከሆነ በደስታ መማራችንን ፣  የምንሰጥ ከሆነ በልግስና መስጠታችንን ፣ ወንድም እህቶችን ለመፈለግ መነሳሳታችንን ፣ በብልቶች መካከልም መለያየት ስለሌለ አታስፈልገኝም የሚለውን የመገፋፋትና የመጠላላት ቋንቋችንን ወዲያ ጥለን አካሌ ነህ ታስፈልገኛለህ ማለታችንን ፣  ወንድሞችና እህቶቻችን  ቢለዩን ደግሞ የሚያጎድሉብን የአካል ብልቶቻችን መሆናቸውን አውቀን በእነርሱ ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆናችንንና መጠቀማችንን ፣ ብልቶች መሆናችንን አውቀንም እርስ በእርስ መተሳሰባችንን የመሣሠሉትን ነገሮች ሁሉ ይፈልገዋል  ታድያ ይህንን ትልቅ የተጻፈልንን የእግዚአብሔር እውነት ሳንረዳና በዚህም እውነት ውስጥ ሳንገባ እንዲሁ ለስማ በለውና ለታይታ  ለልዩ ልዩ ፍላጎቶቻችንም  ማሳክያ ብቻ መድረክ ላይ ወጥተን እናስተምራለን እንሰብካለን እንዘምራለን የመሳሰሉትንም የመድረክ ላይ ሥራዎችን እንሰራለን ብንል ትክክል አይሆንም ለዚህም ነው በማቴዎስ ወንጌል 5 24 ላይ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ የሚለን ወንድም እህቶቻችንን ሳንምርና ይቅር ሳንል ደግሞም ሳንታረቅ በመሰውያ ፊት መባ ብናቀርብ መባችን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሌለው የቃዬል መሥዋዕት ዓይነት ይሆናል ከዚህም ሌላ እግዚአብሔርን ሳይቀር መሸንገል ይሆንብናልና አይሆንም ይህንን አካሄዳችንንም  እግዚአብሔር አይቀበለውም የምንምር ከሆንን ሳናንገራግር በደስታ መማር አለብን ማለትም ምሕረት መስጠትንና ምሕረት መቀበልን እግዚአብሔር ከእኛ ይጠብቃል አለበለዚያ መሥዋዕታችን እውነተኛ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ዋጋ የሌለው ይሆናል  መስጠት ያለብንም ከሆነ ንፉግነትንና ስስትን አስወግደን በልግስና ለእግዚአብሔር ልንሰጥ ይገባል  1ኛ ዜና 29 12 _ 15 ፣ የማርቆስ ወንጌል 12 ፥ 41 _ 44 እንደገናም የእግዚአብሔር እውነት በግልጽ ተጽፎልን ሳለ የማንጠቀምበት በመሆናችን አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል በሕግም ብትደገፍ በእግዚአብሔርም ብትመካ ፈቃዱንም ብታውቅ ከሕግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ በሕግም የእውቀትና የእውነት መልክ ስላለህ፥ የዕውሮች መሪ፥ በጨለማም ላሉ ብርሃን፥ የሰነፎችም አስተማሪ፥ የሕፃናትም መምህር እንደ ሆንህ በራሥህ ብትታመን እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራሥህን አታስተምርምን ? አትሥረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን ? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን ? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን ? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን ? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ ይሆንብናል ሮሜ 2 17 _ 24  ስለዚህ በቅድሚያ እራሳችንን ማስተማርና ማሰልጠን ይገባናል አለበለዚያ  እኛ ያላደረግነውን ነገር ሌሎች እንዲያደርጉ ብናስተምር ፈሪሳዊ እንባላለን የማቴዎስ ወንጌል 23 3 የእግዚአብሔርንም ስም ማሰደብ ይሆንብናልና በብርቱ ልንጠነቀቅ ይገባል ለዚህም ነው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ለራሥህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራሥህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና ሲል የመከረው 1 ጢሞቴዎስ 4 16 ሌላው ሳንገልጸው እና ሳንናገረው የማናልፈው በ1ኛ ቆሮንቶስ 12 4 _ 30 በሮሜ 12 3 _ 8 ከጠቀስነው ሃሳብ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሃሳብ እናገኛለን  ስለጸጋ ስጦታና ስለ አገልግሎቱ ተናግረን ብቻ አናበቃም ስለተሰጠን መክሊትም እንናገራለን የአገልግሎት መክሊቶችም ቢሆኑ እንዲሁ ከእግዚአብሔር የተሰጡ ስጦታዎች እንጂ ሰዎች ከችሎታቸው የተነሳ ያገኙት እንዳልሆነ ልናስተውል ይገባል በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ችሎታ እንጂ የግሌ የራሴ የምንለው የግልና የራስ ችሎታ የለም እነዚህ መክሊቶች ነግደን እንድናተርፍ ከጌታ የተሰጡን የአገልግሎት መክሊቶች ስለሆኑም አንተ ታማኝ ባርያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ እንድንባል በመክሊታችን ነግደን ማትረፍ አለብን አለበለዚያ መክሊት ቀባሪ ተብለን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ ጨለማው እንጣላለን መክሊቶቹም የሚሰጡን አትራፊዎችና ተሸላሚዎች እንድንሆን ስለሚፈለግ በአቅማችን ልክ ነው በሉቃስ 12 48 ላይ ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል ይለናልና  ጌታ ደግሞ ያልሰጠንን አይጠብቅብንም ይህንን ክፍል የምናገኘው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ፥14 _ 30 ላይ ስለሆነ በማስተዋል ሆነን እናንብበው እናጥናው ጌታ የምናነበውን የሕይወት ቃል ይባርክልን በቃሉም ይጥቀመን ተባረኩልኝ



ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment