Monday, March 30, 2015

005 የተወደዳችሁ ወገኖች እነዚህን ማሳሰብያዎች በተራ ቁጥር ያቀረብናቸው ናቸውና እንደሚከተለው ተመልከቷቸው 1ኛ)በዚህ ትምህርት ውስጥ ከመጽሐፍቅዱሳችን ባሻገር ይህንኑ የእግዚአብሔር ቃል አስተምሕሮታችንን የሚደግፉ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተጻፉ ልዩ ልዩ መጽሕፍትን ለማብራርያነት ተጠቅመናል ይህንን ያደረግንበት ምክንያት እነዚህ መጻሕፍት ከመጽሐፍቅዱሳችን ጋራ በእኩልነት እንዲታዩ ለማድረግ ብለን ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል መሠረት የምንሰጠው አስተምሕሮ በእነዚህ መጻሕፍቶችም ውስጥ ተጠቅሰው ስላሉ ሕዝባችንን ወደ ትክክለኛው የእግዚአብሔር ቃል እውነት ለማምጣት በር ስለሚከፍቱልንና መንገድ ስለሚሆኑን ነው 2ኛ)የጥንቷ ኦርቶዶክሳዊት ሐዋርያዊትና ዓለማቀፋዊቷ ቤተክርስቲያን ትክክለኛ የእግዚአብሔር ቃል እውነት የምትከተል ለመሆኗም በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ የሠፈሩት ጽሑፎች ይመሠክራሉ ታድያ እነዚህ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ፍጹም ሳይጋጩ ተስማምተው የተጻፉ ጽሑፎች ካሉ እነዚህን ጽሑፎች ከእግዚአብሔር ቃል ጋር አገናኝቶ ማስተማር ተገቢያችን ነው እንላለን እንዲህ በምናስተምርበት ጊዜ ደግሞ ሕዝባችን የእግዚአብሔር ቃል የማይደግፈውን እውነት ይዞ ከሆነ ከመጽሐፍቅዱሱ ሌላ በእነዚህ በኦርቶዶክስ መጽሕፍት ውስጥ ሠፍረው ያሉ ሃሳቦች ከመጽሐፍቅዱሱ ቃል ጋር የተስማሙ በመሆናቸው ለሕዝባችን እገዛ ሆነው ሕዝባችንን ወደ ትክክለኛ የእግዚአብሔር ቃል እውነት እንዲመጣ የእግዚአብሔርንም ቃል ብቻ እንዲከተል በእርግጠኝነት ይረዱታል ለዚህ ነው ይህንን የምናደርገው 3ኛ)መጽሐፍቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ ብቸኛ የእግዚአብሔር መጽሐፍ እንደሆነ እናምናለን የእግዚአብሔር መጽሐፍ የሆነውን 66ቱን መጽሐፍቅዱስ ብቻ እናስተምራለን ከዚህ ውጪ የምናምነውም የምናስተምረውም ሆነ የምንሰብከው ቃል የለም 4ኛ)በዚህ ትምህርት ውስጥ የሃይማኖተ አበው መጽሐፍንም ሆነ የውዳሴ ማርያምን የጸሎት መጽሐፍ ተጠቅመናል የተጠቀምነውም በእግዚአብሔር ቃል ላለ እውነት እንደ አስረጂና ማብራርያነት የሚያገለግሉን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይጋጩ እውነቶች ስላገኘን ነው ይሁን እንጂ በሃይማኖተ አበው መጽሐፍም ሆነ በውዳሴ ማርያም የጸሎት መጽሐፍ ውስጥ ያለውን የጸሎት መጽሐፍ ተጠቀምን ማለት ሃይማኖተ አበውን እንደገናም የውዳሴ ማርያምን የጸሎት መጽሐፍ ተቀበልን ማለት አይደለም በተለይ የውዳሴ ማርያም የጸሎት መጽሐፍ የሚያሳየን ውዳሴሃ ለማርያም እያለ የማርያምን ውዳሴ ነው ነገር ግን ሊወደስም ሆነ ሊመሠገን የሚገባው እግዚአብሔር ብቻ ነውና ውዳሴ ለእግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ነው የምናምነው ሮሜ 11 ፥ 36 ፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 8 ፥ 5 እና 6 ፤ 2 ቆሮንቶስ 13 ፥ 14 ፤ ዘጸአት 20 ፥ 3 _ 6 ፤ ዮሐንስ ወንጌል 2 ፥ 5 5ኛ )በዚህ ጉዳይ ላይ የአማኞች ቤተክርስቲያንንም ብንመለከት የክርስቶስ አማኞች የሆኑት ቅዱሳን የሚያምኑት 66ቱን ቅዱሳት መጻሕፍትን የያዘውን መጽሐፍቅዱስን ብቻ ነው ነገር ግን በተለያየ ክፍለ ዘመን የተለያዩ የእግዚአብሔር ባሮች የጻፉዋቸውን መጻሕፍት ብዙ አገልጋዮች ለትምህርታቸው በዋቢነት አስረጂ በማድረግ ከመጽሐፍቅዱስ ቃል ጋር እያጣቀሱ ሲያስተምሩበት አይቻለሁ እኔም ይህንኑ መንገድ ተጠቅሜ አውቃለሁ እስካሁንም ሲሰራበት ያለና እየተሰራበት ያለም ነገር ነው ማለቴ አዲስ ነገር አይደለም ለማለት ነው እንደምሳሌ እንውሰድ ብንል ዶክተር ዓለሙ ቢፍቱ የእግዚአብሔር ባርያ የጻፉትን የቃል ኪዳን ታቦት በማደርያው ድንኳን የሚለውን መጽሐፋቸውን ብዙዎች አጣቅሰው ከእግዚአብሔር ቃል ጋራ በማገናኘት ሲያስተምሩበት ይህ ብቻ አይደለም ራሱን መጽሐፉን ሳይቀር ሲማሩት አይቻለሁ እኔም ተጠቅሜያለሁ ታድያ መጽሐፉ ከእግዚአብሔር ቃል ጋራ እስካልተጋጨ ድረስ አጣቅሰን ብናስተምርበት እኛም በግላችን መጽሐፉን ብናነበው ብናጠናው ብንማረውም ክፋት የለበትም እንደገናም የነወንጌላዊ ዶክተር ገብሩ ወልዱ የመንፈስቅዱስ ስጦታዎችና አጠቃቀማቸው የሚለው መጽሐፍ ብዙዎችን የጠቀመ ለመንፈስቅዱስ ሙላትና አሰራር ያዘጋጀ ታላቅ መጽሐፍ ነው እኔና ጓደኞቼም በዘመናችን በብዙ ተጠቅመንበታል የእግዚአብሔርንም ትልልቅ እውነቶች አግኝተንበታል ከዚህ ከከበረው የእግዚአብሔር መንፈስም ጋር በዚሁ መጽሐፍ በብዙ ተዋውቀናል ሌሎችም የእግዚአብሔር ባሮች እነ ፓስተር በቀለ ወልደ ኪዳን እነ ወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን እነ ዶክተር መለሰ ወጉና የመሣሠሉት የጻፉዋቸው መጻሕፍት ለትውልድ የእውቀትን በር የከፈቱና ከዚሁ ከመጽሐፍቅዱሳችንም ጋር ትውልድን በብዙ ያስተዋዋቁ በመሆናቸው በዚህ አጋጣሚ እነዚህን የጠቀስኳቸው የእግዚአብሔር ባሮችና ሌሎችንም ያልጠቀስኳቸውን ጸሐፍት አገልጋዮቻችንን በብዙ ልባርካቸው ላመሰግናቸውም እውዳለሁ ደግሞም ዘመናቸው ሁሉ የተባረከ እንዲሆን እጸልይላቸዋለሁ ይህ በእንዲህ እንዳለ ታድያ ከመጽሐፍቅዱሳችን ሌላ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ አንዳንድ መጻሕፍትም በተመሣሣይ መልኩ ከመጽሐፍቅዱሱ ቃል ጋር በማይቃረን ሁኔታ ተጽፈው የሰፈሩልን እውነቶች አሉ በመሆኑም እነዚህን እውነቶች ሳንታክት በማንበብ እየፈለፈልን በምናገኝበት ጊዜ በዚህ ዘመን በአማኞች ቤተክርስቲያን ያሉትን አገልጋዮች ስም በጥቂቱም ቢሆን አንስቼ እንደባረኳቸው ዛሬም እንዲሁ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከመጽሐፍቅዱሱ ቃል ጋራ በልተጋጨ ወይም ባልተጣረሰ መልኩ የእግዚአብሔርን እውነት የጻፉልንን ባሮች በብዙ ልባርካቸው እወዳለሁ ይህን ያልኩት መጻሕፍቶቻቸውን ጊዜ ወስጄ አንብቤና አጥንቼ የእግዚአብሔርን እውነት ከማግኘቴ የተነሳ ነው ታድያ ካገኘናቸው ከእነዚህ የእግዚአብሔር ቃል እውነቶች የተነሳ ነው የዛሬዋን ኦርቶዶክስ ወደ ጥንተ መሠረትዋ ወደ እግዚአብሔር ቃል እውነት ትመለስ የምንለው ምንም ነገር ሳናገኝ ያነበብነው ነገርም ሳይኖር እንዲሁ ይህንን አባባል ይዘን አልተነሳንም ከእኛ በፊት የነበሩት አባቶች በጽሑፋቸው ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይጋጨውን እውነት አስተምረውና ጽሑፋቸውንም ትተውልን ሄደውል ይህ የሠሩት መልካም ሥራም ሲዘከር ሲተረክና ሲነገር ይኖራል ስለዚህ ወገኖቼ ሃይማኖተ አበው መጽሐፍንና ሌሎችንም የኦርቶዶክስ መጽሐፍንም መጥቀስ ያስፈለገኝ ከዚህ የተነሣ ነውና እነዚህን አባቶች አሁንም እግዚአብሔር በብዙ ይባርካቸው እላለሁ ለትውልዱም የማስተላልፈው አንድና አንድ ነገር ነው ትውልድ ሆይ እምነት አለኝና በእምነቴ ጽንቼ እኖራለሁ የምትል ከሆነ መጻሕፍትን ጽፈህ ለትውልድ የማሻገር አቅም ወይም ደረጃ ላይ ባትደርስ እንኳ መጻሕፍትን ግን ሳትንቅና ሳትሳነፍ አንብብ ስል እመክራለሁ ምክንያቱም የእኛ ሕዝብ በአብዛኛው አንባቢ አይደለም ነገር ግን በብዙ አስተያየት የሚሰጥ ነው ማንበብ ሲታከልበት ግን አስተያየታችን ሙሉ ይሆናል የመንግሥቱም ሥራ እንደሚገባ ይራመዳል 6ኛ )ከዚህም ሌላ የወንጌሉን እውነትና የእግዚአብሔርንም ቃል ለሙስሊም ሕዝብ ለማድረስ እግዚአብሔር ያስነሳቸው ሰዎች ወንጌል ያልገባበት ቦታ የለምና ለሙስሊሙ ሕዝብ ወንጌሉን ከቁርዓን ጠቅሰው ነው የሚያሳዩት እኛም ለኦርቶዶክስ ሕዝብ የእግዚአብሔርን ቃል ከኦርቶዶክስ መጽሐፎች ጠቅሰን እንዲሁ እናስተምራለን 7ኛ)ሰባተኛውና የመጨረሻው መልዕክቴ ደግሞ በኦድዮ መልዕክታችንና ትምህርታችን ላይ የኦርቶዶክስ ዘማርያን መዝሙሮችን ከመዝሙሩም ጋር የተቀናጁትን ነገሮች ሁሉ አብረን ተጠቅመናል ነገር ግን አንድ እውነት የምናገረው ከዚህ በፊትም እንደተናገርኩት እነዚህን ዘማሪዎች በፍጹም አላውቃቸውም ግንኙነትም የለኝም ነገር ግን አሁንም መዝሙሮቻቸው በኢንተርኔት ላይ ሕዝብ እንዲጠቀምበትና እንዲባረክበት ተለቆ ያለ መዝሙር በመሆኑ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ሳይጋጭ በትክክል የተዘመረ መዝሙር ነውና እኔም ለትምህርቴ እንደ መግቢያና መነሻ መዝሙር አድርጌ ተጠቅሜዋለሁ ወደፊትም እጠቀምበታለሁ ይህ የእኛ ሚኒስትሪ ሰዎች የትም ቦታ ይሁኑ ፣ ከየትም ቦታ ሆነው ይዘምሩ የእግዚአብሔርን ቃል እስከዘመሩና እስካመሰገኑ ድረስ መዝሙሩንም ሆነ ቃሉን ይቀበላል አብሮም ይዘምራል ያመሰግናል ዓላማችን የእግዚአብሔርን ቃል ለሰዎች ማድረስ ነው እኛ የምንለው የእግዚአብሔር ቃል በትክክለኛውና በተጻፈው ሃሳቡ ይሰበክ ይዘመር ይመልክ ነው ሌላውን ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ ወደፊት የምንገልጸው ይሆናል እንግዲህ በዚህ ተከታታይ በሆነው በኦድዮ ትምህርት ተባረኩበት ተጠቀሙበት ወደፊትም ሊጠቀሙ ለሚፈልጉ ሰዎች አስተላልፉት እያልኩ እሰናበታችኋለሁ መልካም የበረከት ጊዜ ይሁንላችሁ አሜን

No comments:

Post a Comment