Friday, March 13, 2015

ቤተክርስቲያንን በግሪኩ ቃል ስንመለከተው ኤክሌሽያ የሚለውን ስያሜ አግኝቶ እናየዋለን

ቤተክርስቲያን

ክፍል ሁለት

ቤተክርስቲያንን በግሪኩ ቃል ስንመለከተው ኤክሌሽያ የሚለውን ስያሜ አግኝቶ እናየዋለን በአሁኑ በአዲሱ ኪዳን አጻጻፍ ወይም አባባል ኤክሌሽያ የጋራ የሆነ ቃል ነው ለማዘጋጀት መሰብሰብ  ማለትን ያመለክታል ተጠርቶ የወጣውን ሕዝብ ፎርም ማድረግ ማለት ቅርጽ ማስያዝ ይዘት መስጠትን የሚያመለክት ነገር ነው  ኤክሌሽያ የሚለውን ቃል በቀጥታ ከግሪኩ ቃል ስንተረጉመው ተጠርቶ የወጣ የሚለውን ሃሳብ እናገኝበታለን ኤክሌሽያ ልክ የጥንቷ እስራኤል ከግብጽ ወጥታ በምድረበዳ በስብስብ እንዳለች  በአንድ ላይ ለመሰብሰብ ተጠርቶ የወጣ የሕዝብ አካል ማለት ነው በሐዋርያት ሥራ 7 38 ላይ ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ ለእርሱም አባቶቻችን ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ አሮንንም በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና አሉት ይለናል ከአባቶቻችን ጋር በምድረበዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው የሚለው ሃሳብ እንግዲህ በሐዲስኪዳን ላለችው ኤክሌሽያ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ጥላ ሆኖ በምሳሌነት የሚነገር ነው ኢየሱስም በእርሱ የአገልግሎት ዘመን ውስጥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔ እሰራለሁ የገሃነም ደጆች አይችሉአትም አለ የማቴዎስ ወንጌል 16  18 ቤተክርስቲያኔን ሲል እንግዲህ ያሰባሰብኩትን ወይም እኔ የሰበሰብኩትን ማለቱ ነው በእንግሊዘኛው I will build my  assembly ( Young`s Literal Translation ) ማለትን ያመለክታል ስለዚህ የራሱ ቤተክርስቲያን አድርጎ የሰበሰበን እና የሰራን እርሱ ክርስቶስ ነው ክብር ለስሙ ይሁን በመሆኑም እኛ የማንም ስብስብና ክምችት አይደለንም ባለቤት ያለን ባለቤታችንም ክርስቶስ የሆነ ክርስቶስ የሰበሰበን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ነን ታድያ የቤተክርስቲያን ባለቤት ክርስቶስ ሆኖ ሳለ ሰዎች በባለቤትነት ተጠርተው ቤተክርስቲያን የእነርሱ እንደሆነች ታስቦ የእገሌ የእገሊት የነእገሌ ቤተክርስቲያን ሲባል እጅግ የሚያሳፍርና የሚያስፈራም ነገር ነው ቤተክርስቲያን የሰው ከሆነች ባለቤትዋም ሰው ነው ማለት ነው በዚህ ውስጥ እንግዲህ ክርስቶስ የለበትም እያልን ነውና ከዚህ አስነዋሪ ሥራ ራሱ ጌታችን ይጠብቀን ቤተክርስቲያን ወደድንም ጠላንም የሰው ሳትሆን የክርስቶስ ናት ለዚህም ነው በሐዋርያት ሥራ 20 28 ጀምሮ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ በማለት ቃሉ የነገረን ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ወይም የክርስቶስ ሆና ሳለ ሳያፍሩ እና ሳይፈሩ አፍን ሞልቶ የኔ ናት በማለት በራስ ስም ማስጠራት ጠባቂነት ሳይሆን ተኩላነት ነው የጥሪው አቅጣጫም የሚያመለክተን ቅዱስ ለመሆን መጠራታችንን ነው በ1ኛ ቆሮንቶስ 1 2 በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን ይለናል ስለዚህ የተጠራነው ቅዱሳን ለመሆን ነው ይህ ደግሞ የተለየ የእግዚአብሔር ጥሪ ነው እግዚአብሔር የጠራን ወደ ልጁ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት በመሆኑ ወደዚህ ኅብረት የጠራን እግዚአብሔር የታመነ ነው 1 ቆሮንቶስ 1 9 በመንፈስቅዱስ ሕልውና በአእምሮ ማስተዋል የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን በጥሩ ባሕርይ ልንገልጥ የተሰባሰብን ሕዝቦች ነን ቃሉ እንደሚነግረን እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም ይለናል 1 ቆሮንቶስ 2 12 እና 13 ስለዚህ ነገሩ ምንም እንኳ ለአእምሮአችን የማይመስለን ሆኖ ልንቀበለው ብንቸገርም በሮሜ 8 ፥ 28 _ 30  በተገለጸው ቃል መሠረት እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው ይለናልና ቃሉ የሆነብንን ነገር ይዘን ለምን ሆነብን እያልን ከምናጉረመርምና ከምንተክዝ ይልቅ መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር የሚያስተያይ ማስተዋል ካገኘን በነገሩ ከመደናገጥና ከመሸበር ይልቅ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው እንላለን ለበጎ ነው ብለንም አንቀርም በጎ የሆነውን የእግዚአብሔርን ነገር በፍጻሜው እናያለን የእግዚአብሔር የመጨረሻ ነገሩ እኛን ማክበር ነው እግዚአብሔር የሚያከብራቸውና በእግዚአብሔርም የሚከብሩ ሰዎች ደግሞ በብዙ ነገር ውስጥ ያልፋሉ ብዙ ያልጠበቁትና የማይገምቱት ነገር ይሆንባቸዋል ፍጻሜው ግን ለበጎ የሆነና ክብርም ያለበት ነው ይህንን ነው እንግዲህ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ተረድታ በመንፈስቅዱስ ሕልውናና በበሰለ አዕምሮ  በጥሩ ባሕርይ የእግዚአብሔርን ነገር የምትገልጠው ይህን ለማድረግ ደግሞ በእግዚአብሔር መንፈስ ውስጥ መሆን በመንፈስቅዱስም መጠመቅ ዋናና አስፈላጊ ነገር ነው የሐዋርያት ሥራ 2 38 እና 39 ሮሜ 8 9 ኤፌሶን 4 3 _ 6 በተለይ ተጠርቶ የወጣ እና  ለሕብረት የተጠራ ሕዝብ በልዩነት ሊኖር አይገባም በልዩነት የሚያኖር ነገር ደግሞ የሰው ነገር ነው ሰዎች የራሳቸውን ነገር ሲፈልጉ መከበር መደመጥ የኔ ብቻ ይሰማ እኔ ያልኩት ይሁን ማለት ሲጀምሩ ፖፑላሪቲን ሲፈልጉ እንደ እግዚአብሔር ቃል መሄድ ሲያቅታቸው ልዩነት ይሆናል ይሁን እንጂ ዛሬ ከአንድነት ይልቅ ልዩነቱ ሰፍቶ ሰዎች በክርስቶስ አካል ውስጥ ገብተው በክርስቶስ በተሠራው እውነት መተዋወቅ ሲገባቸው ትውውቁ የሥጋ የሆነ ጓደኝነት አብሮ አደግነት ዝምድናና የመሳሰሉት ይሆኑና ጥቅማጥቅም ላይ የተመሠረተ ልዩነት ውስጥ ይገባል ልዩነቱም የዛኑ ያክል የሰፋ ይሆናል ከዚህ የተነሳ ነው እንግዲህ በሐዋርያት ሥራ 6 1 ላይ በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፥ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና የሚለን በሌላው ላይ ማንጎራጎርና ሌላውን ችላ ማለት የሚመጣው በክርስቶስ አካል ውስጥ ያለውን አንድነት ካለማወቅ የተነሳ ብቻ ሳይሆን ራስንም ካለማወቅ የተነሳና እኔ ማን ነኝ ? ካለማለትም የተነሳ ነው ልዩነቶች ሲመጡና የሥጋ ሥራ ሲጀመር ሁልጊዜ በሌላው ላይ ማንጎራጎርና ሌላውንም ችላ ማለት ይመጣል በዚህም ምክንያት ይሄ ማንጎራጎር ሐሜት ጥላቻና ግልምጫ እንዲሁም መገለል ገጥሞአቸው ከእግዚአብሔር ቤት የሸሹትን ቤት ይቁጠራቸው እንዲህ  የሚያንጎራጉሩ የሚጠሉና ሌላውንም  የሚገላምጡ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቤት የራሳቸው ሊያደርጉ የሚፈልጉ ቡድንንና ግሩፕን የሚፈጥሩ የእግዚአብሔርን ሥራ ሳይሆን የጓደኝነትን ሥራ የሚሰሩ ናቸው እነዚህን ሰዎች ታድያ እግዚአብሔር ይለውጣቸው ያስተምራቸው ከምንል በቀር የምንለው የለንም አሁንም እነዚህን ሰዎች እግዚአብሔር በምሕረቱ ይገናኛቸው ይለውጣቸው ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 12 2 ላይ ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ በማለት ይናገራል በሥጋ በምንተዋወቅበት ጊዜ እየቆዩ ከላይ የዘረዘርኳቸው አወኩሽ ናቅሑሽ ሐሜት ጥላቻ አሉባልታና የመሳሰሉት ነገሮች ይመጣሉ እንደ ጳውሎስ ሰውን በክርስቶስ ስናውቅ ግን በአካል መካከል መለያየት የለምና ከሐሜቱ ከጥላቻውና ከአሉባልታው ይልቅ እርስ በእርስ ባለ ትሕትና የዋሕነት ትዕግሥትና ፍቅር እንመላለሳለን በዚህ ፍቅር ሰዎችንም እንታገሳለን በሰላም ማሰርያም የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ እንተጋለን ኤፌሶን 4 2 _ 6 ከዚህም ሌላ መጽሐፍቅዱሳችን የሚነግረን እንዲህ ነው ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ ይለናል ኤፌሶን 4 24 _ 32 ዛሬ ግን ታድያ ጸጋን ከሚሰጡ ቃላቶች ይልቅ መውጊያ የሆኑና ኃይለ ቃላትን ያዘሉ ቃሎች መራርነት ንዴት ቁጣና፣  ጩኸት የሚወጣው ከእግዚአብሔር ቤት ሆኖአል እግዚአብሔር ይፈውሰን ሰዎችን ለማነጽ ጸጋን የሚሰጡ ቃላት ተናግረን ልናጽናና እኛም ልንጽናና ተነገረን እንጂ በማይጠቅምና በክፉ ቃላት ሰዎችን ልናማርርና እናም ልንማረር አልተናገረንም ለዚህም አልተጠራንም እግዚአብሔር የፍቅር የየዋሕነትንና የመቀባበልን መንፈስ ይስጠን

በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል

         ፊልጵስዩስ 4 8 እና 9



ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ
       
             ሮሜ 15 7




      ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment